ባሕር ጠላቂው 900 ዓመት ያስቆጠረ የመስቀል ጦረኛ ሰይፍ አገኘ

ሰይፉ ምርመራ ከተደረገለት በኋላ ለሕዝብ ዕይታ ይቀርባል ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሰይፉ ምርመራ ከተደረገለት በኋላ ለሕዝብ ዕይታ ይቀርባል ተብሏል።

አንድ ባሕር ጠላቂ በሰሜናዊ እስራኤል 900 ዓመት ያስቆጠረ የመስቀል ጦረኛ ሰይፍ ማግኘቱ ተገለጸ።

አንድ ሜትር ርዝመት ያለውን የመስቀል ጦረኛ ሰይፍ ያገኘው ሻሎሚ ካትዚን ሰይፉን ለእስራኤል ባለሥልጣናት አስረክቧል።

የመስቀል ጦረኞች በመካከለኛው ዘመን ወቅት ለሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ወግነው በበርካታ ሐይማኖታዊ ጦርነቶች ላይ ተሳትፈዋል።

ጦረኞቹ በምሥራቅ ሜዲትራኒያን ቅዱስ የተባሉ ቦታዎችን ከሙስሊም አገዛዝ ለማስለቀቅ ዘመቻ በማድረግ በስፋት ይታወቃሉ።

የእስራኤል ቅርሶች ባለስልጣን በሰይፉ ላይ አስፈላጊው ምርመራ ከተደረገ እና እንዲጸዳ ከተደረገ በኋላ ለሕዝብ ዕይታ ይቀርባል ብሏል።

"ሰይፉ ፍጹም ሊባል በሚችል መልኩ ተጠብቆ ቆይቷል፤ እጅግ ውብ ነው። በቀላሉ ማግኘት የማይቻል ነገር ነው የተገኘው" ሲሉ የእስራኤል ቅርሶች ባለስልጣን ተናግረዋል።

ሰይፉ የተገኘው ካርሜል ተብሎ በሚጠራ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ነው። የእስራኤል ቅርሶች ባለሥልጣን ባለሙያ ሆኑት ኮቪ ሻርቪት ይህ የውሃ አካላት ከበርካታ ዓመታት በፊት መርከቦች ከአደገኛ ማዕበል ለመሸሸግ ተመራጭ የሚያደርጉት አካባቢ ነው ይላሉ።

"በዚህም ይህ የውሃ አካል በርካታ ጥንታዊ ቅርሶች ቦታ መገኛ ሆኗል" ይላሉ።