በመቀለ በአራት ቀናት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ የአየር ጥቃት ተፈጸመ

በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ በአራት ቀናት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ አየር ኃይል የአየር ጥቃት መፈጸሙ ተዘገበ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ ዛሬ ሐሙስ የአየር ጥቃት መፈጸሙን ለሮይተርስ ዜና ወኪል አረጋግጠዋል።

የዛሬው የአየር ድብደባ ኢላማ ያደረገው የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ይዞታ የነበረና በአሁኑ ጊዜ የህወሓት ኃይሎች የማሰልጠኛ ማዕከል መሆኑን ቃል አቀባዩ ለዜና ወኪሉ ጨምረው ገልጸዋል።

የኢፌድሪ መከላከያ ሠራዊት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ በበኩሉ፣ የአየር ኃይሉ በመቀሌ የአየር ድብደባ ማካሄዱን ገልጿል።

መግለጫው የአየር ጥቃቱ መቼ እንደተፈፀመ ባይገልጽም "የመሳሪያ ማከማቻ፣ የጥገና ቦታዎችን፣ ማሰልጠኛዎችን፣ የማዘዣ ጣቢያዎችን እና የሎጂስቲክ አቅርቦት የሚያቀርቡና ሃብት የሚያሸሹትን ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ከባድ መሳሪያዎቻቸውን" ማውደሙን ገልጿል።

መከላከያ በተለያዩ የአፋርና የአማራ አካባቢዎች ጦርነት እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ "ውዥንብር ፈጣሪዎች" ያላቸውን 17 ግለሰቦችንም በደሴና ኮምቦልቻ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል።

በመቀሌ ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 11/2014 ዓ.ም የአየር ድብደባ የተፈፀመው፣ ከሰዓት ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ ሲሆን ቀደም ሲል ሰኞ እና ረቡዕ እለት በተለያዩ ስፍራዎች ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙ ይታወሳል።

የፈረንሳይ ዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በበኩሉ በመቀለ የአየር ጥቃት ስለመፈጸሙ ዘግቧል።

የህወሓት አማፂያን ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ ዛሬ ከሰዓት የአየር ኃይሉ በመቀለ ጥቃት ለማድረስ ሶስት ጊዜ መሞከሩን ነገር ግን "መመከታቸውን" አስፍረዋል።

ጋብ ብሎ የነበረው ጦርነት ከአንድ ሳምንት በፊት መልሶ ከተጀመረ በኋላ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ ጥቅምት 08/2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር ኃይል የመጀመሪያውን የአየር ጥቃት መቀለ ውስጥ በሚገኙ ኢላማዎች ላይ ማድረጉን መግለፁ ይታወሳል።

ስለአየር ድብደባው በዕለቱ ከመንግሥት በኩል ይፋዊ መግለጫ ሳይሰጥ ቆይቶ በመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በኩል በወጣ ዘገባ አየር ኃይሉ በመቀለ ከተማ "ህወሓት ለሽብር ተግባር ሲጠቀምባቸው በቆዩ የመገናኛ አውታሮችና መሳሪያዎች" ጥቃት መፈጸሙን አመልክቶ ነበር።

በጥቃቱ የፈደራል መንግሥቱ ንብረት የነበሩና ህወሓት እየተጠቀመባቸው በነበሩ የመገናኛ ብዙኃንና የግንኙነት ማማዎች እንዲሁም መሳሪያዎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ዘገባው አመልክቶ ነበር።

አየር ኃይሉ ኢላማ ያደረጋቸው በተመረጡ ስፋራዎች ላይ መሆኑን በመጥቀስ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ ማድረጉን ገልጿል።

በእለቱ የደረሰ ጉዳትን በተመለከተ የወጡ ዘገባዎችና የመንግሥታቱ ድርጅት በጥቃቱ ሦስት ሰዎች መሞታቸውን አመልክተዋል።

በተመሳሳይ ረቡዕ ጥቅምት 10/2014 ዓ.ም ረፋድ ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙ የሚታወስ ሲሆን የመንግሥት መረጃ ማጣሪያ ማዕከል በሰጠው መግለጫ ጥቃቱ ያነጣጠረው "የህወሓት የጦር መሣሪያ ማምረቻና የጦር ትጥቅ ጥገና ጣቢያዎች" ላይ መሆኑን ገልጿል።

በጥቃቱ መቀለ ከተማ የሚገኘው የመስፍን ኢንደስሪያል ኢንጂነሪንግ የተባለው ተቋም ላይ ጉዳት መድረሱ የተነገረ ሲሆን ስምንተ ሰዎች ላይ የመቁሰል ጉዳት መድረሱን የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አንድ ዓመት ሊሞላው ሁለት ሳምንታት የቀረው ጦርነት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ማብቂያ ላይ የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት የትግራይ ክልልን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ወደ አማራና አፋር ክልሎች መስፋፋቱ ይታወሳል።

መንግሥት በሽብርተኛ ቡድንነት የፈረጀው የህወሓት ኃይል በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ ጥቃት በመሰንዘር የተለያዩ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ ከፌደራሉ የመከላከያ ሠራዊት፣ ከክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች ጋር ለወራት ውጊያ ሲካሄድ ቆይቷል።

ከጥቅምት ወር መጀመሪያ ጀምሮ ጦርነቱ ተጠናክሮ መቀጠሉ የተነገረ ሲሆን ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ሳምንት ተከታታይ የአየር ድብደባዎችን መቀለ ውስጥ በሚገኙ ኢላማዎች ላይ እያካሄደ ይገኛል።