የቻይና እና የአሜሪካ ፉክክር፣ የአፍሪካ በጋራ የመሥራት ፍላጎት

ዢ ጂንፒንግ እና ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አምባገነንነትን መከላከል በሚቻልበት መንገድ ላይ ለመምከር በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተናጋጅነት ለሁለት ቀናት በሚቆየው የዲሞክራሲ ጉባኤ ላይ 17 የአፍሪካ አገራት እየተሳተፉ ነው። ይህ በአህጉሪቱ አሜሪካ እና ቻይና ቅድሚያ የሚሰጧቸው ጉዳዮች ላይ ያለውን ተቃርኖ አጉልቶ ያሳያል ይላሉ ታዛቢዎች።

ስብሰባው በሴኔጋል መዲና ዳካር የሦስት ዓመት የቻይና-አፍሪካ ትብብር (ፎካክ) ከተካሄደ ከአንድ ሳምንት በኋላ የተካሄደ ነው። የዳካሩ ስብሰባ ቻይና የአህጉሪቱ ትልቋ የንግድ አጋር በመሆኗ ስላለው ፋይዳ አሳይቷል።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በግብርና፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በኢንዱስትሪ ልማት ዙሪያ በትንሹ የ40 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ይፋ አደርገዋል። እንዲሁም አንድ ቢሊዮን ብልቃጥ የኮቪድ-19 ክትባቶችን ለመለገስ እና በጋራ ለማምረት ቃል ገብተዋል።

በሴንተር ፎር ግሎባል ዲቨሎፕመንት ከፍተኛ የፖሊሲ ባልደረባ የሆኑት ጂዩድ ሙር "የሚጋጭ ቢመስልም አገራት ይበልጥ ዴሞክራሲያዊ በሆኑ መጠን ወደ ቻይና ይበልጥ እየተጠጉ ይሄዳሉ" ብለዋል።

"በአፍሪካ ውስጥ ትልቁ ፍላጎት መሠረተ ልማት ነው። ባለፉት 20 ዓመታት አገራት የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ፊታቸውን የሚያዞሩት ወደ ቻይና ነው" ብለዋል ።

መሠረተ ልማት ለምርጫ

በፎካክ ስብሰባ የሴራሊዮን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ጆን ፍራንሲስ ገና ያልተገነባውንና 7 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን ድልድይ ምስል ለቻይናው አቻቸው ዋንግ ዪ ሲያስረክቡ የሚያሳየው ፎቶ ቻይና በአፍሪካ ያላትን ጠቃሚ ሚና አሳይቷል።

1.2 ቢሊዮን ዶላር የተገመተው የሉንጊ ድልድይ የባሕረ ገብ ከሆነችው መዲናዋ ፍሪታውንን ከዋናው አውሮፕላን ማረፊያ ጋር የሚያገናኝ ነው። ሠዓታት የሚወስዱ እና አስተማማኝ ላልሆነው የጀልባ ጉዞ አማራጭ ነው።

አንዳንድ ታዛቢዎች ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ማዳ ባዮ የድልድዩን ፕሮጀክት ለ2023 ዳግም የምርጫቸው ዘመቻ ቁልፍ አድርገው ይመለከቱታል።

ሌሎች ደግሞ ድልድዩ ምንም የኢኮኖሚያዊ ማረጋገጫ የለውም በማለት ገንዘቡ እንደ መሃይምነት እና እናቶች ጤና ያሉ ማኅበራዊ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም ጥቅም ላይ ቢውል ሊጠቅም እንደሚችል ጠቁመዋል።

የጋምቢያ ፕሬዝዳንት አዳማ ባሮው በቻይና የተገነቡትን ድልድዮች ከጎረቤት ሴኔጋል ጋር ያለውን የንግድ ግንኙነት ስለማሳደጉ ከማንሳት ባለፈ በቻይና የሚደገፍ የመንገድ ፕሮጀክት ለመሥራት ቃል ከገቡ በኋላ በቅርቡ በድጋሚ ምርጫ አሸንፈዋል።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የምርምር ባልደረባ የሆኑት ፎላሻዴ ሱሌ-ኮንዱ እንዳሉት የአፍሪካ ፖለቲከኞች በምርጫ ወቅት ቃል የገቡትን ለመፈጸም ብዙውን ጊዜ የቻይና መሠረተ ልማት ፈንድ ያስፈልጋቸዋል።

እንደ አፍሪካ ልማት ባንክ ከሆነ አህጉሪቱ የመሠረተ ልማት ፍላጎቶቿን ለማሟላት በዓመት ከ130 አስከ 170 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል። በአሁኑ ጊዜ ያለው ከፍተኛ ጉድለት ከ68 አስከ 108 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል።

ክፍተቱት ሊሞላ የሚችለው በአዲሱ የአውሮፓ ሕብረት የ340 ቢሊዮን ዶላር የመሠረተ ልማት እቅድ (ግሎባል ጌትዌይ) እና በአሜሪካው ቢውልድ ባክ ቤተር (ቢ3ደብሊው) እቅድ ነው። ሁለቱም ለቻይና ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ (ቢአርአይ) በአማራጭነት በመተዋወቅ ላይ ናቸው።

ለጊዜው ግን ሁለቱ ፕሮጀክቶች በዓለም ዙሪያ መንገዶችን፣ የባቡር ሃዲዶችን እና ወደቦችን ከገነባው ቢአርአይ ጋር ሲነጻጸሩ ወደ ኋላ የቀሩ ናቸው።

ቻይና በኬንያ ናይሮቢ እየገነባችው ያለው የቀለበት መንገድ

የፎቶው ባለመብት, TWITTER/NAIROBI EXPRESSWAY

የምስሉ መግለጫ, ቻይና በኬንያ ናይሮቢ እየገነባችው ያለው የቀለበት መንገድ

የቻይና-አሜሪካ ብረት

የንግድ ባለሙያው የሆኑት ፍራንሲስ ማንጌኒ እንደሚሉት እነዚህ ፕሮጀክቶች ከመወዳደር ይልቅ ቅንጅት ላይ ቢያተኩሩ ለአፍሪካ ይጠቅማል።

"ቻይና በአፍሪካ ያላትን ተጽዕኖ አሉታዊ እንደሆነ ከመመልከት፣ በፉክክር እና በጠላትነት በማየት ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ሌሎች ኃይሎችም የጎደለውን ሊሞሉ ይገባል ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።

ይህ እንዲሳካ የአፍሪካ ሃገሮች የጋራ ተጽዕኗቸውን ማሳየት እንዳለባቸውም አክለዋል።

ሆኖም ግሎባል ጌትዌይ እና ቢ3ደብሊው በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማድረስ እና ብድር ላይ ብዙም በልተንጠለጠለ ኢንቨስትመንቶቹ ከቻይናው የበለጠ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል ሲሉ ሱሌ-ኮንዱ ተናግረዋል።

"አፍሪካ የመሠረተ ልማት ፈንድ የማግኛ መንገዷን ማስፋት ስላለባት ይህ መኖሩ ጥሩ አጋጣሚ ነው" ሲሉ ሙር ይስማማሉ። ቻይና በአህጉሪቱ ወጪ ቆጣቢ መሠረተ ልማቶችን በመገንባቷ በተለይም ለአሜሪካ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ተወዳዳሪነት አስቸጋሪ እንደሚሆን አክለው ገልጸዋል።

በአፍሪካ የመሠረተ ልማት፣ የጤና፣ የትምህርት እና የፀጥታ ፍላጎቶችን ለማሟላት አሜሪካ እና ቻይና የተለያዩ ጥንካሬዎች እንዳላቸው ጠቁመዋል።

"ዩናይትድ ስቴትስ በሰው ሃብት ካፒታል ኢንቨስትመንት ላይ ትልቅ ጥንካሬ አላት። ዩኒቨርሲቲዎቿ በዓለም ላይ ከሚገኙት ምርጦች ሲሆኑ የጤና ሥርዓቷም ቀዳሚ ነው። ቻይና ሆስፒታሎችን ስትገነባ ዩናይትድ ስቴትስ በበኩሏ ባለሙያዎችን ማሰልጠን ትችላለች" ብለዋል ሙር።

በ2050 የአህጉሪቱ ሕዝብ ቁጥር በእጥፍ አድጎ 2.5 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህ ደግሞ በኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ ቁልፍ ነው።

በጥር ወር የተጀመረው የአፍሪካ ነፃ አህጉራዊ የንግድ ስምምነት (ኤኤፍሲቲኤ) ከዝቅተኛ ንግድ ጀምሮ በአፍሪካ አገራት መካከል የንግድ ትስስር እንደኖር የሚያደርግ ሲሆን እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካትም ቁልፍ መንገድ ተደርጎ ይወሰዳል።

ቻይና ቢአርአይ እና ኤኤፍሲቲኤን ለማገናኘት ያቀረበችው ሃሳብ "በአህጉሪቱ እና ከዚያም ውጪ ያለውን የንግድ ልውውጥ በእጅጉ ያሳድጋል" ይላሉ ማንጌኒ።

"በአፍሪካ ያለው የንግድ ዋጋ በዓለም ላይ ከፍተኛው ሲሆን ከሸቀጦች ዋጋ 90 በመቶው የማጓጓዣ ወጪው ነው። አንዳንዶቹ ቻይናን ቢተቹም በመሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስት ለማድረግ አልገቡም" ብለዋል ።

በአሜሪካ የዲሞክራሲ ጉባኤ ላይ ያልተጋበዙት የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ (ውሳኔውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ "ትልቅ ስህተት" ብሎ የገልጾታል) የቻይናን የግሉ ሴክተር መስፋፋት በደስታ ተቀብለው ምዕራባውያን የግል ባለሃብቶች "ፍላጎት እያጡ" ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ምርቶች ወደ ቻይና ገበያ እንዲገቡ ከሚገፋፉ መሪዎች መካከል ሙሴቬኒ አንዱ ናቸው። ቻይና የአፍሪካ አገራትን ለማጥመድ ብድር መስጠትን ትጠቀማለች ተብሎ በሰፊው ለሚወራው ነገር ግን ባልተረጋገጠው ውንጀላ የአገሪቱ ዋና አየር ማረፊያ ሊወሰድ ይችላል የሚለውን ዘገባ በቅርቡ ውድቅ አድርገዋል።

እነዚህ ፕሮጀክቶች ብዙ ጊዜ በሙስና በመዘፈቅ፣ እንቅፋት እና ግልጽነት የጎደላቸው በመሆናቸው አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ዕዳቸውን ለመክፈል እንዲንገዳገዱ አድርጓል።

ወደ ምራቅ ወይም ወደ ምዕራብ ሳይሆን ወደፊት

አንዳንድ ባለሙያዎች አህጉሪቱ በቻይና ላይ ያላት የጋራ ፖሊሲ አነስተኛ መሆን ስትራቴጅካዊ እቅዶቿን ይጎዳዋል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

በጆሃንስበርግ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ-ቻይና ጥናት ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ዴቪስ ሞንዬ "በአጠቃላይ ቻይና እንደ አፍሪካ የልማት አጋር ትልቅ ሚና ትጫወታለች። አፍሪካ ከቻይና ጋር ባላት ግንኙነት ግን የበለጠ ተሳታፊ እና የተቀናጀ መሆን አለባት" ሲሉ ጽፈዋል።

"ቻይና እአአ ከ2006 ጀምሮ ሦስት የአፍሪካ ፖሊሲዎችን ይፋ አድርጋለች። አፍሪካ ግን በቻይና ዙሪያ ፖሊሲ አላዘጋጀችም" ብለዋል።

ሃዋርድ ፍሬንች 'ቻይናስ ሰከንድ ኮንቲኔንት' በተሰኘ መጽሐፋቸው በዛምቢያ የቻይና አምባሳደር ከነበሩት የቀድሞ አምባሳደር ጋር በነበራቸው ውይይት በአፍሪካ የአሜሪካን ፖሊሲ ስለማፌዛቸው ያስታውሳሉ።

"እናንተ (አሜሪካ) የአገሪቱን ዜጎች ቀጥራችሁ በየምርጫ ጣቢያው ታዛቢ አድርጋችሁ ታስቀምጣላችሁ... ሌላ ምን አለ? መንገድ፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች ማንኛውንም ሰውን የመጠቅሙ እና ሕብረተሰቡን ለረዥም ጊዜ የሚያገለግል ነገር ስትሠሩ አላየሁም። ምናልባት የምርጫ ሰዎችን በማሰልጠን ትልቁ አስተዋፅ አድርጋችሁ ሊሆን ይችላል" ሲሉ በወቅቱ የዛምቢያ አምባሳደር የነበሩት ዡ ዩክሲያዮ ተናግረዋል።

እአአ በ2003 ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአህጉሪቱ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት አድን መድኃኒቶችን ያቀረበውን የአሜሪካ ኢመርጀንሲ ፕላን ፎረ ኤድስ ሪሊፍን (ፔፕፋር) በመጥቀስ ምላሽ እንደሰጡ ፍሬንች ጽፈዋል። .

አሜሪካ በአፍሪካ በተለይ በፀጥታ እና በጤና አገልግሎቶች ላይ ያላት ተሳትፎ ሰፊ ነው። የአፍሪካ ግሮወዝ ኤንደ ኦፖርቹኒቲ አክት (አጎዋ) ለአፍሪካ ምርቶች አትራፊ በሆነው የአሜሪካ ገበያ ዕድል ይሰጣል።

ነገር ግን የጋና የነጻነት መሪ ክዋሜ ንክሩማህ አህጉሪቱን "ወደ ምሥራቅም ወደ ምዕራብም ሳይሆን ወደፊት" መጓዝ እንዳሉት አፍሪካ በጋራ የራሷን መንገድ መፍጠር አለባት።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት አብዛኛዎቹ አፍሪካውያን በነጻ ዲሞክራሲያዊ አገሮች ውስጥ መኖር ይፈልጋሉ። ነገር ግን ጥሩ መንገዶችን፣ የተሻለ ትምህርት፣ ደኅንነት፣ ጤና እና ሌሎች ብዙ ፍላጎቶችን የሚያቀርቡ መንግሥታትን ይፈልጋሉ።

እነዚህን ፍላጎቶች ከግብ ለማድረስ የአፍሪካ መሪዎች የዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ውድድር ደጋፊ ከመሆን በሚቀርቡት እቅዶች በራስ ወዳድነት መሳተፍ አለባቸው ይላሉ ተንታኞች።