ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባልተለመደ ሁኔታ ከቻይና እስር ቤት አምልጦ የነበረው ሰሜን ኮሪያዊ ተያዘ
ከቻይና እስር ቤት አምልጦ የነበረው ሰሜን ኮሪያዊ ከ40 ቀናት ፍለጋ በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋለ።
በቻይና መገናኛ ብዙሃን ዡ ዢያንጂን በሚል ስም የሚጠራው የ39 ዓመት ሰሜን ኮሪያዊ፤ ባልተለመደ ሁኔታ ከቻይና እስር ቤት ማምለጥ ችሎ ነበር።
ዡ እአአ 2013 ከሰሜን ኮሪያ ሸሽቶ ቻይና ከገባ በኋላ ፈጽሟቸዋል በተባለው ወንጀል በእስራት እንዲቀጣ ተበይኖበት ነበር።
ከእስር ያመለጠውን ሰሜን ኮሪያዊ መልሶ ለመያዘ የቻይና ፖሊስ መጠነ ሰፊ ክትትል ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ፍርደኛው ያለበትን ለጠቆመም የገንዘብ ሽልማት እንደሚሰጥ ባለሥልጣናት አስታውቀው ነበር።
መንግሥታዊው ቤጂንግ ኒውስ ሰሜን ኮሪያዊው ጥቅምት 9 ከእስር ሲያመልጥ ነው ብሎ ባሳየው ምስል ላይ፤ ዡ በእስር ቤት አጥር ላይ ተንጠላጥሎ ጣራ ላይ ሲወጣ ታይቷል።
ተንቀሳቃሽ ምስሉ የእስር ቤቱ ጥበቆች እስረኛውን ለመያዝ ሲጣጣሩ አሳይቷል።
የዡ ከእስር ማምለጥ የቻይናውያን መነጋገሪ ሆኖ ነበር። ባለሥልጣናት ዡ ያለበትን ለጠቆመ እስከ 100 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንሸልማለን ብለው ነበር።
ዡ ከዚህ ቀደም በቻይና እስር የተፈረደበት ወደ ቻይና በሕገ ወጥ መንገድ በመግባት፣ በዝርፊያ እና ሌብነት ነበር።
የፍርድ ቤት ሰነዶች እንዳመለከቱት፤ ዡ እአአ 2013 ላይ ቻይና እና ሰሜን ኮሪያን የሚያዋስን ወንዝ ተሻግሮ ወደ ቻይና ከገባ በኋላ በአቅራቢያው ከሚገኙ መንደሮች ገንዘብ፣ አልባሳት እና ሞባይል ስልኮችን ዘርፏል።
ከዚህ በተጨማሪም ዡ ሲሰርቅ የተመለከቱትን ሴት አዛውንት በስለት ወግቶ ለማምለጥ ሲል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋሉን የፍርድ ቤት ሰነዶች አመልክተዋል።
ዡ ከእስር ቤት ሲያመልጥ ከተላለፈበት ፍርድ 9 ዓመት አጠናቆ ሁለት ዓመታት የእስር ጊዜ ብቻ ቀርተውት ነበር። ይሁን እንጂ ከእስሩ መጠናቀቅ በኋላ ዡ ወደ ሰሜን ኮሪያ ተላልፎ ስለሚሰጥ ወደ ትውልድ አገሩ ላለመመለስ ከእስር ለማምለጥ ስለመወሰኑ በርካቶች ግምታቸውን እየሰጡ ነው።
ቻይና የእአአ 1951 የተመድ የስደተኞች ስምምነት ፈራሚ ብትሆንም፤ ስደተኞችን ወደ ሰሜን ኮሪያ በኃይል ትመልሳለች።
በተመድ ስምምነት መሠረት ሰዎች ወደ ትውልድ አገራቸው መመለሳቸው መሠረት ለሌለው ክስ እና ስቃይ የሚዳርጋቸው ከሆነ ፈራሚ አገራት ሰዎችን ወደ ትውልድ አገራት አሳልፈው እንዳይሰጡ ይከለክላል።
ቻይና ግን ሰሜን ኮሪያዊያንን የተሻለ ሕይወት ፈልገው ከአገራቸው የሚሸሹ ሕገ ወጥ ስደተኞች አድርጋ እንጂ የደህንነት ስጋት ያለባቸው ስደተኛ አድርጋ አትመለከታቸውም።