ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአዲሱ ቫይረስ ምክንያት በደቡብ አፍሪካ ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳ እንዲነሳ ፕሬዝዳንቱ ጠየቁ
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ኦሚክሮን በተሰኘው አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ምክንያት በአገራቸው እና ጎረቤቶቻቸው ላይ የተጣለውን የጉዞ እገዳ ተቃመው።
ፕሬዝዳንቱ በተወሰደው እርምጃ "በጣም አዝኛለሁ" ሲሉ ቅሬታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ውሳኔውንም ምክንያታዊ ያልሆነ ብለውታል። አክለውም የጉዞ እገዳው በፍጥነት እንዲነሳ ጠይቀዋል።
ኦሚክሮን የተባለው የኮቪድ አዲስ ዝርያ በደቡባዊ አፍሪካ አገራት መገኘቱ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ በአካባቢው አገራት ላይ የጉዞ እገዳ ከጣሉት መካከል ዩናይትድ ኪንግደም፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ አሜሪካ እና ካናዳ ተጠቃሽ ናቸው።
አዲሱ ኦሚክሮን የተሰኘው የኮሮናቫይረስ አይነት አሳሳቢ የሚባሉ የኮቪድ ዝርያዎች ምድብ ውስጥ የገባ ሲሆን ከሰው ወደ ሰው የመታላለፍ እድሉም ከፍተኛ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል።
በደቡብ አፍሪካ እና በሌሎችም አገራት በስፋት የተገኘው አዲሱ ቫይረስ፤ በያዝነው ወር መጀመሪያ አካባቢ በደቡብ አፍሪካ መታየቱን ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ ዕለት የዓለም ጤና ድርጅት ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
በደቡብ አፍሪካ በሕዝብ ብዛት አንደኛ በሆነችው ጋውቴንግ ግዛት በኮሮናቫይረስ ከተያዙ ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ በዚህ አዲስ ቫይረስ መጠቃታቸው ተገልጿል። ይህ የሆነው ባለፉት ሁለት ሳምንታት ሲሆን አሁን ላይ ግን በሁሉም የአገሪቱ ግዛቶች ተስፋፍቷል።
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ አገራት ቸኩለው የጉዞ እገዳ ከማድረግ እንዲቆጠቡና ያለውን ስጋት ከግምት ውስጥ ያስገቡ እንዲሁም ሳይንሳዊ መንገድን በተከተለ መልኩ ውሳኔ እንዲያስተላልፉ ጠይቋል። ነገር ግን በርካታ አገራት የጉዞ እገዳ እና ሌሎች እርምጃዎችን መውሰዳቸውን እያጠናከሩ ይገኛሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ማትሂዲሶ ሞዌቲ እሁድ ዕለት ሲናገሩ "ምንም እንኳን ይህ አዲሱ ኦሚክሮን በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች ቢስተዋልም አፍሪካ ላይ የጉዞ እገዳ መጣል ዓለም አቀፍ ወንድማማችነታችንን የሚያውክ ነው'' ብለዋል።
ዳይሬክተሩ በንግግራቸው የጉዞ እገዳው ሳይንሳዊ የሆነ መሠረት ያለውም ያሉ ሲሆን አክለውም በተለይ ደቡባዊ አፍሪካ ተገቢ ባልሆነ መልኩ መገለል እየደረሰበት እንደሆነ ገልጸዋል።
የጉዞ እገዳዎቹ የቫይረሱን ስርጭት በትክክል ለመቆጣጠር እንደማይረዱም አሳስበዋል።
"የጉዞ እገዳዎቹ ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጫና ከማሳደራቸው በተጨማሪ አገራቱ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የሚገታ ነው'' ብለዋል።
ይህንን እንደ ምክንያት በማቅረብም የአፍሪካ ዳይሬክተሩ የጉዞ እገዳ ያደረጉ አገራት በፍጥነት ውሳኔያቸውን እንዲቀለብሱና የአገራት ኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰውን ጫና እንዲያስቆሙ ጠይቀዋል።
ኦሚክሮን ከደቡባዊ አፍሪካ በተጨማሪ እስካሁን በዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያ እና እስራኤል መገኘቱ ተረጋግጧል።
ኔዘርላንድስ ውስጥ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ ወደ መዲናዋ አምስተርዳም የተጓዙ 13 ሰዎች አዲሱ ቫይረስ እንዳለባቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ የአገሪቱ ፖሊስ ደግሞ ከለይቶ ማቆያ ያመለጡ ጥንዶችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
እሁድ ዕለት እስራኤል ከሌሎች አገራት የሚመጡ ሁሉም ተጓዦች ወደ ድንበሯ መግባት እንደማይችሉ አስታውቃለች።