አሜሪካ የኮቪድ-19 ምልክት የማያሳዩትን የለይቶ ማቆያ ጊዜ በግማሽ ቀነሰች

አሜሪካ ምልክት ያላሳዩ እና ኮቪድ ያለባቸው ሰዎችን የለይቶ ማቆያ ጊዜ ከአስር ወደ አምስት ቀናት በማውረድ በግማሽ ቀነሰች።

የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) ከአምስት ቀናት ለይቶ ማቆያ በኋላ ደግሞ ሰዎች ባሉበት አካባቢ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መልበስ ያስፈልጋቸዋል ብሏል።

አዲሱ ምክረ ሐሳብ ግዴታ ባይሆንም በመላው አሜሪካ ባሉ ብዙ መሥሪያ ቤቶች እና ፖሊሲ አውጪዎች በቅርበት ይተገበራል።

ይህ የተገለጸው የኮቪድ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ አገርሽቶ በመላ አገሪቱ የጉዞ መሰናከል እየፈጠረ ባለበት ወቅት ነው።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኦሚክሮን ምክንያት ሆስፒታሎች ሊጨናነቁ በሚችሉበት ወቅት የመመርመሪያዎችን እጥረት ለማቃለል ቃል ገብተዋል።

ሲዲሲ ለውጡ የተደረገው በሽታው በአብዛኛው የሚተላለፈው በመጀመሪያዎቹ የህመም ጊዜያት ነው የሚለውን "ሳይንሳዊ መነሻን" መሰረት አድርጎ ነው ብሏል።

ለኮቪድ የተጋለጡ ሰዎች ያልተከተቡ ወይም ሦስተኛ ዙር ክትባት ያላገኙ ሰዎች ናቸው ሲል ምክረ ሐሳቡ ቀደም ሲል በነበረው መመሪያው ላይ አካቷል።

ሲዲሲ እነዚህ ሰዎች ለቫይረሱ ከተጋለጡ በኋላ "ለአምስት ቀናት በለይቶ ማቆያ እና ለተጨማሪ አምስት ቀናት ደግሞ ጥብቅ የአፍና አፍንጫ ጭንብልን መጠቀም ይመከራል" ብሏል።

ሲዲሲ አክሎም የማጠናከሪያ (ሦስተኛ ዙር) ክትባት የተሰጣቸው ሰዎች በቫይረሱ ከተጋለጡ ለይቶ መቆየት ባያስፈልጋቸውም ለ10 ቀናት ማስክ ማድረግ አለባቸው ሲል ገልጿል።

ለውጡን በሚገልጸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የሲዲሲ ዳይሬክተር ሮሼል ዋለንስኪ ለውጦቹ "ሰዎች የዕለት ተዕለት ህይወታቸውን ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እንዲቀጥሉ ያደርጋል" ብለዋል።

"መከላከል ምርጡ አማራጫችን ነው። መከተብ፣ ማጠናከሪያ ክትባት መከተብ፣ ሕዝብ በተሰበሰበበት እና ከፍተኛ ስርጭት ሊኖር በሚችልባቸው ቦታዎች ላይ የአፍና አፍንጫ ጭንብል ይልበሱ እና ከመሰብሰብዎ በፊት ይመርመሩ" ብለዋል።

ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ ከ200 ሺህ በላይ በኮቪድ የተያዙ ሰዎችን ባስመዘገበችው አሜሪካ ኦሚክሮን በዋነኝነት የሚስፋፋው ዝርያ ሆኗል።

ፕሬዝዳንት ባይደን ሆስፒታሎች "ሊጨናነቁ" እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል። ሆኖም አገሪቱ የኮቪድ ከፍተኛ ስርጭትን ለመቋቋም በተሻለ ሁኔታ የተዘጋጀች በመሆኗ መደናገጥ አያስፈልግም ብለዋል ።

ምርመራን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

የአስተዳደራቸው የኮቪድ ምላሽ ቡድን እና የአገረ ገዥዎችን ጥሪ መቀላቀላቸውን ገልጸው "አንዳንድ ሰዎች ቅዳሜና እሁድ ለመመርመር መቸገራቸውን ማየታችን ብዙ የምንሠራው ሥራ እንዳለን ያሳያል። በግልጽ ሲቀመጥም በቂ አይደለም" ብለዋል።

የሚወሰዱት አዳዲስ እርምጃዎች የቤት ውስጥ መመርመሪያዎችን ምርት ማሻሻል እና ጎግል በአቅራቢያ ያሉ የምርመራ ማዕከላትን ለማግኘት በቀላል አንዲጠቁም ማድረግን ያካትታሉ ብለዋል።

የአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች እና ባለሥልጣናት እየጨመረ ያለውን ስርጭት ለመግታት አዳዲስ እርምጃዎችን እያስተዋወቁ ነው። ኒውዮርክ በግል ዘርፍ ለሚሠሩ በአስገዳጅ መከተበን ጨምሮ አዲስ የክትባት መስፈርቶችን ተግባራዊ አድርጋለች።