ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ ዳግም በህወሓት አማጺያን ቁጥጥር ሥር መግባቷ ተዘገበ
ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ በድጋሚ በህወሓት አማጺያን እጅ መግባቷን የዓይን እማኞችን በመጥቀስ ሮይተርስና አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገቡ።
የትግራይ ኃይሎች ከተማዋን የተቆጣጠሩት ያለምንም የተኩስ ልውውጥ መሆኑንም የዜና ወኪሎቹ አመልክተዋል።
አንድ የዓይን እማኝ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት የፌዴራል መንግሥት አጋር የሆኑ ኃይሎች ቅዳሜ ምሽት ነበር ላሊበላን እየለቀቁ መውጣት የጀመሩት።
የዓለም እጅግ አስደናቂ ቅርሶች መገኛ እና በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ የምትገኘው የላሊበላ ከተማ ለመጀመርያ ጊዜ ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ነበር በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ወድቃ የነበረው።
ከዚያ ወዲህ ላሊበላ ከጥቂት ቀናት በፊት በፌዴራል መንግሥት እጅ ስር ተመልሳ ገብታ የነበረ ሲሆን ከ11 ቀናት በኋላ ደግሞ አሁን በድጋሚ የትግራይ ኃይሎች ተቆጣጥረዋታል።
የፌዴራል ኃይሎች ጥምረት ከቅርብ ቀናት ወዲህ በርካታ ከተሞችን ከአማጺያኑ በማስለቀቅ በእጁ መልሶ ማስገባት ችሎ ነበር።
የትግራዩን ጦርነት ተከትሎ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ የተከሰተ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልል በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚሹ ይፋ አድርጓል።
ለወራት በህወሐት ኃይሎች ቁጥጥር ስር የቆየችው ላሊበላ በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይል፣ በሚሊሻና በፋኖ በተካሄደ ዘመቻ በመንግሥት ቁጥጥር ስር መግባቷ የተገለጸው ከቀናት በፊት ነበር።
በወቅቱ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን እንዳስታወቀው የመንግሥት ጥምር ኃይሎች ታሪካዊቷን የላስታ ላሊበላ ከተማንና የላሊበላ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን መቆጣጠራቸውን ይፋ አድርጎ ነበር።
ሐምሌ 29/2013 ዓ.ም በአማጺያኑ ቁጥጥር ሥር ለአራት ወራት ያህል የቆየችው የላሊበላ ከተማ እና አካባቢዋ ልክ ኅዳር 22/2014 ዓ.ም ከትግራይ ኃይሎች ነጻ መውጣቷን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤትም በማኅበራዊ ገጹ ላይ አስፍሮ ነበር።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የፌደራሉ መንግሥት በህወሓት ቁጥጥር ነጻ ካወጣቸው ከተሞች መካከል ደሴ እና ኮምቦልቻ ተጠቃሽ ናቸው።
የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው ተቆጣጥሯቸው ከነበሩ የተወሰኑ አካባቢዎች እየወጡ ያሉት "ለስትራቴጂ" እንደሆነ ሲናገሩ ነበር።
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ የምትገኘው ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ፣ ከክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር 310 ኪሎ ሜትሮች ትርቃለች።
የህወሓት አማጺያን መቀመጫ ከሆነችው መቀለ ደግሞ በስተደቡብ 348 ኪሎ ሜትሮች ርቃ ትገኛለች።
ከዐለት ተፈልፍለው የተሠሩት የጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት መገኛ የሆነችው የላሊበላ ከተማ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ ከሚገኙ ትልልቅ ከተሞች መካከል አንዷ ስትሆን በሰላሙ ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጎብኚዎችን ታስተናግድ ነበር።
ለሮይተርስ ዜና አውታር እማኝነታቸውን የሰጡት አንድ ነዋሪ፣ "የመንግሥት ኃይሎች ጥምረት የመጨረሻዎቹ ወታደሮች እሁድ ጠዋት ሲወጡ ነበር። ከርቀት የተኩስ ድምጽ እንሰማ ነበር። ነገር ግን የትግራይ ኃይሎች ከተማዋን የተቆጣጠሩት በከተማ አንዳችም የተኩስ ልውውጥ ሳይደረግ ነው" ብለዋል።
የትግራይ ኃይሎች በሰጡት መግለጫ ደግሞ ሰፊ የፀረ ማጥቃት ዘመቻ በመክፈት ከላሊበላ በተጨማሪ ጋሸናን በድጋሚ መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል።
የትግራይ ኃይሎች ላሊበላን ዳግም ስለመቆጣጠራቸው በመንግሥት በኩል እስካሁን ምንም የተባለ ነገር የለም።
የላሊበላ ነዋሪዎች ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተናገሩት የትግራይ ኃይሎች ከሐምሌ መጨረሻ እስከ ኅዳር መጨረሻ በከተማዋ በቆዩባቸው ጊዜ ታሪካዊውን ቤተ ክርስቲያን በመልካም ሁኔታ ያቆዩ ቢሆንም ሕይወታቸውን አስቸጋሪ አድርጎባቸው እንደነበረ ግን አልካዱም።
አማጺያኑ ሞባይል ስልክና ምግብ አምጡ ይሉ እንደነበረና መድኃኒትም ይዘርፉ እንደነበረ ተዘግቧል።
ለዚሁ የዜና አውታር ቃሉን የሰጠ አንድ የከተማዋ ነዋሪ በርካታ የላሊበላ ነዋሪዎች በቀልን በመፍራት ከተማዋን ለቀው ሸሽተው ወጥተዋል።
የበቀል ፍርሃቱ የመንግሥት ኃይሎች ከተማዋን ከአማጺያኑ አስለቅቀው ሲቆጣጠሩ ደስታችንን በመግልጻችን ነው ብሏል።