በአዲሱን የኮቪድ ቫይረስ ምክንያት አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት በደቡባዊ አፍሪካ አገራት ላይ የጉዞ እገድ ጣሉ

አዲስ የኮሮናቫይረስ በደቡባ አፍሪካ አገራት መገኘቱን ተከትሎ አሜሪካ፣ ካናዳ እና የአውሮፓ ሕብረት ከደቡባዊ አፍሪካ አገራት በሚደረጉ በራራዎች ላይ ክልከላዎችን ጣሉ።

ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ አሜሪካ ከደቡብ አፍሪካ እና ከሌሎች 7 የደቡባዊ አፍሪካ አገራት የሚደረጉ በራራዎች ላይ ክልከላዎችን አስተላልፋለች።

የአሜሪካ ባለስሥጣናት ከሰኞ ጀምሮ ከደቡብ አፍሪካ፣ ቦትስዋና፣ ዚምባብዌ፣ ናሚቢያ፣ ኢስዋቲኒ፣ ሞዛምቢክ እና ማላዊ ወደ አሜሪካ መብረር የሚችሉት አሜሪካውያን እና የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው ብቻ ናቸው ብለዋል።

ይህ የአሜሪካ ውሳኔ የተሰማው የአውሮፓ ሕብረት እና ዩናይትድ ኪንግደም በተጠቀሱት አገራት ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ከወሰዱ በኋላ ነው።

በተመሳሳይ ሰሜን አሜሪካዊቷ አገር ካናዳም ተመሳሳይ እርምጃ ትወስዳለች ተብሏል።

የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይንደ ስለ አዲሱ ቫይረስ ዝርዝር መረጃዎች እስኪታወቁ ድረስ ይህን ጊዜያዊ እርምጃ ለመውሰድ ተገደናል ብለዋል።

ቀደም ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አዲሱ የኮቪድ ዝርያ 'አደገኛ' ሲል የፈረጀው ሲሆን 'ኦሚክሮን' የሚል መጠሪያም ሰጥቶታል።

ይህ በአይነቱ የተለየው የኮሮናቫይረስ ዝርያ፤ በመዛመት ፍጥነቱ ከሌሎቹ የከፋ ነው ተብሏል።

በዚህ ዝርያ ተይዘው የተገኙ 59 ሰዎች ብቻ ሲሆኑ እነሱም በደቡብ አፍሪካ፣ በሆንግ ኮንግና በቦትስዋና ውስጥ ነው ሪፖርት የተደረጉት።

ዘግየት ብሎም ይህ አዲስ የኮቪድ ዝርያ በእስራኤል ውስጥ መገኘቱ ሪፖርት ተደርጓል።

ኦሚክሮን ተብሎ ስለተጠራው አዲስ ዝርያ እስካሁን የምናውቀው

ኦሚክሮን እስካሁን ከታዩ የኮሮናቫይረስ አይነቶች እጅግ የተለየው ነው ተብሏል።

በበርካታ የዘረመል ለውጥ ውስጥ በማለፉ በአንድ ሳይንቲስት "አሰቃቂ" ተብሎ ሲገለጽ ሌላው ደግሞ እስካሁን ከታዩት "የከፋ" ዝርያ ነው ብለዋል።

አዲሱ ዝርያ በምን ያህል በፍጥነት እንደሚሰራጭ እና ክትባቶችን በመቋቋም አቅሙ ዙሪያ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ።

ይህ የዝርያ ለውጥ ቫይረሱን ማሸነፍ ካልቻለ አንድ ታካሚ የመጣ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል።

አሳሳቢው ነገር ይህ ቫይረስ በቻይና ዉሃን ከተፈጠረው የመጀመሪያው ቫይረስ በእጅጉ የተለየ ነው።

ይህም ማለት የመጀመሪያውን ቫይረስ ከግምት በማስገባት የተመረቱት ክትባቶች ለዚህ አዲስ ዝርያ ያን ያክህ ውጤታማ ላይሆኑ ይችላሉ።

በደቡብ አፍሪካ የኩዋዙሉ-ናታል ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ሌሰልስ "ይህ ቫይረስ የመሰራጨት ችሎታውን ከፍ አድርጎ ከሰው ወደ ሰው ከመተላለፍ ባለፈ የበሽታ ተከላካይ ክፍሎችን ማካለል ይችላል የሚል ስጋት አሳድሮብናል" ብለዋል።