ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሃሳብን በመግለጽ ነጻነት ላይ ጫና ይኖረው ይሆን?
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባን የሚመለከቱ አንቀጾችን ይዞ ነበር ጥቅምት 23/2014 ዓ.ም ተግባራዊ የሆነው።
በዚህም ይህ በመላዋ አገሪቱ ለስድስት ወራት ተግባረዊ እንደሚሆን የተነገረው አዋጅ አንቀጽ 4 ንዑስ ቁጥር 10 ስለመገናኛ ብዙኃን እና ጋዜጠኞች የሚለው አለ።
የአዋጁ አስፈጻሚ አካል "በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሽብር ቡድኖች የሞራል ድጋፍ ያደርጋል ብሎ የሚያምነውን የመገናኛ ብዙኃን ወይም ጋዜጠኛ በሚመለከተው ባለሥልጣን እንዲታገድ ወይም ፈቃዱ እንዲሰረዝ ሊያዝ ይችላል" ሲል አዋጁ ይደነግጋል።
በመቀጠልም ቁጥር ስድስት ላይ በአዋጁ መሰረት ስለተከለከሉ ንግግሮች ያትታል።
"የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መምሪያ ዕዝ እንቅስቃሴ እና የአዋጁን አላማ የሚቃወም እና ለሽብር ቡድኖች አላማ መሳካት አስተዋጽኦ የሚያደርግ፣ የሽብር ቡድኖችን የሚያበረታታ፣ ሰላማዊ ዜጎችን የሚያሸብር ንግግር በማንኛውም መንገድ ማድረግ ወይም ማሰራጨት የተከለከለ ነው" በማለት።
ይህም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ የተቀመጠው ገደብ ከመገናኛ ብዙኃን ባለፈ መደበኛ ዜጎችንም የሚመለከት መሆኑን ያስረዳል።
በእርግጥ በዚህ የዲጂታል ዘመን በተለይም የማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች የዜጋ ጋዜጠኝነት በሚባለው አዲስ እውነታ ውስጥ መረጃ ከመቀበል አልፎ ማሰራጨትም አስችሏቸዋል።
ታዲያ ይህንን ሚሊዮኖች የሚሳተፉበትን የዜጋ ጋዜጠኝነት ልክ እንደ ተለመዱት መደበኛ የመገናኛ ብዙኃን ሁሉ በሕግ ቁጥጥር ስር ማድረግ ይቻላል ወይ? ስንል የሕገ መንግስት ምሁሩን አደም ካሴን (ዶ/ር) ጠይቀናቸዋል።
አደም አንደሚሉት ሕግ ሲወጣ ሁሉንም ተግባራት በሙሉ ለመቆጣጠር ይቻላል ከሚል እሳቤ እንዳልሆነ እና በርግጥም በዲጂታሉ ዘመን እንዲህ ያለ ቁጥጥር ማድረግ ሙሉ በሙሉ የሚሳካ እንዳልሆነ ይናገራሉ።
ነገር ግን የተወሰኑ በመጠናቸው ከፍ ያለ እና የሚታይ ጉዳት ያመጣሉ ተብለው የሚታሰቡ ተግባራትን ለመቆጣጠር ለማስቻል ሕጎች እንደሚወጡም ያስረዳሉ።
"ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በዓለም አቀፍ ደረጃም ገደብ ሊጣልባቸው ከሚችሉ መብቶች መካከል አንዱ ነው። ስለዚህ መገደቡ አዲስ ነገር አይደለም" የሚሉት አደም ይህ ገደብ ሲፈጸም የሚፈጠሩ ቅሬታዎችን በአግባቡ የሚያስተናግድ የሕግ ሥርዓት ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው" ይላሉ።
በአዋጁ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እስኪጠናቀቅ ድረስ የትኛውም የዳኝነት አካል ሥልጣን እንደማይኖረው ተደንግጓል።
አደም እንደሚሉት በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች በሌሎች ላይ የሚፈጥሩት ፍርሃት ቀላል የሚባል አይለም። እንዲህ ያለ ፍርሃት "የሚዲያ ባለሞያዎች ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ እና ገና ለገና ያስቀጣኝ ይሆናል በሚል ራሳቸውን መቆጠባቸው በተለይም ኅብረተሰቡ ማግኘት የሚገባውን መረጃ ለመስጠት እንዳይችሉ ያደርጋል" ይላሉ።
ትግበራው እና አዋጁ የፈጠራቸው ስጋቶች
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ማኅበር ፀሐፊ የሆነው ሲሳይ ሳህሉ በተወሰነ መንገድ አደም የገለጿቸው አይነት ስጋቶች በመገናኛ ብዙኃን ዘንድ እየተፈጠሩ መሆኑን እና ይህም በተለይ አዋጁን በሚያስፈጽሙ አካላት ዘንድ የአፈጻጸም ወጥነት ያለመኖሩን ተከትሎ የመጣ ነው ሲል ያስረዳል።
"አገር አደጋ ላይ መሆኑን እንረዳለን። ነገር ግን ሕጉ ጋዜጠኞች ለኅብረተሰቡ ተገቢውን መረጃ የማቅረብ ሥራቸውን ማከናወን አለባቸው" የሚለው ሲሳይ፣ በግሉ አበዲስ አበባ ውሰጥ ለዘገባ በወጣበት ከሌሎች ባልደረቦቹ ጋር ለሁለት ሰዓታት ያህል በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ መቆየቱን ይናገራል።
"ባጅ አምጡ ነበር የሚሉት። መታወቂያ ስናሳያቸው 'አይ በዚህ ሰዓት ያለባጅ መስራት አይቻልም' ነበር የሚሉት። ይህ ጋዜጠኛው ተስፋ እንዲቆርጥ ያደርገዋል" ሲል ሲሳይ ይናገራል። ይህም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ያልተደነገገ ነገር ጭምር እንደሚጠይቁ እና የአረዳድ ችግሮች እንዳሉ ይናገራል።
በእርግጥ ሲሳይ ማኅበሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በራሱ ችግር አለበት ብሎ እንደማያምን እና ዋናው የአፈጻጸም ችግር መሆኑን ይናገራል።
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ የሰሃራ በታች ወኪል ሙቱኪ ሙሞ ግን በእዚህ አይስማሙም። አዋጁ እንዲሁም እርሱን ተከትሎ ከአስፈጻሚ ዕዙ የወጣው መግለጫ መሰረታዊ ችግሮች እንዳሉባቸው ያስረዳሉ።
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ በተለይም ለባለሥጣናት ያለ ገደብ ሰዎችን እንዲያስሩ ሥልጣን መስጠቱ እና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ "ለሽብር ቡድኖች" የሞራል ድጋፍ ያደርጋሉ ተብለው በታመኑ የሚዲያ ተቋማት ላይ ፈቃድን እስከመሰረዝ የሚያደርስ እርምጃ እንዲወስድ የሚያዙት ከመገናኛ ብዙኃን ነጻነት አንጻር አሳሳቢ መሆኑን ሲፒጄ እንደሚያምን ይናገራሉ።
በቅርቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጽም የሚከታተለው ዕዝ ባወጣው ትዕዛዝ ላይ ጦርነቱን የተመለከቱ ዘገባዎች ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ካልመጣ በስተቀር መዘገብን አግዷል ብለው እንደሚያምኑም ጨምረው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እነዚህ ድንጋጌዎች ለትርጉም የተጋለጡ እና ግልጽ ያልሆኑ መሆናቸው ሌላው አሳሳቢ ነገር መሆኑን ሙቱኪ አክለዋል። በተለይም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶችን የሚገድቡ ሕጎች ሲወጡ ሕጉ የሚመለከታቸው ሰዎች ባሕሪያቸውን ከሕጉ አንጻር ማስተካከል ይችሉ ዘንድ ግልጽ መሆን አለባቸው ሲሉም ወኪሏ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ለምሳሌ በተዘዋዋሪ የሞራል ድጋፍ ማድረግ ማለት ምን ማለት ነው? የፀጸጥታ ኃይሎች እርምጃ ውሰዱ ሲባል ምን ማለት ነው? እሰሩ ማለት ነው? ወይስ የጋዜጠኞችን መሳሪያዎች ውረሱ ማለት ነው? ወይስ ፈቃድ ሰርዙ ማለት ነው? ይህ በግልጽ አልተቀመጠም። በቀጣይ የወጣውም መግለጫ መንግሥት የሚዲያ ክልከላ አይደለም ቢልም በርግጥም ዘገባን የሚያግድ ነው" ሲሉ የሲፒጄዋ ሙቱኪ ተናግረዋል።
እዚህ ጋር ስጋቱ የሚመነጨው የሰዎች መሠረታዊ መብቶች እንዲጣሱ በር ይከፍታል ከሚል የመነጨ እንደሆነም ይናገራሉ።
"እነዚህ በጣም የተለጠጡ ሥልጣኖች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ የተቀመጡ መሆናቸውን ግን መርሳት የለብንም" ያሉት ሙቱኪ ሰዎችን ስለተጠረጠሩ ብቻ ምርመራ ማድረግ ሳያስፈልግ ገደብ ለሌለው ጊዜ ያለ ፍርድ ቤት ፈቃድ ማሰርን አዋጁ መፍቀዱን በማከል።
የጋዜጠኞች ማኅበሩ ፀሐፊው ሲሳይ እንደሚለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተክትሎ የመረጃ ፍሰት ላይ እንቅፋት መፈጠሩን እና ይህም "ከአንድ የመንግሥት አካል ወደ ሌላ የመንግሥት ሚዲያ" እንዲፈስ አድርጓል ሲል ይናገራል።
ይህም በተለይም የግል የመገናኛ ብዙኃን ላይ ጫና ማድረጉን እና የመንግሥት አካላት መረጃ ለመስጠት መሸሻቸውን ጠቅሶ፣ ይህም ለሕዝቡ የተፈለገውን ጥራት ያለውን ዘገባ ለመስጠት አስቸጋሪ ማድረጉንም እዚሁ ላይ ይጠቅሳል።
የጋዜጠኞች ደኅንነት ለመጠበቅ
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ማኅበር ፀሐፊው ሲሳይ እንደሚለው ማኅበራቸው ገና አዲስ መሆኑን ተከትሎ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የጋዜጠኞችን መብት ለማስጠበቅ ያደረጉት ጥረቶች ጥቂት መሆናቸውን ይናገራል።
በተለይም ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር በሚውሉበት ጊዜ የተለያዩ መግለጫዎችን በማውጣት ጫና ለመፍጠር እንደሚሞክሩ እና ይህም ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር በመተባበር የሚደረግ እንደሆነ ይናገራል።
ሲሳይ ማኅበራቸው አስካሁን ያከናወነው ተግባር አጥጋቢ የሚባል እንዳልሆነ በመገለጽ፣ በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ጋዜጠኞች ያለ አግባብ እስር እንዳይደርስባቸው በየጊዜው ውይይቶችን እንደሚያደርጉ ተናግሯል።
ሙቶኪ የጋዜጠኞችን ደኅንነት የመጠበቅ ትልቁ ኃላፊነት መንግሥት ላይ ቢወድቅም የመገናኛ ብዙኃን በእንዲህ አይነት ወቅቶች የሠራተኞቻቸውን ደኅንነት የመጠበቅ ከፍተኛው ኃላፊነት እንዳለባቸው ይናገራሉ።
ጋዜጠኞችም ኃላፊነት እንዳለባቸው መዘንጋት እንደሌለበት የሚገልጹት የሲፒጄዋ ሙቱኪ፣ የሚሰጣቸው ሥራ አደገኛ መሆኑን በመለየት የመሥራት ፍላጎት እንደሌላቸው ለመናገር ሁል ጊዜ ድፍረቱ ላይኖራቸው እንደሚችልም ያክላሉ።
ስለዚህም የዜና ክፍሎች ጋዜጠኞች አንድን ዘገባ ከመጀመራቸው በፊት የጋዜጠኞችን ደኅንነት ማስቀደም እንዳለባቸውም ያብራራሉ።
"ነገር ግን ጋዜጠኞች ከሲፒጄም ሆነ ከሌሎች መሰል ድርጅቶች እርዳታ ካስፈለጋቸው በቀጥታ ሊያነጋግሩን ይችላሉ" ሲሉም የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ ወኪል ለቢቢሲ ተናግረዋል።