ፅንስ የማቋረጥ መብትን የሚጠይቁ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ለተቃውሞ ወጡ

ፅንስ የማቋረጥ መብት እንዲከበር የሚጠይቁ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን በአምሳ የአሜሪካ ግዛቶች የተቃውሞ ሰልፍን እያካሄዱ ነው።

በቴክሳስ ፅንስ ማቋረጥን በእጅጉ የሚገድብ አዲስ ህግ መፅደቁንም ተከትሎ በርካቶች ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።

ምርጫ ሊከበር ይገባል የሚሉ አሜሪካውያን ህገ መንግሥታዊ መብቶች ሊጣሱ ይችላሉ የሚልም ፍራቻ አላቸው

በሚቀጥሉት ወራት የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፅንስ ማቋረጥን በአገር አቀፍ ደረጃ ህጋዊ ያደረገውን 'ሮ ቨርሰስ ዌድ' የተባለውን የአውሮፓውያኑን 1973 ውሳኔ ይሻር የሚለውንም ጉዳይ ያያል።

በዋሽንግተን ዲሲ ተቃዋሚ ሰልፈኞች "ፅንስ ማቋረጥ ህጋዊ ይሁን" የሚሉ ባነሮችን ይዘው ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕንፃ ዘምተዋል።

ሰልፉ በጀመረበት ወቅት ፅንስ ማቋረጥን በሚቃወሙ ሌሎች ሰልፈኞች ተረብሾ ነበር።

"የንጹሃን ሕፃናት ደም በእጃችሁ ላይ ነው!"በማለት አንድ ሰው የጮኸ ሲሆን ነገር ግን በሕዝቡ ዘፈን እና ጭብጨባ ምላሽ ድምፁ መዋጡን ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ዘግቧል።

በሰልፍ ላይ የተገኘች አንዲት ግለሰብ የሴት የመምረጥ መብቷ እንዲከበር ድጋፍ ለመስጠት እንደወጣች ተናግራለች።

"እኔ እንደ እድል ሆኖ እኔ ያጋጠመኝ ነገር ባይኖርም ብዙ መምረጥ አንዳይችሉ የተደረጉ በርካታ ሴቶች አሉ። መንግሥትም ሆነ ወንዶች በሰውነታችን ላይ ምንም አስተያየትም ሆነ መብት ሊኖራቸው አይገባም' በማለት ሮቢን ሆርን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

የተቃውሞ ሰልፎቹን ያዘጋጁት ከዓመታዊው የሴቶች መጋቢት ዘመቻ ጀርባ ያሉት ግለሰቦች ናቸው። የመጀመሪያ ሰልፋቸውም በአውሮፓውያኑ 2017 የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከተሾሙ ከአንድ ቀን በኋላ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ተቃውሟቸውን ያሰሙበት ነው።