የኢትዮጵያ ሠራዊት በርካታ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ ወደ ወልዲያ እየተቃረበ መሆኑ ተነገረ

የኢትዮጵያ ጥምር የፀጥታ ኃይሎች በሰሜን ወሎ ውስጥ ባካሄዱት ዘመቻ ተጨማሪ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው ወደ ወልዲያ እያቀኑ መሆናቸውን መንግሥት ገለጸ።

የመከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይልና ሚሊሻዎች ባለፉት ቀናት በሰሜን ወሎ ውስጥ ባሉት የህወሓት ኃይሎች ላይ በወሰዱት እርምጃ መርሳ እና ጊራናን ነጻ አውጥተው ተቆጣጥረዋል ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።

የአገሪቱ ጥምር የፀጥታ ኃይሎች ቀደም ሲል በቆቦ ግንባር ተቆጣጥሯቸው ከነበሩት የዞብል ከፍተኛ ቦታዎች በተጨማሪ በራያ ሰሜናዊ አቅጣጫ ያሉትን ከፍተኛ ቦታዎችን ጨምሮ በቁጥጥራቸው ስር ማስገባታቸው ተነግሯል።

እንዲሁም ከዞብል ከፍታማ ቦታዎች ደቡብ አቅጣጫ ጉራ ወርቄ የተባሉ አካባቢዎችን የመንግሥት ኃይሎች ተቆጣጥረዋቸው የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ የጉራ ወርቄን ከፍተኛ ሰንሰለታማ ቦታዎችን ሙሉ በሙሉ ነጻ አውጥተዋል ተብሏል።

ባለፈው ሳምንት ለወራት በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ያለው ከወልዲያ ከተማ ወደ መቀለ የሚወስደው መስመር በኢትዮጵያ ኃይሎች መቆረጡ የተነገረ ሲሆን፣ ሠራዊቱ በዚሁ መስመር ይዞታውን በማስፋት ከወልዲያ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በተጨማሪም ቀደም ሲል የውጫሌ ከተማን የተቆጣጠረው ጥምር ኃይሉ፣ በዘመቻው በመግፋት የውጫሌ ወረዳን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ውርጌሳን፣ ሊብሶን፣ ጊራናን፣ መርሳንና ኪሌ ከተሞችን እንዲሁም በሰሜን ወሎ የሐብሩ ወረዳን ሰንሰለታማ ተራሮችን መቆጣጠሩ ተነግሯል።

በዚህ የማጥቃት ዘመቻ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከልዩ ኃይልና ከሚሊሻው በተጨማሪ የአገሪቱ አየር ኃይል የተሳተፈ መሆኑ ተገልጿል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ትግራይ ውስጥ ሲካሄድ ቆይቶ የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም በማወጅ ሠራዊቱን ከክልሉ ካስወጣ በኋላ ነበር የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች በመዝለቅ ጥቃት የከፈቱት።

በዚህም ሳቢያ በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ቦታዎችን በመቆጣጠር እስከ ሰሜን ሸዋ ለመድረስ ችለው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ በኅዳር ወር የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት፣ ከአፋርና ከአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች እንዲሁም ሚሊሻዎች ጋር በመቀናጀት ባካሄዱት የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ የህወሓት ኃይሎች ከአፋር ክልል ሙሉ ለሙሉ እንዲሁም ከአብዛኛው የአማራ ክልል ለማስወጣት ችለዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አርብ ምሽት ይፋ ባደረገው መረጃ ላይ የተጠቀሱት የመንግሥት ኃይሎች የተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች በሰሜን ወሎ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።