ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአንድ ስብሰባ 900 ሠራተኞቹን ከሥራ ያባረረው አሜሪካዊ አለቃ እየተወገዘ ነው
አንድ የአሜሪካ ኩባንያ አለቃ በአንድ ጊዜ 900 ሠራተኞቹን ከሥራ አባረረ፡፡ ድርጊቱ ውግዘትን አስከትሎበታል፡፡
ሚስተር ቪሻል ካርግ የተባለው የኩባንያው አለቃ 900 ሠራተኞቹን ከሥራ ያባረረው በዙም ስብሰባ ጠርቶ ነው፡፡
‹‹በዘህ ስብሰባ የተጠራችሁ በሙሉ እድለ ቢሶች ናችሁ፡፡ ምክንያቱም ከሥራ ተባራችኋል፡፡ ›› ሲል መርዶ ያረዳቸው ይህ ‹ክፉ› አለቃ በረዥም ጊዜ ብድር ቤት አቅራቢ (ሞርጌጅ) ሥራዎች ላይ የተሠማራው የቤተር ዶት ኮም ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ነው፡፡
ግለሰቡ ጨካኝና ርህራሄ ያልፈጠረበት ክፉ አለቃ ነው በሚል በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች እየተብጠለጠለ ይገኛል፡፡
በተለይም በዚህ በፈረንጆች አዲስ ዓመት ዋዜማ ይህንን ማድረጉ የጭካኔውን ጥግ የሚያሳይ ነው ያሉም አልጠፉም፡፡
ሚስተር ጋርግ ግን የሠራተኞች ምርታማነት ማሽቆልቆልና የገበያው መቀዛቀዝ አበሳጭቶት እዚህ ውሳኔ ላይ እንዳደረሰው አብራርቷል፡፡
የሚገርመው ይህ ኩባንያ ይህን ሁሉ ሠራተኛ ከማባረሩ ከአንድ ሳምንት በፊት 750 ሚሊዮን ዶላር ከባለሀብቶች ፈሰስ ተደርጎለት ነበር፡፡
ይህ ገንዘብ እንደተሰበሰበ ግን ይህ አለቃ ለሠራተኞቹ አልተናገረም፡፡
የቤተር ዶት ኮም የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ ኬቨን ራየን ለቢቢሲ እንደተናገረው ይህን ሁሉ ሠራተኛ በተለይም በዘመን መለወጫ በዚህ ሁኔታ ማባረር ቀላል እንዳልሆነ አብራርቶ ነገር ግን ለኩባንያው መቀጠል አስፈላጊ እርምጃ ነው፡፡
አለቃው ይህን እርምጃ ከወሰደ በኋላ ፎርቹን መጽሔት ባደረገው ምርመራ ይህ አለቃ ከዚህ ቀደም በብዕር ስም በጻፈው አንድ መጣጥፍ ሠራተኞቹን ‹‹ሌቦችና አጭበርባሪዎች›› በሚል ገልጾ ነበር፡፡
ሠራተኞችን እንዲህ ከፍ ዝቅ ያደረጋቸው 8 ሰዓት መሥራት ሲገባቸው ሁለት ሰዓት ብቻ እየሠሩ ነገር ግን ገንዘብ የሚቀበሉት ረዥም ሰዓት እንደሠሩ በማስመሰል ነው በሚል ነው፡፡
ይህ አለቃ ሠራተኞችን በማበሻቀጥ ዝናን ያተረፈ ነው፡፡
እሱ የሚያስተዳድረው ኩባንያ ለቤት ግዥ የረዥም ጊዜ ብድርን የተቀላጠፈና ዘመናዊ ለማድረግ ቴክኖሎጂን መጠቀም የተሻለ እንደሆነ እያመነ መጥቷል፡፡
ሚስተር ጋርግ ከዚህ ቀደም ለሠራተኞቹ በላከው አንድ የዲጂታል ጦማር እንዲህ ያለ መራር ወቀሳን አካቶ ነበር፡፡
‹‹እጅግ ቀርፋፋ ሠራተኞች ናችሁ.፡፡ ዱንዙዝና መፍዙዝና ፍዝ ናችሁ፡፡ በቃ ሁሉንም ነገር ተውት፡፡ አሳፍራችሁ ልትገድሉኝ ነው እንዴ!››