ኮሮናቫይረስ፡ ደቡብ አፍሪካ አዲሱን የኮቪድ ዝርያ በማግኘቷ 'እየተቀጣሁ' ነው አለች

ደቡብ አፍሪካ አሚክሮን የሚል ስያሜ የተሰጠውን አዲሱን የኮቪድ ዝርያ በማግኘቷ ከምስጋና ይልቅ እየተቀጣሁ ነው በማለት ቅሬታ አቅርባለች።

የአገሪቱ የወውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንን መግለጫ ያወጣው በአለም ዙሪያ ያሉ አገራት ከደቡብ አፍሪካ የሚደረገውን ጉዞ በማገዳቸውና አንዳንዶቹም በሂደት ላይ መሆናቸውን ተከትሎ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ የጉዞ እገዳውን አጥብቆ ተችቷል።

አክሎም "ምርጥ ሳይንስ ሊደነቅ እንጂ ሊቀጣ አይገባም" ብሏል።

እገዳዎቹ "ደቡብ አፍሪካ ለላቀ ምርመራዋና አዳዲስ ዝርያዎችን በፍጥነት መለየት መቻሏ ከመቅጣት ጋር ተመሳሳይ ነው" በማለት ተቃውሟል።

መግለጫው አክሎም በዓለም ላይ ከዚህ ቀደም አዳዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች ሲገኙ ምላሹ ፍጹም የተለየ ነበር ሲልም ወቅሷል።

በአሁኑ ሰዓት ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት አሚክሮን በፍጥነት የሚስፋፋና እንደገና የመያዝ አደጋውም ከፍተኛ ነው ተብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት በያዝነው ሳምንት አርብ ዕለት እንዳስታወቀው አዲሱ ዝርያ "አሳሳቢ ነው" ብሏል።

በአሁኑ ሰዓት በአዲሱ ዝርያ የተያዙ በርካታ ሰዎችም በአውሮፓ ተገኝተዋል።

ከነዚህም መካከል ሁለቱ በእንግሊዝ ፣ ሁለት በጀርመን ፣ አንድ በቤልጂየም እና አንድ በጣሊያን እንዲሁም አንድ ተጠርጣሪ በቼክ ሪፖብሊክ ውስጥ መገኘታቸው ተገልጿል።

አዲሱ ዝርያ መገኘቱ የተረጋገጠባት እስራኤል ከቅዳሜ እኩለ ሌሊት ጀምሮ ሁሉም የውጭ ዜጎች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ ለማገድ ወስናለች።

እንደ እስራኤል ታይምስ ዘገባ ከሆነ ይህ የገደብ እርምጃ ለ14 ቀናት ይቆያል።

ኦሚክሮን ከነዚህ አገራት በተጨማሪ በቦትስዋናና በሆንክ ኮንግም ተገኝቷል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከደቡብ አፍሪካ ወደ ኔዘርላንድ የመጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች ላይ አዲሱ ዝርያን መኖሩን ለመለየት ምርመራ እየተካሄደ ይገኛል።

በሁለት የኬኤልኤም በረራዎች ላይ 61 መንገደኞች በኮቪድ-19 ተይዘው የተገኙ ሲሆን በአምስተርዳም ስኪሆል አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ ተገልለው ተጨማሪ ምርመራዎች ሲያደርጉ መቆየታቸውን የኔዘርላንድ ባለስልጣናት ተናግረዋል ።

ኔዘርላንድስ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ካገረሸው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር እየታገለች ትገኛለች። በዛሬው ዕለትም አገሪቱ መለስተኛ የእንቅስቃሴ ገደብ ጥላለች።

አዲሱ የኦሚክሮን ዝርያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከደቡብ አፍሪካ ለአለም ጤና ድርጅት ሪፖርት የተደረገው በያዝነው ሳምንት ህዳር 15፣ 2014 ዓ.ም ነው።