በአፍጋኒስታን የበረታው ረሃብ እናት ልጇን በአምስት መቶ ዶላር እንድትሸጥ አደረገ

ታሊባኖች በ20 ዓመታት የሽምቅ ውጊያ አሜሪካኖችን ረፍት ነስተው አፍጋኒስታንን ለቀው ከወጡ ከሁለት ወራት በኋላ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ተሽመድምዷል ረሃብ ስር ሰዶ አገሬው ከረሃብ ማምለጫ መላ እየፈለገ ነው።

በዚህም ሳቢያ ረሃብ ወላጅ የገዛ ልጁን ወደ ገበያ አውጥቶ አስከመሸጥ አድርሷል። የማይታመን፣ ግን እየሆነ ያለ ሐቅ ነው። በአፍጋን ምድር ልጆች እንደ እንቁላል በገበያ መሸጥ ጀምረዋል።

ይህ መዓት እንዴት ሊከሰት ቻለ?

ከ20 ዓመታት በፊት በአሜሪካ ወረራ ከሥልጣናቸው ተፈንግለው ወደ ሸማቂነት የተቀየሩት ታሊባኖች ያልተቋረጠ ጦርነት ውስጥ ቆይተው በድል ወደ ካቡል ተመለሱ።

ምዕራባውያኑ አሸባሪ ባሉት ታሊባን የተራዘመ የሽምቅ ዘመቻ የሳቡትን ሳያሳኩ ተሸንፈው ወጡ። አፍጋኒስታናዊያን ግን ወደ ከፋ ቅጣት የተሸጋገሩት እንጂ ነጻነት አልተቀዳጁም።

የምዕራብ አገራት ለመንግሥቱ ይሰጡት የነበረውን ሰብአዊ እርዳታ ጭምር በማቆማቸው አፍጋናዊያን የዳቦ ያለህ እያሉ ነው።

ከሁሉ አንጀት የሚበሉት ግን የአፍጋን እናቶች ናቸው። ልጇን ለመሸጥ የቆረጠች እናት ምንኛ ተስፋ ብትቆርጥ ነው?

የቢቢሲ ዘጋቢ ዮጊታ ሊማይ ወደ አፍጋኒስታን ተጉዛ ነበር። በሔራት ከተማ የሚገኘውን የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን ሆስፒታልን ስትጎበኝ ልብ የሚሰብሩ ታሪኮችን ሰማች።

በሆስፒታሉ የሕጻናት ክፍል የተኙ ሕጻናት ሥጋቸው አልቆ በአንጥንታቸው ናቸው። የሚላስ የሚቀመስ የላቸውም። በዕድሜያቸው መመዘን ካለባቸው ኪሎ ግማሽ እንኳ አይሞሉም። ከአምስቱ አንዱ ሕይወታቸው በረሃብ ያልፋል።

ረሃብ ጊዜ ይሰጣል? አይሰጥም። ስለዚህ አንድ ነገር መደረግ አለበት።

እናቶች የአብራካቸው ክፋይ መንምኖ ሲሞት እያዩ ያነባሉ። ደረቅ እንባ። መራር እንባ። በረሃብ ከመሞት ልጅን ሽጦ መሰንበት ሌላው አማራጭ ነው።

ሕጻን ኡስማን በረሃብ መንምኖ አልቋል። መንታው በሌላኛው ክፍል ረሃብ አስተኝቶት ያቃስታል። እናቱ ስሜቷን ለመግለጽ ቃል አጥታለች።

"የልጄ እያንዳንዷን ሕመም እየታመምኳት ነው። ትሰማኛለች። ልጄን ሳየው የሚሰማኝን የውስጥ ሕመም ፈጣሪ እንጂ ሌላ ሊያውቀው አይችልም። ሁለት ልጆቼ በሚቀጥሉት ደቂቃዎች ሊሞቱ ይችላሉ። ምክንያቱም የሚበሉት የለም። ገንዘብ የለንም። የዓለም ሕዝብ አፍጋኒሰታንን ሊረዳ ይገባል። የትኛዋም እናት እኔ እያለፍኩበትን ያለውን ስቃይ እንዳታልፍበት አልሻም።"

በአፍጋኒስታን የጤና መዋቅሩ እየተፍረከረከ ነው። ሆስፒታሎች በታማሚዎች ተሞልተዋል። ሆኖም በቂ መድኃኒት የለም፣ በቂ ሐኪምም መሣሪያም የለም። ሆስፒታሎች ስማቸውን ታቅፈው ቀርተዋል። በደረቅ አልጋቸው ላይ እንደ አጥንት የደረቁ ሕጻናት ተኝተዋል።

በአፍጋኒስታን ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል የጤና መሠረተ ልማት ይደገፍ የነበረው በውጭ እርዳታ ነበር። አሁን ግን እርዳታው ቀረ። ለምን ቀረ?

የምዕራብ መንግሥታት ለታሊባን እውቅና እንስጠው ወይስ አንስጠው እያሉ እየተወዛገቡ ነው። በዚህ የተነሳ አንድም ሐኪም ባለፉት አራት ወራት ደመወዝ ተከፈለኝ የሚል የለም።

ይህ ሁሉ ተደማምሮ አፍጋናዊያን የገዛ አገራቸው ምድራዊ ገሐነም ሆናባቸዋለች። በሰው ልጅ ይሆናል ተብሎ የማይገመተውን ለማድረግም ተገደዋል።

እናት የገዛ ልጇን እንደ ሽንኩርትና ቲማቲም ገበያ ወስዳ መሸጥ። ከሔራት ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ከተማ በእርግጥም ይህ እየሆነ ነው።

አንዲት ሕጻን በ500 ዶላር ተሸጠች። የገዛ እናቷ ናት ይህን ያደረገችው። ምን አማራጭ ነበራት?

"ሌሎች ልጆቼ በረሃብ ሊሞቱብኝ ሆነ። አንዷን ልጄን ሸጥኩ። እንዴት ነው የማላዝነው? እንዴት ነው ልቤ የማይደዋው። ልጄን እኮ ነው የሸጥኩት።"

ለመሆኑ ይህ 500 መቶ ዶላሩ ሌላውን ቤተሰብ ለስንት ቀናት በሕይወት ያቆይ ይሆን?

እናት እርግጠኛ አይደለችም። ልጇን የገዛት ሰውዬም ቢሆን ሙሉ ክፍያ አልፈጸመም። 250 ዶላር ቀብድ ብቻ ነው የከፈለው።