ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወልዲያን ጨምሮ የሰሜን ወሎ ዞን ከህወሓት አማጺያን ነጻ መውጣቱ ተገለጸ
የወልዲያ ከተማን ጨምሮ በህወሓት ቁጥጥር ስር የቆዩ የሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ ነጻ መውጣታቸውን መንግሥት አስታወቀ።
ከወራት በፊት በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ገብታ ለረጅም ጊዜ የቆየችውን የወልዲያ ከተማና ሌሎች በአማጺያኑ ቁጥጥር ስር የቆዩ ሲሆን አሁን በመንግሥት ቁጥጥር ስር መግባታቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ገልጸዋል።
በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው የወልዲያ ከተማ በህወሓት የተያዘችው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ የነበረ ሲሆን ለአራት ወር ያህል በአማጺያኑ ቁጥጥር ስር ቆይታለች።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ቅዳሜ ታኅሣሥ 09/2014 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ እንዳስታወቀው የኢትዮጵያ ጥምር የፀጥታ ኃይሎች ባካሄዱት ዘመቻ ሳንቃን፣ ሲሪንቃን፣ ሰሜን ወሎ ዋና ከተማ የሆነችውን የወልዲያ ከተማን፣ ሐራን፣ ጎብዬን፣ ሮቢትን እና ቆቦን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዋል።
በተጨማሪም የሐሙሲት፣ እስታይሽ፣ አሁን ተገኝ፣ ድልብ፣ ኩል መስክ እና በዙሪያቸው ያሉ አካባቢዎችም በመከላከያ ሠራዊትና በክልል ልዩ ኃይሎች ነጻ መውጣታቸው ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ጥምር ኃይሉ ባለፈው ሳምንት ተመልሳ በህወሓት ኃይሎች እጅ መግባቷ የተነገረው "የላሊበላ አካባቢን ከአማጺያኑ በማጽዳት፣ ወደ ሰቆጣ ከተማና በዙሪያው ወዳሉ አካባቢዎች" ማምራቱን በመግለጽ ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማና አካባቢዋ ተመልሰው በቁጥጥር ስር መግባታቸውም ተገልጿል።
መንግሥት ጨምሮም አሁን ነጻ የወጡት አካባቢዎችና ከተሞች ለረዥም ጊዜ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር የቆዩ በመሆናቸው አማጺው በነዋሪዎች ላይ በርካታ በደሎችን ሲፈጸምባቸው ነበሩ ብሏል።
የህወሓት ኃይሎች ጥቃታቸውን ወደ አማራ እና አፋር ክልል ባስፋፉበት ጊዜ በቁጥጥራቸው ስር ያስገቧት የመጀመሪያዋ ትልቅ ከተማ ወልዲያ ስትሆን፣ መንግሥት በአማጺያኑ ላይ የከፈተውን መልሶ ማጥቃት ተከትሎ ነጻ ልትወጣ ችላለች።
የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ማዕከል የሆነችው የወልዲያ ከተማ በመንግሥት ቁጥጥር ስር መግባቷ ይፋ የተደረገው የደቡብ ወሎ አቻዋ ደሴ ከህወሓት ቁጥጥር ነጻ ከወጣች ከሁለት ሳምንት ገደማ በኋላ ነው።
ከአዲስ አበባ በ520 ኪሎ ሜትሮች ላይ የምትገኘው ጥንታዊቷ የወልዲያ ከተማ ከ200 ሺህ በላይ ነዋሪ እንዳላት የሚነገር ሲሆን፣ በዙሪያዋ ላሉ ሌሎች የሰሜን ኢትዮጵያ ትልልቅ ከተሞች እንደ ማዕከል የምትታይ ናት።
በዚህም ወልዲያ በስተ ምዕራብ ከአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር 360 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ ደግሞ 260 ኪሎ ሜትሮች ትርቃለች።
በተጨማሪም ወልዲያ ከታሪካዊቷ ላሊበላ 168 ኪሎ ሜትር እና በአፋር ክልል በኩል የኢትዮጵያ አብዛኛው ገቢና ወጪ ንግድ ከሚስተናገድበት የጅቡቲ ወደብ 553 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።
ባለፈው ዓመት በትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክሎች የተስፋፋው ጦርነት ከጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ ተባብሶ ከሰሜን ወሎ ወደ ደቡብ ወሎ በመስፋፋት ወሳኝ የሚባሉት የደሴና የኮምቦልቻ ከተሞች በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከገቡ በኋላ ወደ ሰሜን ሸዋ ተስፋፍቶ ነበር።
የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልል በመግባት ዘመቻ በማካሄዳቸው በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የተለያዩ ቦታዎችን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ለማቅናት ፍላጎት እንዳለቸው ሲገልጹ ቆይተው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ግንባር በመሄድ ሠራዊቱን ለመምራት መወሰናቸውን ተከትሎም በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ለማስለቀቅ ውጊያዎች ተጠናክረው ሲካሄዱ ቆይተዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ግንባር በመሄድ ሠራዊቱን መምራት መጀመራቸውን ተከትሎ የአማጺያኑ ግስጋሴ ከመገታቱ በተጨማሪ ይዘዋቸው ከነበሩ የአፋርና የአማራ ክልል አካባቢዎች ለቀው ለመውጣት ተገደዋል።
በዚህ የማጥቃት ዘመቻ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከልዩ ኃይልና ከሚሊሻው በተጨማሪ የአገሪቱ አየር ኃይል የተሳተፈ መሆኑ ተገልጿል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ትግራይ ውስጥ ሲካሄድ ቆይቶ የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም በማወጅ ሠራዊቱን ከክልሉ ካስወጣ በኋላ ነበር የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች በመዝለቅ ጥቃት የከፈቱት።
በዚህም ሳቢያ በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ቦታዎችን በመቆጣጠር እስከ ሰሜን ሸዋ ለመድረስ ችለው ነበር።
ይህንንም ተከትሎ በኅዳር ወር የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት፣ ከአፋርና ከአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች እንዲሁም ሚሊሻዎች ጋር በመቀናጀት ባካሄዱት የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ የህወሓት ኃይሎች ከአፋር ክልል ሙሉ ለሙሉ እንዲሁም አሁን ደግሞ ከሰሜን ወሎ ዞን ሙሉ ለሙሉ ለማስወጣት መቻላቸው ተገልጿል።