ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ6 ሺህ በላይ ሆነ
በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ስድስት ሺህ ማለፉን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ባለፉት ጥቂት ወራት በአገሪቱ ውስጥ በወረርሽኙ ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በአሳሳቢ ሁኔታ መጨመሩን በየዕለቱ የሚወጣው መረጃ የመለክታል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ እንደተናገሩት በኮሮናቫይረስ ተይዘው ለሞት ከተዳረጉት ሰዎች መካከል ሁሉም በሚባል ደረጃ ያልተከተቡ ናቸው።
በአገሪቱ ውስጥ ከሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ እሰከ ነሐሴ ወር አጋማሽ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በወረርሽኙ ከሞቱ ሰዎች መካከል አንድ ግለሰብ ብቻ የመጀመሪያውን የኮቪድ መከላከያ ክትባት የወሰደ ሲሆን ሌሎቹ በሙሉ ያልተከተቡ መሆናቸው ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት መሰጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ወደ ሦስት ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች መከላከያ ክትባቱን ማግኘታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።
በሽታው በአገሪቱ ውስጥ መገኘቱ ከታወቀ ጊዜ ጀምሮ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች አሃዝ አስከ ትላንት ድረስ ከስድስት ሺህ በታች የነበረ ሲሆን ሰኞ ጥቅምት 01/2014 ዓ.ም 36 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር 6026 ደርሷል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በበሽታው የሚያዙ፣ በጽኑ የሚታመሙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ለመጨመሩ በአገሪቱ ውስጥ አደገኛው የዴልታ ዝርያ መኖሩ፣ በአንድ ስፍራ በብዛት የሚደረጉ መሰባሰቦችና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን ጨምሮ የበሽታውን የመከላከያ መመሪያዎች በአግባቡ ተግባራዊ አለማድረግ ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ጨምረውም በበሽታው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑንና ባለፈው ሳምንት ብቻ 308 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ይህም ወረርሽኙ ከበኢትዮጵያ ከተከሰተ በኋላ ከፍተኛው የሞት አሃዝ ሆኖ እንደተመዘገበ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ በየዕለቱ በአማካይ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ የሚረጋገጥ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት በየቀኑ በአማካይ 44 ሰዎች ህይወታቸው እንዳለፈ ተገልጿል።
በአገሪቱ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ምረመራ መደረግ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ አስከ ትናንት ድረስ 3,557,710 ሰዎች ምርመራ ተደርጎላቸው በ355,001ዱ ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል።
ከእነዚህ ውስጥም 324,450ው ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን 6,026ቱ ደግሞ ህይወታቸው ማለፉንም የጤና ሚኒስቴር አመልክቷል።