በሱዳን የዴሞክራሲ ደጋፊ ሰልፈኞች በአደባባይ ተቃውሟቸውን ማሰማት ቀጥለዋል

የሱዳን የጸጥታ ሃይሎች በመዲናዋ ካርቱም ዴሞክራሲን እንደግፋለን የሚሉ ተቃዋሚዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተኩሰዋል።

ተቃዋሚዎቹ በሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት ቢሰበሰቡም ከፍተኛ የጸጥታ ኃይሎች አላፈናፍን ብለዋቸዋል።

ወታደራዊው መንግሥት ለሰልፈኞቹ የአደባባይ ተቃውሞ አጸፋዊ ምላሽ በከተማዋ የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎቶችን ገድቦ እንደነበር ዘገባዎች አመልክተዋል።

ፖርት ሱዳንን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችም የአደባባይ ተቃውሞች ታይተዋል።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በሱዳን የተፈጠረውን መፈንቅለ መንግሥት በመቃወምና የሲቪል አገዛዙ ይመለስ የሚል ጥያቄም አንግበው ወደ አደባባይ ወጥተዋል።

ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ተቃውሞ ከፖሊስ ጋር በተፈጠረ ግጭት ከ100 በላይ ሰዎች ቆስለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የጸጥታ ሃይሎችም ከ12 በላይ ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የመድፈር ወንጀሎችን ፈጽመዋል የሚል ክሶች ቀርቦባቸዋል።

በሱዳን ጦሩ ስልጣንን በሃይል የተቆጣጠረበትን ሁለተኛ ወር በማስመልከት፣ ኢንተርኔት ከመቋረጡ በፊት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በትናንትናው ዕለት ተከታታይ የአደባባይ ላይ የተቃውሞ ሰልፎች አቅደው ነበር።

አንድ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደገለጹት የኢንተርኔት መቋረጥ የተፈጠረው ዘርፉን የሚቆጣጠረው የሱዳን ብሄራዊ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን (ኤንቲሲ) ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነው።

በመዲናዋ ተጨማሪ የጸጥታ ሃይሎች መሰማራታቸውንና ካርቱምን ከሌሎች ከተሞች ጋር የሚያገናኙት የናይል ወንዝ ድልድዮች መዘጋታቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የአደባባይ ተቃውሞው ደጋፊ የሆነው የዶክተሮች ማህበር እንዳሳወቀው የጸጥታ ሃይሎች ጉዳት የደረሰባቸውን ተቃዋሚችን እያሳደዱ እንደነበረና በሆስፒታል ውስጥ አስለቃሽ ጭስ እና ፈንጂ መተኮሳቸውን ነው።

የመፈንቅለ መንግስቱ መሪ ጄኔራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን በጥቅምት ወር ጦሩ ስልጣንን በኃይል የተቆጣጠረው የፖለቲካ ቡድኖች ሰላማዊ ዜጎች በጸጥታ ኃይሎች ላይ እንዲነሱ ከመቀስቀሳቸው ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችለውን የእርስ በርስ ጦርነት ለመከላከል ነው ሲሉ ተሰምተዋል።

ከአመት በኋላ ሊታቀድ ለተደረገው ምርጫና ወደ ሲቪል አገዛዝ ለመሸጋገር ቁርጠኛ እንደሆኑም ተናግረዋል። ነገር ግን አዲሱ ሲቪል መንግሥት በወታደራዊው ጫና ስር ስለሚውል ምን ያህል ስልጣን ይኖረዋል የሚለው ጥያቄን አጭሯል።

ጄኔራሉ አሁን እየተካሄዱ ያሉ ተቃውሞዎች ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ሽግግርን ሊያደናቅፍ እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።

የዲሞክራሲ ደጋፊ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ለረዥም ዘመን ሱዳንን የገዙትን ኦማር አልበሽር ከስልጣን እንዲወገዱ ምክንያት የሆነውን አብዮት ጦሩ ጠልፏል በማለት ይከሷቸዋል።