በሱዳን የፀጥታ ኃይሎች በተቃዋሚዎች ላይ ከመጠን ያለፈ ኃይል ተጠቅመዋል ተባለ

በሱዳን መንግሥት ወታደራዊ መሪዎች ላይ የሚካሄደው ተቃውሞ በቀጠለበት በአሁኑ ጊዜ የፀጥታ ኃይሎች በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ ከመጠን ያለፈ ኃይል ተጠቅመዋል በሚል ክስ ቀረበባቸው።

የተቃውሞ እንቅስቃሴውን የሚደግፈው የዶክተሮች ቡድን ባወጣው አሀዝ ቅዳሜ ዕለት በተደረገው ተቃውሞ ሰልፍ ላይ ከተሳተፉ ሰዎች መካከል 178 የቆሰሉ ሲሆን፣ የፀጥታ ኃይሎች በተቃዋሚዎች ላይ ጥይት ተኩሰዋል ሲል ከሷል።

የሱዳን መንግሥት ባለሥልጣናት በበኩላቸው በተቃውሞ ሰልፎቹ ወቅት በ58 የፖሊስ መኮንኖች ላይ የመቁሰል ጉዳት ደርሷል ሲሉ ተናግረዋል።

ጨምረውም ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ በዋና ከተማዋ ካርቱም ውስጥ ከ100 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክተዋል።

ቅዳሜ ዕለት በተደረጉት ዴሞክራሲያዊ ለውጥን በሚጠይቁት የተቃውሞ ሰልፎች ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ወታደራዊ ባለሥልጣናቱን የሚቃወሙ መፈክሮችን እያሰሙ ወደ ፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት ቀርበው ነበር።

እዚያም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፀጥታ ኃይሎች የጠበቋቸው ሲሆን ተቃዋሚዎቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭሽ ተኩሰዋል።

ከካርቱም በተጨማሪ የወደብ ከተማዋን ፖርት ሱዳንን ጨምሮ በሌሎችም ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል እዚያም የፀጥታ ኃይሎች ተቃዋሚዎችን መደብደባቸውና ማሰራቸው ሪፖርት ተደርጓል።

ባለፈው ሳምንት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ካርቱም ውስጥ ወደ ጎዳና ወጥተው አገሪቱ ወደ ሲቪል አስተዳደር እንድትመለስ መጠየቃቸው ይታወሳል።

በዚህም ከፖሊስ ጋር በተፈጠረ ግጭት ከ100 በላይ ሰዎች የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በተጨማሪም የፀጥታ ኃይሎች በርካታ ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት ፈጽመዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ከሦስት ዓመት በፊት በተደረሰውና ባልተከበረው የሥልጣን ክፍፍል ስምምነት መሠረት የሱዳን የሽግግር መንግሥት መሪ የነበሩትና የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄነራል አል ቡርሐን ሥልጣናቸውን ለሲቪል ፖለቲከኞች ማስረከብ የነበረባቸው ባለፈው ኅዳር ወር ላይ ነበር።

ጄነራሉ መፈንቅለ መንግሥት ያካሄዱት ፖለቲከኞች ሰላማዊ ሰዎችን በፀጥታ ኃይሎች ላይ እያነሳሱ በመሆናቸው የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይከሰት ለመከላከል ነው ሲሉ የእርምጃቸውን ተገቢነት ገልጸው ነበር።

ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ ወደ ሥልጣናቸው ከተመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር በተደረሰው ስምምነት ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ የባለሙያዎች ካቢኔ እንደሚኖራቸው ተገልጿል።

ጄነራሉ እንደሚሉት ሱዳን አሁንም በሽግግር ሂደት ላይ እንደሆነችና አገሪቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለማሻገር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸው ከሁለት ዓመት በኋላ ምርጫ እንደሚካሄድ አመልክተዋል።

የሱዳን የጦር ሠራዊት ከፍተኛ መሪ የሆኑት የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን በመንግሥታቸው ላይ የሚካሄደው ተቃውሞ ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት እንቅፋት ይሆናል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ተቃዋሚዎች ግን የዛሬ ሦስት ዓመት ኦማር ሐሰን አል ባሽርን ከሥልጣን ያስወገደውን ሕዝባዊ አብዮት የአገሪቱ ጦር ኃይል ጠልፎታል በማለት ይከሳሉ።