"የቀጣዩ መጽሐፌ ርዕስ ‘ኮማ ውስጥ’ ነው" የተስፋዬ ገብረአብ የመጨረሻዎቹ ሰዓታት በወንድሙ አንደበት

ጋዜጠኛ እና ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ባለፈው አርብ ታኅሣሥ 15/2014 ዓ. ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

በኬንያ መዲና ናይሮቢ አጋ ካሃን ሆስፒታል ውስጥ ለአንድ ወር ያህል ሕክምና ሲደረግለት ቆይቶ በስተመጨረሻ በ53 ዓመቱ ማረፉን የተስፋዬ ታላቅ ወንድምና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ወንድም ነጋሲ ገብረአብ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተስፋዬ ቀዶ ሕክምና ከተደረገለት በኋላ አገግሞ እንደነበርና ታኅሣሥ 17/2014 ዓ. ም. ከሆስፒታል ይወጣል ተብሎ እየተጠበቀ ሳለ በድንገት በገጠመው የሰውነት ውስጥ ደም መፍሰስ ሳቢያ ሕይወቱ ማለፉን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

"ያረፈ ቀን ጠዋት ላይ ከተስፋዬ ጋር ስናወራ የነበረው እሑድ [ታኅሣሥ 17] ከሆስፒታል እንደሚወጣ ነበር። ድንገት ግን ሄሞግሎቢኑ [በደም ሕዋስ ውስጥ ያለ ኦክስጅን ተሸካሚ] ከ11 ወደ 4 ወረደ። ነርሶቹ ሊያተርፉት ሞከሩ። ነገር ግን ጽኑ ሕሙማን ክፍል እንኳን ሳይደርስ ሕይወቱ አለፈ" ብለዋል።

የተስፋዬ የመጨረሻዎቹ ሰዓታት

ተስፋዬ ሕይወቱ ባለፈችበት ቀን ያወራ የነበረው "ድኖ ስለመውጣት" እንደነበር ወንድም ነጋሲ ያስታውሳሉ።

ከሆስፒታል ከወጣ በኋላ የሚያርፍበት ቦታ እያዘጋጁ ነበር። ባለቤቱም ወደ ኬንያ ለመምጣት የአውሮፕላን ትኬት ቆርጣ ነበር።

"ነርሶቹ ሲገቡ እኔ ከክፍሉ ወደ ውጪ ወጣሁ። ከዚያ ድንገት ሄሞግሎቢኑ ወረደ። ነርሶቹ እንደነገሩኝ ምክንያቱ የሰውነት ውስጥ ደም መፍሰስ ነው። እዚያው ሊረዱት ሞክረው፣ እዚያው አረፈ።"

ተስፋዬ ወደ ናይሮቢ ለሕክምና የመጣው ከወር በፊት ነበር። ከቀዶ ሕክምና በኋላ እያገገመም ነበር።

"አልጋ ላይ ሳለ ፎቶ አነሳው ነበር። ሰዎች እንዴት ነው? ሲሉኝ ደኅና ነው ብዬ ፎቶ እልክላቸዋልሁ። ተስፋ የመቁረጥ ስሜት አልነበረውም" ይላሉ የተስፋዬን የመጨረሻዎቹ ቀናት ሲያስታውሱ።

ሕይወቱ ከማለፏ በፊት መጨረሻ ላይ የተነጋገሩት ከሆስፒታል ስለሚወጣበት ቀን ነበር።

ነገር ግን ከሆስፒታል እወጣለሁ ብሎ ተስፋ ካደረገበት ከሁለት ቀናት በፊት አረፈ።

ሕመሙ ምን ነበር?

ተስፋዬ የታመሙ ከሁለት ወር በፊት ነበር።

ወንድም ነጋሲ እንደሚሉት "እግሩ ድንገት አበጠ። እግሩ ላይ ላፕቶፕ አስቀምጦ ረዥም ሰዓት ይጽፍ ስለነበር የሕመሙ ምክንያት እሱ ነው ብሎ ችላ ብሎት ነበር።"

እብጠቱ እየጨመረ ሲሄድ ለሕክምና አሥመራ ወደሚገኝ ሆስፒታል ሄደ። እብጠቱ የደም መርጋት እየፈጠረ እንደሆነና ሌላም ሕመም ሊኖርበት ስለሚችል ወደተሻለ ሕክምና እንዲሄድ ተነገረው።

በወቅቱ ቤተሰቡ የተስፋዬ ሕመም እምብዛም ከባድ ነው ብሎ እንዳልገመተ ያስታውሳሉ። ከአንድ ወር በፊትም ወደ ናይሮቢ መጡ።

"ውስጡ እንደ እጢ ያለ ነገር እንዳለ ተነገረን። እሱ ሳይታወቀው ለረዥም ዓመታት የቆየ ነበር። ከዚያም ወደ ቀዶ ሕክምና ተወስዶ ጥሩ እያገገመ ነበር። ለሕይወቱ የሚያሰጋ ነገር አልተነገረንም። አሁን ሄደ፣ ሞተ ተብሎ እየተጠበቀ አልነበረም" ይላሉ።

ተስፋዬ በመጨረሻዎቹ ቀናት ፍርሀት እንዳልታየበት ወንድም ነጋሲ ያስታውሳሉ። በየቀኑ አጠገቡ ስለነበሩ ብዙ ያወጉ ነበር።

እንዲያውም ከቀዶ ሕክምናው በኋላ "እስኪርብቶ እና ወረቀት ስጠኝ" ነበር ያላቸው።

'ወደ ሰማይ ስትሄድ ግን እዚህ ያልኖርከውን ፍቅር ነው የምትኖረው'

ተስፋዬ ከቀዶ ሕክምና ሲወጣ ከወንድሙ ከአቶ ነጋሲ እስኪርብቶ እና ወረቀት ጠየቀ።

ከዚያም የቀጣዩ መጽሐፌ ርዕስ "ኮማ ውስጥ" ነው ብሎ ጻፈ።

መጻፍ ቢከብደውም ይሞክር እንደነበር ወንድሙ ይናገራሉ። "ኮማ ውስጥ" 10 ገጽ ደርሶም ነበር።

ወንድም ነጋሲ እንደሚሉት የመጽሐፉ ታሪክ፤ ምድር ላይ ያለውን መከፋፈል እና ጥላቻ፤ ሰማይ ቤት ካለው ፍቅር አንጻር ያወሳል።

"ታሪኩ ተስፋዬ ኮማ ውስጥ ሳለ የታየው ነገር ይመስላል። የእሱን ተሞክሮ፣ መሬት ላይ ያለውን መከፋፈል እና ጥላቻን አንስቶ፤ 'ወደ ሰማይ ስትሄድ ግን እዚህ ያልኖርከውን ፍቅር ነው የምትኖረው' ብሎኝ ነበር።"

ተስፋዬ ወደ ሕትመት የገባ "ቀይ ዘመን" የተባለ መጽሐፍን ጨምሮ ሌሎችም ጅምር ሥራዎች፣ ሐሳቦችም እንደነበሩት ወንድም ነጋሲ ይገልጻሉ።

"ቀይ ዘመን ስለ ድሮ ነገሥታት፣ ስለ ባሕረ ነጋሲ አጫጭር ታሪኮች የያዘ ነው። ማስታወሻ ደብተሩ ላይ ወደ አራት ሥራዎች ርዕሳቸውን ጽፎ፣ ሲያቅድ አየው ነበር። ካገገመ በኋላ "ሰቆቃው ሰሚራ" የሚል ጽሑፍ አቅዶም ነበር።"

ተስፋዬ የሚመጡለትን ሐሳቦች በአጠቃላይ መዝግቦ ከያዘ በኋላ በተለያየ ጊዜ ይጽፋቸዋል።

"መጽሐፍ ልጀምር ብሎ ጀምሮ አይጨርስም። አንደኛውን እየጻፈ ሌላውን ይጀምረዋል" በማለት ነው ነጋሲ የአጻጻፍ ስልቱን የሚገልጹት።

የተስፋዬ ልጆች

ተስፋዬ ባለ ትዳር እና የሦስት ልጆች አባት ነበር። ልጆቹ የ12፣ የ9 እና የ8 ዓመት ናቸው።

የመጀመሪያ ልጁ የአማርኛ መጽሐፉን እንደምታነብ ወንድም ነጋሲ ይናገራሉ።

"ልጆቹ እሱን እያዩ ያነባሉ፤ ሊጽፉ ይሞክራሉ። ምናልባት እንደሱ ፀሐፊ ሊሆኑ ይችላሉ። ሲጽፍ ከእሱ ሥር አይጠፉም። ከቤተሰቡ ጋር ቅርብ ግንኙት ነበረው" ሲሉ ይገልጻሉ።

የቢሾፍቱ ናፍቆት

ተስፋዬ ነሐሴ 22/1960 ዓ. ም. ከኤርትራውያን ቤተሰቦቹ በቢሾፍቱ ከተማ ነበር ተወልዶ ያደገው።

ቤተሰቦቹ ቢሾፍቱ ውስጥ ልጆች አፍርተው ለዓመታት ኖረዋል።

ከዓመታት በፊት ቢሾፍቱን ቢለቅም አንድ ቀን እንደሚመለስ ተስፋ ያደርግ እንደነበር ወንድሙ ይናገራሉ።

ወንድማማቾቹ ስለ አብሮ አደጎቻቸው፣ ስለሚያውቋቸው ቦታዎችም በትውስታ ያወሩ ነበር።

"እንደሁላችንም ለቢሾፍቱ የተለየ ፍቅር አለው። ትስስር አለው። እርግጠኛ የነበረው ወደ ቢሾፍቱ እንደሚመለስ ነበር። ይናፍቅ ነበር። ያስብ ነበር። ቢሾፍቱ መምጣት፣ ማየት፣ መቀመጥ ይፈልግ ነበር። ሳይመለስ በማለፉ በጣም አዝናለሁ።"

ተስፋዬ ለቢሾፍቱ ካለው ፍቅር አንጻር በቢሾፍቱ የመቀበር ፍላጎት እንደነበረው የተጠየቁት ወንድሙ፤ ከተስፋዬ ጋር ስለ ቀብር እንዳላወሩና የሚቀበርበት ቦታ ምርጫ የቤተሰቡ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከኤርትራ ወደ ኬንያ ሲበሩ አውሮፕላኑ "በቢሾፍቱ በኩል ያልፋል" እያሉ ማውራታቸውን ያስታውሳሉ።

"በአየር እያለፍን ወደ ኬንያ ስንሄድ ጨለማ ስለነበር ምንም አላየንም። ከኬንያ ስንወጣ ግን በቢሾፍቱ ነው የምናልፈው ብለን ተነጋግረን ነበር። ሞቶ በቢሾፍቱ ከሚቀበር በሕይወት እያለ ቢያየው የበለጠ ትርጉም ይኖረው ነበር።"

ተስፋዬ እና አወዛጋቢ ጽሑፎቹ

ተስፋዬ በደርግ ዘመን ማብቂያ አካባቢ በጦር ሠራዊቱ ተመልምሎ ሥልጠና ከወሰደ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወታደራዊው መንግሥት ሲወድቅ ከኢሕአዴግ ጋር ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ጋዜጠኛ ሆኗል።

ዕለታዊዎቹን የመንግሥት ጋዜጦች የሚያሳትመው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ነበር። "እፎይታ" መጽሔትንም መርቷል።

የጋዜጠኝነት ሥራውን ካቆመ በኋላ አስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ የሙሉ ጊዜ ጸሐፊ በመሆን ከስምንት በላይ ሥራዎችን ለአንባቢያን አድርሷል።

"እፍታ" በሚል ርዕስ ከ1992 እስከ1993 ዓ. ም. የአጫጭር ጽሑፎች ስብስብ የሆኑ አምስት ቅጾችን አሳትሟል።

"ገዳ" በሚለው ስም በበርካቶች የሚጠራው ተስፋዬን በአንባቢያን ዘንድ በስፋት ያስተዋወቀው "የቡርቃ ዝምታ" የተሰኘው ረዥም ልብ ወለዱ ነው።

የገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ እና የባለሥልጣናቱ የውስጥ ምስጢሮችን የያዙትን "የጋዜጠኛው ማስታወሻ" እና "የደራሲው ማስታወሻ" መጻሕፍትንም ለንባብ አብቅቷል።

ከህወሓት የትግል ጅማሬ እስከ ኢሕአዴግ አዲስ አበባ መግባት ድረስ ያለውን ዘመን የሚተርከው ተከታታዩ "ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ" ይጠቀሳል።

ተስፋዬን በሥነ ጽሑፍ ችሎታው የሚያሞካሹት እንዳሉ ሁሉ በሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች የሚተቹትም በርካቶች ናቸው።

በአንድ በኩል በኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች መካከል 'መቃቃርን' ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል በሚል በርካቶች ይወቅሱታል።

በሌላ በኩል ጽሑፎቹ የተዳፈኑ የጭቆና ታሪኮችን ያነሳሉ፣ የተገለሉ ማኅበረሰቦችን እውነታም ያንጸባርቃሉ ብለው የሚከራከሩ ወገኖች አሉ።

ስለእነዚህ ጽሑፎቹ የጠይቅናቸው ወንድም ነጋሲ "አንድ ታሪክ ውስጡን ከነካው፣ ይጠቅማል ብሎ ካሰበው ከመጻፍ ወደኋላ አይልም። የተለየ ወይም አንድ ነገር ላይ ያተኮረ ጥላቻ ያለበት መስሎ አይሰማኝም" ሲሉ መልሰዋል።

ከእሱ ጋር የማይስማሙ ሰዎች "ተንኮል አስቦ፣ ሊያጣላ ነው የጻፈው" ሲሉ መስማታቸውን አይክዱም።

የወንድም ነጋሲ ምላሽ "እንደ ሰው ሳየው የተለየ አስቦ፣ አስልቶ የሚያደርገው ነገር አላስታውስም። እንዲህ ያለ ነገር አይኖርምም፤ የለምም" የሚል ነው።

ከተስፋዬ ጋር አብረው እንደኖሩ እንዲሁም ሲጽፍ ያለውን ስሜት በቅርብ እንደሚያውቁ ጠቅሰው "የተለየ የጥላቻ መንፈስ በውስጡ አይቼበት አላውቅም። ያመነበትን እና ያየውን የሚጽፍ ሰው ሆኖ ይሰማኛል" ይላሉ።

ላደጉበት ቢሾፍቱ ሁለቱም ልዩ ፍቅር እንዳላቸው፣ ከተለያዩ ማኅበረሰቦች ከተውጣጡ ሰዎች ጋር በጉርብትና መኖራቸውን ያወሳሉ።

ተስፋዬ ለጓደኝነት የሚመርጠው የጥበብ ሰዎችን እንደሆነም ይናገራሉ።

የኢሕአዴግ ዋነኛ ሰው ሆኖ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ የቆየው ተስፋዬ፤ እሱ እንደሚለው ከአገሪቱ ዋነኛ ፖለቲከኞች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ከኢትዮጵያ ተሰዷል።

በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በኔዘርላንድስ እና ኋላ ላይም በኤርትራ ኖሯል።

የተስፋዬ ጽሑፎች አወዛጋቢ እንደሆኑ አይካድም።

አድናቂዎቹም ተቺዎቹም በርካታ የሆኑት ተስፋዬ፤ በተለይም በዘመናዊ የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ በጉልህ ከሚጠቀሱ ጸሐፍት አንዱ ነው።