በአፍጋኒስታን የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑ ሴቶች "አርፋችሁ ቤት ተቀመጡ" ተባሉ

የታሊባን አዲሱ የካቡል ከንቲባ በከተማዋ የሚገኙ የማዘጋጃ ቤት ሴት ሠራተኞችን 'አርፋችሁ ቤት ተቀመጡ' ሲሉ ተናገሩ።

ከንቲባው ሐምዱላህ ኖማኒ ይህን ያሉት ታሊባን ለጊዜው ሴቶች ሥራ እንዳይሠሩ ማዘዙን በመጥቀስ ነው።

"ክፍት የሥራ መደቦች በወንዶች የማይሞሉ ከሆነ ብቻ ለሥራ ልትመጡ ትችላላችሁ፤ አለበለዚያ ግን አርፋችሁ ቤት ተቀመጡ" ብለዋል ከንቲባው።

ታሊባን በ1990ዎቹ መጀመሪያ በአፍጋኒሰታን ሥልጣን በያዘ ጊዜ ተመሳሳይ ዕቀባን በሴቶች ላይ ጥሎ ነበር።

ሆኖም የአሜሪካንን ከአገሪቱ መውጣት ተከትሎ ሥልጣን ከ20 ዓመታት በኋላ የተቆናጠጡት ታሊባኖች የሴቶችን መብት በሸሪዓ ማዕቀፍ ውስጥ እስከሆኑ ድረስ እንደሚያከብሩ ለዓለም ቃል ገብተው ነበር።

ሆኖም ታሊባን ከዚያ ይልቅ ጥብቅ የሸሪዓ አስተዳደርን የመረጠ ይመስላል።

ታሊባኖች ሥልጣን ከያዙበት ዕለት ጀምሮ ሥራ የነበራቸው ሴቶች በሙሉ የአገሪቱ የደኅንነት ሁኔታ እስኪሻሻል ድረስ ቤት እንዲቀመጡ አዟል።

ሕጉን በመቃወ ሰልፍ በወጡ ሴቶች ላይም ድብደባ ፈጽሟል።

ታሊባን የሴቶች ጉዳይ ሚኒስትርን ያፈረሰ ሲሆን በምትኩ ሐይማኖታዊ ደንቦች መከበራቸውን የሚቆጣጠር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አቋቁሟል።

በዚህ ሳምንት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተከፈቱ ቢሆንም ወንድ ተማሪዎች እና ወንድ አስተማሪዎች ብቻ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ነው የተነገራቸው። ሴት ተማሪዎቸና አስተማሪዎች ግን ለጊዜው ቤት እንዲቆዩ ተደርጓል።

ታሊባን እንደሚለው ለሴቶች የተለየ ትምህርት ቤቶችን እያዘጋጀ ነው።

የካቡል አዲሱ ከንቲባ እንዳሉት በከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ሠራተኞች ውስጥ አንድ ሦስተኛው ሴቶች ነበሩ።

ይህም በቁጥር ወደ አንድ ሺህ ይጠጋሉ። እነዚህ በሙሉ ቤት እንዲቀመጡ ተነግሯቸዋል።

ሆኖም ከንቲባ እንዳሉት አንዳንድ ሴቶች ግን ሥራቸውን መቀጠል ይችላሉ።

ሥራቸውን መቀጠል የሚችሉት የትኞቹ ሴቶች ናቸው በሚል ለሚነሳ ጥያቄ ከንቲባው በምሳሌ ሲያብራሩም "ሴቶች መጸዳጃ ቤት የምትሠራ የጽዳት ሠራተኛ፣ ወንዶች ይህን ሥራ ሊሠሩት ስለማይችሉ በዚህ መደብ ትሠራ የነበረች ሴት ሥራዋን መቀጠል ትችላለች" ብለዋል።

ነገር ግን ማንኛውም የሥራ መደቦች ወንዶች ሊሠሯቸው የሚችሉ እስከሆነ ድረስ ሴት ሠራተኞች ዝር እንዳይሉ አስጠንቅቀዋል።

"ነገሮች እስኪስተካከሉ ድረስ የከተማዋ ሴቶች አርፋችሁ ቤት ተቀመጡ" ብለዋል ከንቲባው።