ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሰሞኑ ጦርነት ምን ተከናወነ? ምንስ ተባለ?
በአማራ እና አፋር ክልሎች እንደ አዲስ ያገረሸውን ጦርነት ተከትሎ በርካቶች መፈናቀላቸውን የክልሎቹ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።
መከላከያ ሠራዊት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ እንደ አዲስ ተጠናክሮ የቀጠለውን ጦርነት የከፈተው ህወሓት መሆኑን በመግለጽ "በሁሉም ውጊያ በከፈተባቸው ግንባሮች ከባድ ጉዳት እየደረሰበት" ነው ብሏል።
ሕወሓት አማፂያን ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ደግሞ ጦራቸው በተሰለፈባቸው ግንባሮች ሁሉ "ድል እየቀናው" መሆኑን በመግለጽ በርካቶችን ደምስሰናል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ በደሴ እና ኮምቦልቻ የተገኘው የአሜሪካው ኤንፒአር የምሥራቅ አፍሪካ ዘጋቢ አይደር ፐራልታ በርካታ ወታደሮችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ጦርነቱ አካባቢ ሲያመሩ መመልከቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።
በደሴ እና ኮምቦልቻ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የገለፀው አይደር፣ በርካቶች የሚመገቡት አነስተኛ ምግብ መሆኑንና የመጠለያ ቦታ አጥተው ሲቸገሩ እንደተመለከተ ገልጿል።
ቀደም ሲል ወደ ከተሞቹ ከገቡት በተጨማሪ አዲስ የተቀሰቀሰውን ጦርነት በመሸሽ በርካታ ተፈናቃዮች እየመጡ መሆናቸውን አመልክቷል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የደሴ ከተማ ከንቲባ፣ አቶ አበበ ገብረመስቀል በደኅንነት ስጋት ምክንያት ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ደሴ የሚገባው ተፈናቃይ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።
"ሴቶች፣ ሕፃናት እና አረጋውያንን ጨምሮ የተፈናቃዮች ቁጥር ወደ 500 ሺህ ይገመታል። በእርግጥ አሁን ያለው የተፈናቃይ ቁጥር በትክክል አልታወቀም" ብለዋል።
የኤንፒአር ዘጋቢ አይዳ በኮምቦልቻ ስለተመለከተው ለቢቢሲ ሲናገር በቁጥር ላቅ ያሉ ወጣቶች ጦርነቱ ወዳለባቸው አካባቢዎች በከባድ መኪኖች ተጭነው ሲሄዱ ተመልክቷል።
በዚህ ግጭት የትግራይ አማጽያን የደሴ ከተማን ለመቆጣጠር በማለም ከባድ ውጊያ እያካሄዱ ሲሆን በከተማዋ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የመጡ ነዋሪዎችም በጭንቀት ውስጥ መሆናቸውን ዘጋቢው አክሏል።
እነዚህ ወደ ግጭት ቀጠናው በመኪና ተጭነው የሚሄዱ ወጣቶች በእጃቸው ያገኙትን መሳሪያ ሁሉ መያቸውን መመልከቱን ገልጿል።
"የመከላከያ ሠራዊት አባላት በአውቶቡስ ተጭነው ሲሄዱ ተመልክቻለሁ። . . . ሌላው ደግሞ ሚሊሻዎች ከመኪና ኋላ ተጭነው፣ ወጣቶች ቆንጨራ፣ መጥረቢያ፣ እጃቸው ላይ የገባውን ነገር ሁሉ ይዘው ወደ ውጊያው ሲሄዱ ተመልክቻለሁ።"
ባለፉት ሳምንታት በጎንደር እና ደሴ አካባቢዎች ማሳለፉን የተናገረው አይደር፣ ራሳቸውን ፋኖ በማለት የሚጠሩ ወጣቶች ይህ ጦርነት የሕልውና መሆኑን እንደሚናገሩ ይገልጻል።
በኮምቦልቻ ከሐምሌ ወር ጀምሮ በህወሓት አማጺያን ቁጥጥር ስር ከሚገኙ የአማራ ክልል አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ማግኝቱን የሚናገረው አይደር፣ እነዚህ ሰዎች ጦርነቱ ወደ ኮምቦልቻ እና ደሴ መጥቶ ዳግም እንዳይፈናቀሉ ስጋት እንደገባቸው ገልጿል።
"ምናልባት ይህ ሁላችንም የምንሞትበት ስፍራ ይሆናል" ሲሉ አንድ ግለሰብ እንደተናገሩም አክሎ ገልጿል።
የአየር ጥቃት
በሰሜን ኢትዮጵያ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት ተፋፍሞ ከቀጠለ ከአንድ ሳምንት በላይ ሆኖታል። ስለጦርነቱ አስተማማኝ መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ ሲሆን ከተለያዩ ወገኖች የሚወጡት መረጃዎች ግን በሰሜን ወሎ አካባቢዎች ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን ያመለክታሉ።
ከዚህ በተጨማሪም የአገሪቱ አየር ኃይል በሦስት ቀናት ሁለት ጊዜ መቀለ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ኢላማዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙ ተነግሯል።
ሰኞ እለት በተፈጸመው ጥቃት በመቀለ ከተማ ውስጥ ሁለት ቦታዎች ኢላማ ሆነው ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን፤ ረቡዕ ረፋድ ላይ ደግሞ እንዲሁ በሁለት ስፍራዎች ላይ የአየር ጥቃት ተፈጽሟል።
በመጀመሪያው ቀን ጥቃት የህወሓት አመራሮች ይጠቀሙባቸዋል ተባሉ የግንኙነት አውታሮች ኢላማ መሆናቸው የተነገ ሲሆን፤ ሁለተኛው ጥቃት ደግሞ የአማጽያው የጦር መሣሪያ ማምረቻና የጦር ትጥቅ ጥገና ጣቢያዎች ላይ ያነጣጠረ እንደነበረ መንግሥት ገልጿል።
ትግራይ
የህወሓት አማጺያን ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በአፋር እና በደቡብ ወሎ ደሴ አቅራቢያ ጦርነት መቀጠሉን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
አቶ ጌታቸው የመንግሥት ኃይሎች በአፋር እና በአማራ የጦርነት ቀጠናዎች "እየተሸነፉ" በመሆኑ የአየር ድብደባውን በመቀለ ማካሄዳቸውን በመጥቀስ ከሰዋል።
አቶ ጌታቸው የፌደራል መንግሥቱ እና የአማራ ክልላዊ መንግሥት በቂ ስልጠና የሌላቸውን ንፁሃን ዜጎችን በዚህ ጦርነት ውስጥ በመሳተፋቸው በርካታ ሟቾች በጦር ግንባሮች እንዲታዩ ማድረጉን አክለው ተናግረዋል።
የህወሓት አማጽያን ከደሴ በስተሰሜን ርቀው ባሉ አካባቢዎች ውጊያ እያካሄዱ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ጌታቸው፣ የመከላከያ ሠራዊቱ በቂ መከላከል እንኳ ማድረግ አልቻለም ብለዋል።
በዚህ ጦርነት ንፁሃን እየተጎዱ መሆኑን በመግለጽ ከመንግሥት ጋር ለመደራደር ፈቃደኝነታቸውን የተጠየቁት አቶ ጌታቸው ሁሌም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አፋር
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ውጊያ እየተካሄደባቸው ባሉት በአማራ ክልል በሚገኙት እንደ ውጫሌ እና ሀብሩ በመሳሰሉ ወረዳዎች ውስጥ የነበሩ በርካታ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ወደ ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች እንደሸሹ ተገልጿል።
በአፋር ክልል ደግሞ ከጭፍራ መጋሌና ሌሎች ወረዳዎች ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የሚመለከታቸው የክልሉ ባለሥልጣኖች ለቢቢሲ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል በአፋር ክልል በተለይም ከጭፍራ እና ከመጋሌ ወረዳዎች ባለፉት ጥቂት ቀናት ነዋሪዎች እየተፈናቀሉ እንደሚገኙ የአፋር ክልል የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ከጭፍራ ወረዳ ከ35 ሺህ በላይ ሰው ተፈናቅሏል። ከመጋሌ ወረዳ ደግሞ ወደ 10 ሺህ ሕዝብ ተፈናቅሏል። ከዚህ ወረዳ የሁለት ቀበሌ ሕዝብ ነው የተፈናቀለው። ከዚህ በፊት ከነበረው 150 ሺህ ተፈናቃይ ጋር ሲደመር አሁን ያለው የተፈናቃዮች ቁጥር ከ200 ሺህ በላይ ይሆናል" ብለዋል።
ጭፍራ ወረዳ ከአማራ ክልል ጋር የሚዋሰን ሲሆን፤ መጋሌ ወረዳ ከትግራይ ክልል ጋር ይዋሰናል።
ተፈናቃዮችን ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ መሐመድ፤ ውጊያው በከፍተኛ ሁኔታ በቀጠለባቸው እንደ ጭፍራ ያሉ አካባቢዎች ግን ሰዎች አሁንም እየተፈናቀሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
"በርካታ ሰዎች በየጫካው፣ በየጥሻው ተበትነው ይገኛሉ። አሁን የጠፉ እና ከቤተሰብ የተለያዩ ሰዎችን አግኝቶ አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ ለመስጠት ጥረት እያደረግን ነው" ብለዋል።
መጠለያ፣ ምግብ እና የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የጀመሩትን ጥረትም አክለዋል።