በአሜሪካ እና አውሮፓ ለሚገኙ የከፍተኛ ተቋም ተማሪዎች ጥናታዊ ጽሑፍ በመሸጥ የሚኖሩ ኬንያውያን

ዩኒቨርስቲ ውስጥ ትምህርት የሚከታተሉ ተማሪዎች የሚሰጡ አሳይመንቶች ሲበዙባቸውና ሲጨናነቁ ኬኔዲ እና ጓደኞቹ ክፍያ በመቀበል ሥራውን ጨርሰው ለተማሪው ያቀርባሉ።

ከዚያም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ዘና ብለው በማስረከቢያው ቀን ልክ እንደራሳቸው የልፋት ውጤት ሚጠበቅባቸውን ለመምህራኖቻቸው ያስረክባሉ፤ በአንዳች መንገድ ካልተነቃባቸው በዚሁ መንገድ ወደ ሌላናው ደረጃ ያልፋሉ።

ኬኔዲ ከዚህ ቀደም በመምህርነት ሙያ ያገለግል ነበር። ነገር ግን ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ኑሮውን የሚገፋው በተለየ የሥራ መስክ ነው።

"የጥናት ጽሁፎችን እሰራለሁ" ይላል።

የእርሱ የሥራ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያበበ ሲሆን፣ በኬንያ ደግሞ የዚህ 'የሥራ እድል' ተቋዳሾች ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ ነው።

ነገር ግን ኬኔዲ እና በርካታ ሌሎች ኬንያውያን "ጥናታዊ ጽሁፍ መጻፍ" ብለው ሥራቸውን ቢያስረዱም ቀሪው ዓለም ግን ማጭበርበር ሲል ይጠራዋል።

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና በእነ ኬኔዲ መካከል ያለው አገናኝ መድረክ ድረ ገጾች ናቸው፤ እዚያ ላይ አሳይመንቶቻቸው (የጥናት ጽሁፎችና ሌሎች በግል የሚሰሩ መመዘኛዎች) እንዲሰራላቸው የሚፈልጉ ተማሪዎች ጥያቄዎቻቸውን ያስቀምጣሉ።

የአካዳሚክ ጽሁፎችን የሚጽፉት ግለሰቦች ደግሞ ምስላቸውን በድረ ገጹ ላይ ለጥፈው ደንበኞቻቸውን ይጠባበቃሉ።

ነገር ግን ምስሎቹ በአጠቃላይ በነጮች የተሞሉ ሲሆን ይህም ተማሪዎቹ የተሰጣቸውን ሥራዎች የሚሰሩት የምዕራቡ ዓለም ዜጎች እንደሆኑ ለማስመሰል እና በቀላሉ ለማጭበርብ በሚል የተደረገ ነው።

ነገር ግን ይህ እንደ በርካታ ቢዝነሶች ማጭበርበሪያ መንገድ ነው።

እውነታው ለተማሪዎች የተሰጠውን ሥራ የሚሰራላቸው ፍለጋ ወደ ድረ ገጾቹ ጎራ ሲሉ፣ ኬንያ የሚገኝ አንድ ኬንያዊ፤ ምናልባትም ተማሪ ወይንም ተመራቂ የሆነ ግለሰብ የሚከፈለውን ገንዘብ ተደራድሮ ሥራውን ይከውናል።

እንደዚህ ዓይነት በርካታ ድረገጾች መቀመጫቸውን ያደረጉት በአሜሪካ እና በምሥራቅ አውሮፓ ሲሆን ክፍያቸውም በግማሽ ዝቅ ያለ ነው።

ክፍያው ደግሞ እንደ አሳይመንቱ ዓይነት ይለያያል።

ቀላል ጥናታዊ ጽሁፎችን (essay) ከማጻፍ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ የማሟያ ጽሁፍ ድረስ የሚዘልቅ ከሆነ እንደ ሥራው ትዕዛዝ ክፍያውም ይለያያል።

ይህንን ቢዝነስ ያጠኑ ባለሙያዎች ኬንያ መናኸሪያ መሆኗን ይገልጻሉ።

ባለሙያዎቹ "ኮንትራት ወስዶ ማጭበርበር" ሲሉ የሰየሙት ይህ የሥራ ዓይነት ኬንያውያን ለመስራት የመረጡበት ምክንያት የእንግሊዘኛ ተናጋሪ አገር እና፣ የትምህርት ሥርዓቷ የተሻለ በመሆኑ ነው።

በተቃራኒው ደግሞ በተለይ ለወጣቶች ያለው የሥራ እድል አነስተኛ መሆኑ ይበልጥ የሥራውን መስክ ሳቢ አድርጎታል።

በተመረቁበት ዘርፍ የሥራ እድል ያጡ ወጣቶች እውቀታቸውን ተጠቅመው ለሚከፍሉ የባሕር ማዶ ተማሪዎች የሚፈልጉትን ሥራ ማከናወንን እንደ መልካም የሥራ እድል ቆጥረውታል።

ለኬኔዲ ደግሞ ይህንን የሥራ እድል ማግኝት 'እልል በቅምጤ' የሚያስብል ነው።

"መምህር ሆኜ ይከፈለኝ ነበርው አሁን ከማገኘው ጋር ሲታሰብ በጣም ትንሽ ነው" ይላል።

የ30 ዓመቱ ኬኔዲ በወር 1ሺህ 360 የአሜሪካ ዶላር (150 ሺህ ሽልንግ) ያገኛል፤ ይህ ደግሞ ከአገሪቱ አማካኝ ገቢ ጥቂት ከፍ ያለ ማለት ነው።

እርሱ ቀጥሮ የሚያሰራቸው ግለሰቦች ደግሞ በወር እስከ ሁለት መቶ ቀላል ጥናታዊ ጽሁፎችን ወይንም የኦን ላየን ፈተናዎች ይሰራሉ።

"በአካውንታቸው ገብቶ ፈተናውን ለእነርሱ መስራት ነው" ሲል ያክላል።

በዓለም ላይ ያለውን የትምህርት ጥራት ዝቅ ማድረግ ላይ አስተዋጸኦ ማበርከቱን በሚመለከት ምን ይሰማው ይሆን? የቢቢሲ ጥያቄ ነበር።

ከዚህ ቀደም መምህር እንደነበረ በማንሳት "በሥነምግባር ጥያቄ ውስጥ" እንደሚወድቅ ይናገራል፤ ነገር ግን ለገንዘቡ ሲል እንደሚሰራው በማስረዳት ለማሳመን ይሞክራል።

"እጨነቃለሁ፤ ግን ከገዛ ሕይወቴ በላይ ስለምን ልጨነቅ እችላለሁ? አንዳንዴ ስለ ሞራል ልዕልና ለመጨነቅ አስቀድመህ መኖር አለብህ።"

ኬኔዲ የእርሱ የእጅ ፍሬ ደንበኞቹ ባልዋሉበት የትምህርት መስክ ዲግሪያቸውን እንዲያገኙ፣ ከዚያም እርሱ ከሚያገኘው ከፍ ያለ የሥራ እድል ሊገጥማቸው እንደሚችል ያውቃል።

"ከእነርሱ ጋር ውድድር አለመያዜን እረዳለሁ፤ አንዳንዴ ፉክክሩ ከድህነት ጋር ነው" አጭር እና ቁፍጥን ያለ መልሱ ነው።

በሌላ አገር የተማሪዎችን አሳይመንት የሚሰሩ የመኖራቸውን ያህል በኬንያ የሚገኙት ደግሞ የራሳቸውን ባህል አዳብረዋል።

የተለያዩ ክፍት የሥራ እድሎችን እና መተግበሪያዎች እንደሚተዋወቁባቸው እና እንደሚሸጡባቸው ያሉ የፌስቡክ እና የቴሌግራም ገጾች ሁሉ "የአካዳሚክ ጽሁፎችን የሚጽፉ ሰዎች" ቡድኖች አሉ።

አንዳንዶቹ በአስር ሺዎች የሚቆጠር አባላት አሏቸው።

በእነዚህ ገጾች መካከለኛ ገቢ የሚያስገኙ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ እና ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ከቋመጡ፣ በዩኒቨርስቲዎች እስካሉ ተማሪዎች በአባልነት ይገኙበታል።

ዴቪድ የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ለማጠናቀቅ አንድ ዓመት ብቻ የቀረው ሲሆን ትምህርቱን በገንዘብ የሚደጉመው በዚህ መልኩ መሆኑን ይናገራል።

"ወላጆቼ እኔን ከፍለው ለማስተማር አይችሉም" የሚለው ዴቪድ፣ "ስለዚህ ራሴን ለማስተማር እንዲሁም ቤተሰቦቼን ለመርዳት መንገድ መፈለግ ነበረብኝ" ብሏል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ዴቪድ ዲግሪውን እየሰራ ወደ 360 አነስተኛ የጥናት ጽሁፎችን በብሪታኒያ እና በአሜሪካ ለሚገኙ ደንበኞቹ ጽፏል።

በገጽ 250 ሺልንግ (2.28 ዶላር) ለከፈለው በቀን 15 ገጾች ያለው አሳይመንትን ያጠናቅቃል።

"ከሰኞ እስከ አርብ ቀንም ማታም ልሰራ እችላለሁ፤ ቅዳሜና እሁድ ግን የራሴ ትምህርት ላይ አተኩራለሁ።"

በሚያገኘው ገቢ በትውልድ ስፍራው መሬት መከራየት እንዲሁም የሚያርስለት የጉልበት ሠራተኛ መቅጠር ችሏል።

ዴቪድ ተቀጥሮ የሚሰራው ከእርሱ ቀድሞ ወደዚህ ሥራ ለገባ ሌላ ግለሰብ ነው።

ይህ ግለሰብ በአንድ ትልቅ የውጭ ድረገጽ የፀሐፊዎች አካውንት አለው።

ነገር ግን የራስ አካውንት በድረገጾቹ ላይ መክፈት ቀላል አይደለም።

አንዳንድ ኩባንያዎች አመልካቾች የአካዳሚ ፈተና እንዲወስዱ ይጠይቃሉ።

አምስት ኮከብ ያላቸው እና በደንበኞቻቸው ጥሩ ዝና ያገኙ አካውንቶች ገበያው ላይ ተፈላጊ ብቻ ሳይሆኑ ወደዚህ የሥራ መስክ ለመግባት በሚፈልጉ ግለሰቦች ይገዛሉ፤ ይሸጣሉ።

በትምህርታቸው የሚያጭበረብሩ ተማሪዎች ራሳቸው የሚጭበረበሩት እዚህ ጋር ነው።

የተሰጣቸው አሳይመንት በሥራው በተመሰከረለት ባለሙያ የሚሰራላቸው ይመስላቸዋል።

ነገር ግን እውነታው የቤት ሥራቸው የሚወድቀው ጥሩ ሙገሳ ካገኘ አካውንት የገዛ አንድ ግለሰብ እጅ ላይ ነው።

"ከአስር አካውንቶች በላይ ገዛቻለሁ" ይላል ኬኔዲ። "አንዳንዶቹ እስከ 500 ሺህ የኬንያ ሽልንግ (4550 ዶላር) ድረስ ያወጣሉ። ከዚህ ውጪ ደንበኞችን ለማግኘት ሌላ አማራጭ የለም"

ዴቪድ ከተመረቀ በኋላ የራሱን አካውንት እንዲኖረው ይፈልጋል።

ገና 23 ዓመቱ ቢሆንም በሥራው መስክ በርካታ ዓመት ካስቆጠሩት እኩል ወደ መሆን እየተሸጋገረ ነው።

ወደ ሥራው ዓለም የሚቀላቀሉ ጀማሪ ፀሐፊዎችን ስልጠና እየሰጠ ቀላል ሥራዎችን እንዲሰሩ እያደረገ ነው።

"ጓደኝነታችንን እናጠናክራለን እና በተጨማሪ እንረዳዳለን። ስለዚህ እያደገ የሚገኝ ኢንደስትሪ ነው።"

ሌሎች ግን በዚህ የሙያ መስክ ላይ ተስፋ ማድረግ አይፈልጉም።

ጆን የአካዳሚ ጽሁፎችን ወደ መጻፍ የገባው ከተመረቀ በኋላ ነው።

ነገር ግን ይህንን ሥራ ሁሌም የሚመኘውን የጋዜጠኝነት ሥራ ካገኘ በኋላ ለማቆም ይፈልጋል።

"ለነርሲንግ ተማሪዎች የሚሰጡ አሳይመንቶችን የሚሰሩ ሰዎች አሉ። የተሰጠውን ፈተና ለሌሎች ከፍሎ ባሰራ የሕክምና ባለሙያ ለመታከም ወደ ሆስፒታል መሄድ አልፈልግም። በጣም አደገኛ ነው። ሳስበው ራሱ ይሰቀጥጠኛል" ካለ በኋላ "ሊቆም ይገባዋል" ሲል አክሏል።

ዶ/ር ግላዲስ ኒያቺዮ፣ በናይሮቢ መልቲሚዲያ ዩኒቨርስቲ የሶሲዮሎጂ መምህርት ናቸው።

እርሳቸው እንደሚሉት ኮንትራት ገብተው የማጭበርበር ሥራ የሚሰሩትን ለማስቆም ቁልፉ ያለው ከሀብታም አገራት ዘንድ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው የእነዚህ ደንበኞች የሚገኙት በአገራቸው መሆኑን በመጥቀስ ነው።

"ፍላጎት ሳይኖር አቅርቦት አይኖርም" ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

"ይህ ጉዳይ እንዲታገድ ወይንም ሕገወጥ እንዲሆን እርምጃ የሚወስዱ ከሆነ ሊቀንስ ይችላል" ሲሉ አክለዋል።

አንዳንድ አገራት እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል።

ባለፈው ዓመት አውስትራሊያ ጥናታዊ ጽሑፍ የሚሸጥበትን አገልግሎት አግዳለች።

በእንግሊዝም ተመሳሳይ የሆነ ሕግ እየታሰበ ነው።

ነገር ግን ይህ በቀላሉ ዓለም አቀፍ ድንበርን የተሻገረ የሥራ ዘርፍን ለማስቆም ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል የሚለው ላይ አፍ ሞልቶ መናገር አይቻልም።

ዶ/ር ኒያቺዮ ግን የበኩላቸውን ለማድረግ እየጣሩ መሆኑን ይናገራሉ።

"ለተማሪዎቼ መልካም ሥነምግባር አለመሆኑን፣ ተገቢ እንዳልሆነ እነግራቸዋለሁ" በመቀጠልም "ነገር ግን ያንን ብቻ ነው ማድረግ የምችለው፤ ለአንዳንድ ሰዎች የመኖር እና ያለ መኖር ጥያቄ ነው፤ ስለዚህ መንታ መንገድ ላይ እንደመቆም ያለ ነው" ብለዋል።

* በዚህ ታሪክ ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ ግለሰቦች ስም ተቀይሯል