ከመቀለ ውጪ በሁለት የተለያዩ ስፍራዎች የአየር ጥቃቶች ተፈጸሙ

የኢትዮጵያ መንግሥት የህወሓት ይዞታዎች ናቸው ባላቸው ከመቀለ ውጪ በሚገኙ በሁለት የተለያዩ ስፍራዎች ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

መንግሥት ዛሬ ጥቅምት 14/2014 ዓ.ም መፈጸማቸውን ባሳወቃቸው የአየር ጥቃቶች በሁለት የተለያዩ ስፍራዎች ላይ ባሉ ኢላማዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን በተከታታይ የወጡት መግለጫዎች አመልክተዋል።

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በበኩላቸው በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ ባሳፈሩት ጽሁፍና ለሮይተርስ ዜና ወኪል በሰጡት ቃል የጥቃቱን መፈፀም አረጋግጠዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት በቀዳሚነት ባሰራጨው አጭር መግለጫ ላይ የመጀመሪያው የአየር ጥቃት በምዕራብ ግንባር የህወሓት ቡድን "ማሠልጠኛ እና የሰው ኃይል ማደራጃ" ነው በተባለው ማይጠብሪ ላይ የተፈጸመ መሆኑን ገልጿል።

በተከታይነት ደግሞ ዓድዋ አካባቢ የሚገኝ ቡድኑ ወታደራዊ ትጥቅ እና አልባሳት የሚያመርትበት ማዕከል በአየር ጥቃቱ "መውደሙን" በመግለጽ፣ የአልባሳት ማምረቻው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የደንብ ልብስ ተመሳስሎ የሚመረትበት ነው ብሏል።

የመንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት ለገሰ ቱሉ ለሮይተርስ ዜና ወኪል "በማይጠብሪ የህወሓት የስልጠናና የከባድ መድፍ ማስቀመጫ ቦታዎች ላይ የተሳካ የአየር ጥቃት" መፈጸሙን አረጋግጠዋል።

የህወሓት ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳም ማይጠብሪ ውስጥ ከሚገኝ "ሆስፒታል አቅራቢያ ጥቃት መፈጸሙን" ከባልደረቦቻቸው ማረጋገጣቸውንና በሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱን እንደተናገሩ ሮይተርስ ዘግቧል።

አቶ ጌታቸው ዓደዋ ውስጥ ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት በትዊተር ገጻቸው ላይ "ቀደም ባለው ጦርነት ሙሉ ለሙሉ የወደመ" ባሉት የአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪ ላይ የተፈጸመ መሆኑን አስፍረዋል።

ዛሬው የአየር ድብደባ ቀደም ካሉት ቀናት በተለየ ከክልሉ ዋና ከተማ ውጪ ከመሆኑ ባሻገር በሁለት የተለያዩ ስፍራዎች በሚገኙ ኢላማዎች ላይ የተፈጸመ ነው።

ከሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ የተስፋፋው ጦርነት ተባብሶ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ካለፈው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ ትግራይ ውስጥ በሚገኙ እና የተመረጡ ኢላማዎች ላይ የአየር ድብደባ እያካሄደ ይገኛል።

ዛሬ እሁድ ከተፈጸመው የአየር ጥቃት በተጨማሪ መንግሥት ሰኞ፣ ረቡዕ፣ ሐሙስ እና አርብ በመቀለ በሚገኙ የተለያዩ ስፍራዎች ላይ የአየር ድበደባ ማድረጉ ይታወሳል።

ጋብ ብሎ የነበረው ጦርነት ከቀናት በፊት መልሶ ካገረሸ በኋላ በዚህ ባለፈው ሰኞ ጥቅምት 08/2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር ኃይል የመጀመሪያውን የአየር ጥቃት መቀለ በሚገኙ ህወሓት ይጠቀምባቸዋል በተባሉ የመገናኛ አውታሮችና መሳሪያዎች ላይ መፈጸሙ ተገልጾ ነበር።

በተመሳሳይ ረቡዕ ጥቅምት 10/2014 ዓ.ም ረፋድ ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙ የሚታወስ ሲሆን የመንግሥት መረጃ ማጣሪያ ማዕከል በሰጠው መግለጫ ጥቃቱ ያነጣጠረው "የህወሓት የጦር መሣሪያ ማምረቻና የጦር ትጥቅ ጥገና ጣቢያዎች" ላይ መሆኑን ገልጿል።

ሐሙስ ጥቅምት 11/2014 ዓ.ም ደግሞ መንግሥት ቀደም ሲል የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት የሥልጠና ተቋም ነበረ ያለውና አሁን ህወሓት የሚጠቀምበት ነው ያለውን መቀለ የሚገኝ የሥልጠና እንዲሁም ወታደራዊ አመራሩ የውጊያ እቅድና ልምምድ የሚያደርግበት ስፍራ ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተገልጿል።

አርብ ጥቅምት 12/2014 ዓ.ም ደግሞ በመቀለ ህወሓት ለወታደራዊ ማሰልጠኛነት እና የወታደራዊ እና የመገናኛ ማዘዣ ማዕከል ነበር የተባለው ቦታ ላይ ጥቃት መፈጸሙን መንግሥት አስታውቆ ነበር።

ህወሓት ጥቃቶቹ በሰላማዊ ሰዎችና ተቋማት አካባቢ የተፈጸሙ ናቸው ብሎ ቢከስም መንግሥት ግን ኢላማዎቹ በተመረጡና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ የተካሄዱ ናቸው ሲል አስተባብሏል።

በመጀመሪያው ዕለት የአየር ጥቃት ሦስት ሰዎች መሞታቸው የተነገረ ሲሆን ከዚያ በኋላ በተፈጸሙ ጥቃቶች ስምንት ሰዎች ላይ የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው በመቀለ የሚገኙ የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበው ጦርነት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ማብቂያ ላይ የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት የትግራይ ክልልን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ወደ አማራና አፋር ክልሎች መስፋፋቱ ይታወሳል።