ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትምህርት ቤት፡ በትግራይ የዳስ ትምህርት ቤት መምህርቷ ተሞክሮ
በትግራይ ክልል ጥቁር ሰሌዳ የሌላቸው፣ የአጋዥ መማሪያ መጽሐፍት እጥረት ያለባቸው፣ በእጃቸው እንጨት ይዘው ድንጋይ በከበበው ጥላ ስር የሚያስተምሩ አስተማሪዎች፣ ድንጋይ ላይ ተቀምጠው የሚማሩ ተማሪዎች የሚገኙባቸው "ትምህርት ቤቶች" አሉ።
ትምህርት ቤቶቹ በቆላማ ስፍራ የሚገኙ ከሆነ ደግሞ ፀሐይዋ የሚቀመጡባትን ድንጋይ ስለምታግል፣ ተማሪዎቹ " ድንጋዩን ጭቃ ቀብተው" ለመቀመጥ ይገደዳሉ።
የዚህ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም ጠዋትና ማታ ድንጋይ ስር ቁጭ ብለው፣ በዙርያቸው ሳር እየጋጡ ከሚጮሁ የቤት እንስሳት፣ በድንጋይ ስር ከሚሹለከለኩ ተሳቢ ነፍሳት ጋር ጸሐይና ንፋስና እየተፈራረቀባቸው በዳስ ስር ይማራሉ።
ይህ እውነት የትግራይ የዳስ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የእለት ተእለት እውነታ ነው። የመምህራኖቹም የሕይወት ተሞክሮ።
የመማሪያ ክፍሎቹ መቀመጫ፣ መምህራንም ቋሚ ቢሮ የላቸውም።
ትምህርት ቤቶቹ በክረምት ወቅት ፈርሰው መስከረም ሲጠባ ዳግም በተማሪዎች ወላጆች ተጠግነው ነው አገልግሎት የሚሰጡት።
በክፍሎች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች በንፋስና ፀሐይ ይታወካሉ። ዝናብ በሚመጣበት ጊዜ መማሪያ ክፍላቸው ስለማያስጠልል ትምህርት ይቋረጣል።
መምህርት ሙሉብርሃን አረጋዊ፡ በትግራይ ምእራባዊ ዞን ቃፍታ ሑመራ ወረዳ በሚገኘው ሶላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪም ርእሰ መምህርትም ሆና ሰርታለች።
"በአካባቢው በርካታ የዳስ ክፍሎች ስላሉ፤ ተማሪዎች ትምህርት የመቀበል አቅማቸው ከ50 በመቶ በታች ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም" ትላለች።
'የተፈጥሮ አደጋ፣ እንስሳት ወይም ሌላ ይመጣብን ይሆን?' ተማሪዎቿ በትምህርታቸው መካከል የሚጠይቋት ጥያቄ ነው።
በዚህ ምክንያት ትኩረታቸው ከምትሰጣቸው ትምህርትና መጽሐፋቸው ላይ ሳይሆን፤ አይኖቻቸው ውጪ ውጪ እያማተረ በተከፋፈለ ስሜት ነው ተምረው ነው ወደ ቤት የሚመለሱት።
"ድንጋይ ስር ጸሐይና ንፋስ እየመታው የሚማር ተማሪ ዝቅተኛ የትምህርት ውጤት ሊኖረው ግድ ይላል። በተለይ ህጻናት ስለሆኑ፡ በዚህ ሁኔታ ማለፋቸው እጅግ አስቸጋሪ ነው። ሁሉም ነገር ባልተሟላበት ክፍል ውስጥ ገብቶ የሚማር ተማሪም በእያንዳንዱ ነገር ትኩረቱ ስለሚሰረቅ የሚፈለገውን ያክል እውቀት መያዝ አይችልም" ትላለች መምህርቷ።
በአካባቢው አሁንም ለውጥ የለም፤ ብዙዎቹ በዳስ ትምህርት ቤቶች መማራቸው አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።
አስተማሪዎቹም ቢሆን የሚመችና በቂ ማረፈያና ቢሮዎች እንደሌላቸው መምህርት ሙሉብርሀን ትገልጻለች።
"በረሃ ላይ ለአምስት አመታት አስተምሬያለሁ። ሁለት ህንጻና አንድ የአስተማሪዎች ጽህፈት ቤት አለ። ከዛ ውጪ በየአመቱ እየፈረሰና ኗሪዎች እያደሱት የምናስተምርባቸው የዳስ ክፍሎች ናቸው ያሉት"።
የሑመራ አካባቢ ጸሐይና ሙቀት የሚበረታበት ስለሆነ፤ ተማሪዎቹ ድንጋዩን በጭቃ እየቀቡ ለመማር እንደሚጥሩ አስተማሪዋ ትናገራለች።
በዚህ ምክንያት ከአንድም ሦስቴ በምታየው ነገር ጭንቀት ይፈጥርባት እንደነበረ ገልጻለች።
"በዚህ ሁኔታ አይደለም ርእሰ መምህርትና አስተማሪ ሆኜ አንድም ሌሊት የማሳልፍ አይመስለኝም ነበር። በጊዜ ሂደት ግን ከህብረተሰቡ አልበልጥም ብዬ ተቀበልኩት" ብላለች።
በጊዜው ምንድን ነው የማስተምረው? በሚል ሃሳብ ትጨነቅ እንደነበረ የምትናገረው መምህርት ሙሉብርሃን፡ "ምቾት በሌለበት የምትሰራው ሁሉ እርካታ የለውም" ስትል ሁኔታውን ትገልጻለች።
"በዚህ ተስፋ ቆርጠው ወደ ውጪ የሄዱ አሉ"
ትምህርት ሲነሳ በቀዳሚነት ስሟ ከሚጠቀሰው አገር መካከል አንዷ ሲንጋፖር ነች።
ሲንጋፖር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እንደ ሃገር በአንድነት እንትድጠነክር ካደረጓት ነገሮች መካከል አንዱ ትምህርት ነው።
አገሪቷ ለአስተማሪዎች ባላት ትኩረት በትምህርት፤ በተለይ ደግሞ በሒሳብና በሳይንስ በቀዳሚነት የምትጠራ ሲሆን በቆዳ ስፋት ትንሽ ብትሆንም በትምህርትና እውቀት ግን ታላላቅ አገሮችን እየመራች ነው።
በሲንጋፖር በትምህርት ጉዳይ ቀልድ የለም፤ ወላጆች የልጆቻቸውን የእውቀት ደረጃ የማይገነቡ እና ደረጃውን ወደ ጠበቀ ትምህርት ቤት የማይልኩ እንደሆነ፡ በህግ ስለሚጠየቁ ጠንቃቃ ናቸው።
ሲንጋፖር ለአስተማሪዎች ክብር ከሚሰጡት 10 የዓለማችን አገራት መካከል አንዷ ስለሆነች፤ ወላጆች ልጆቻቸውን መምህር እንዲሆኑ ያበረታታሉ።
ሙሉብርሃንም፤ "ፈጣሪም እንኳ መምህር ስለሆነ 'ረቡኒ' አይደል የሚሉት? እኔም ትልቅ ክብር እየሰጠሁት መምህርት እንድሆን እየተመኘሁ አደግኩ" ስትል፤ የ20 አመት ወጣት ሆና ማስተማር እንደጀመረች ገልጻለች።
"አዲስ ሆኜ ስቀጠር ከአንድ እስከ ስምንተኛ አስተምራለሁ። ተማሪዎች አይደለም ወንበር የሚጽፉበት ጥቁር ሰሌዳ የላቸውም። ይሄንን ሳይ ተስፋ እቆርጥ ነበር፤ እነሱ ግን በጭንቅ ነጭ ጨርቅ ላይ ጥቁር ቀለም ቀብተው ያዘጋጁ ነበር" ብላለች።
በዚህ ምክንያት ብዙ ህጻናትና ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንደሚያቋርጡ የምትናገረው መምህርት ሙሉብርሃን፤ "ምንም ነገር በሌለበት አካባቢ የሚፈለገው ርቀት መጓዝ አትችልም። ለዚህ ነው የተማርኩት? ብለው ተስፋ በማጣት ወደ ውጪ የሄዱ አሉ፤ እንደ ሁኔታው ብለው የቀጠሉም አሉ" ስትል የሁኔታው አስከፊነት ትገልጻለች።
ይሄንን፡ አስተማሪዎች ተገቢውን መልእክት ለማስተላለፍ ስለማያበረታታቸው፤ ደስተኛና ጠንካራ ትውልድ ማነጽ ላይ ተጽእኖ ያሳድርባቸዋል።
"አንድ ቀን ሱፐርቫይዝ [ክትትል] ላደርግ ወደ አንድ ዳስ ገባሁ። አስተማሪው እያስተማረ እያለ በመሃል ከብቶች እየተጋፉ ገቡ። ሌሎች የበረሃ እንስሳትም ይመጣሉ። ይህ ልጆቹ ላይ የሚፈጥረው ድንጋጤና የትምህርት ሰአት መስተጓጎል ቀላል አይደለም" ስትል ከገጠመኞቿ አንዱን ታወሳለች።
መምህርት ሙሉብርሃን ባለው የትግራይ የትምህርት ሁኔታ ደስተኛ ባትሆንም "ቤት ያፈራውን ስለምትጠቀም፣ ባለው ሁኔታ እየሰራን መጥተናል። ግን በዚህ ሁኔታ መቀጠል የለበትም" በማለት ነገ የተሻለ ይሆን ዘንድ ተስፋ ታደርጋለች።