በኦሃዮ አካል ጉዳተኛውን ከመኪና ጎትተው ያወረዱት የፖሊስ አባላት ላይ ምርመራ እየተደረገ ነው

ተንቀሳቃሽ ምሥሉ ግለሰቡን ከመኪናው ጎትተው ሲያወርዱት ያሳያል

የፎቶው ባለመብት, DAYTON POLICE DEPARTMENT

የፖሊስ አባላት አንድን ጥቁር ግለሰብ "እኔ አካል ጉዳተኛ ነኝ" እያለ እየወተወተ ከመኪናው ጎትተው ሲያወርዱት የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል ከታየ በኋላ የአሜሪካ ፖሊስ ጉዳዩን እየመረመረ ነው።

በአነስተኛ ካሜራ የተቀረጸው ተንቀሳቃሽ ምሥል ባለፈው ወር በኦሃዮ ዳይተን ከተማ የፖሊስ አባላቱ ክሊፎርድ ኦውንስቢይ የተባለውን ግለሰብ አስቁመው አደንዛዥ እፅ ይዞ እንደሁ ለመፈተሽ ከመኪናው እንዲወርድ ሲጠይቁት ያሳያል።

የ39 ዓመቱ ኦውንስብይም በእግሮቹ መንቀሳቀስ እንደማይችል በመግለፅ እንደማይወርድ ሲገልጽላቸው ተደምጧል።

የፖሊስ አባላቱ ግን በማስገደድ ግለሰቡ እርዳታ እየተማፀነ ጸጉሩንና እጆቹን ጨምድደው እየጎተቱ ከመኪናው አውርደውታል።

የዳይተን ፖሊስ መስከረም 20/2014 ዓ.ም የተፈፀመውን ይህንን ድርጊት እየመረመርኩ ነው ብሏል።

ባለሥልጣናት እንዳሉት የፖሊስ አባላቱ ኦውንስብይን ያስቆሙት ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዘ ከተጠረጠረ ቤት እያሽከረከረ ሲወጣ በማየታቸው ነው።

ፖሊስ በግለሰቡ መኪና ውስጥ 22 ሺህ 450 ዶላር ጥሬ ገንዘብ የያዘ ቦርሳ አግኝቻለሁ ብሏል።

በእርግጥ ኦውንስብይ ከዚህ ቀደም ከአደንጻዥ እፅ ጋር በተያያዘ ክስ ቀርቦበት አያውቅም።

ድርጊቱ ተፈፀመበት በተባለበት ጊዜ ኦውንስብይ ምንም እንኳን ፖሊሶች ከመኪናው ለመውረድ እንደሚረዱት ቢገልፁለትም በተደጋጋሚ ከመኪናው እንደማይወርድ ገልጿል።

ኦውንስብይም የፖሊስ አባሉን 'ነጭ ለባሽ ወይም 'የበላይ' ካለ ጥራልኝ ሲል ጠይቋቸዋል።

በዚህ ጊዜ "ከመኪናው ጎትቼ አወርድሃለሁ፤ ከዚያም ነጭ ለባሹን እጠራልሃለሁ" ሲል የፖሊስ አባሉ ምላሽ ሰጥቷል።

ከዚያም የፖሊስ አባሉ ብስጭት ሲጨምር "ተባብረን ከመኪናው እናውርድህ ወይስ ከመኪናው ጎትቼ ላውርድህ ? " በማለት ፖሊሱ ሲጠይቀው ይታያል።

የዳይተን ከንቲባ ናን ዋሊይ ተንቀሳቃሽ ምሥሉን "በጣም አሳሳቢ" ብለውታል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም ጉዳዩን እየተመለከቱት እንደሆነ ገልጸዋል።

ለጥቁር ሕዝቦች የሚሟገተው ብሔራዊ ማኅበር ኃላፊ ዴሪክ ፎዋርድ " ፀጉሩን ጨምድደው ይዘው ይህንን አካል ጉዳተኛ ግለሰብ ከመኪና ማውረድ ሰብዓዊነት የጎደለው እና በከተማችን ላይ ጥቁር ጠባሳ የጣለ ነው" ሲሉ ለዋሽንግተን ፖስት ተናግረዋል።

አንዳንዶች ግን ለፖሊስ አባላቱ ተሟግተዋል።

የዳይተን ፖሊስ ሎጂ 44 ፕሬዚደንት ጄሮሜ ዲክስ " የፖሊስ አባላቱ ሕጉን፣ ሥልጣናቸውንና ፖሊሲያቸውን ተከትለዋል" ብለዋል።

ዲክስ አክለውም "አንዳንዴ የማይታዘዙ ግለሰቦችን ማሰር ጥሩ አይደለም፤ ነገር ግን የሕብረተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ የሆነ የሕግ ማስፈፀም አካል ነው።" ሲሉ ተናግረዋል።