ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሕንድ ውስጥ ከ2.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያውጣ ኮኬይን ተያዘ
የሕንድ ባለሥልጣናት ጉጃራት በምትባለው ግዛት ወደ 3ሺህ ኪሎ ግራም የሚመዝን ኮኬይን የተባለውን አደንዛዥ ዕጽ መያዛቸውን አስታወቁ።
ይህ በጉጃራት በሚገኝ ወደብ ላይ የተያዘው ከፍተኛ መጠን ያለው ይህ ኮኬይን ለገበያ ቢቀርብ ከ2.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያወጣል ተብሏል።
ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሁለት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው እና በርካታ ሰዎች ላይ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑም ተነግሯል።
የኮኬይኑ መነሻ አፍጋኒስታን መሆኑ የተነገረ ሲሆን፤ በይፋዊ ሰነዶች ላይ እቃው 'ታልክ' የተሰኘ የማዕድን ድንጋይ መሆኑ ነበር የተመለከተው።
ዕጹ በቅድሚያ ከአፍጋኒስታን ወደ ኢራን ከተጓጓዘ በኋላ ነበር በሕንድ ጉጃራት ሙንደራ ወደብ የተያዘው።
የሕንድ የገቢዎች ደኅንነት ዳይሬክቶሬት እንዳለው ከሆነ፤ ኢራን ከሚገኘው ባዳር አባስ ወደብ አደንዛዥ ዕጹ ወደ ሕንድ መላኩን የሚጠቁም መረጃ ደርሶን ነበር ብሏል።
ዳይሬክቶሬቱ እቃውን ወደ ሕንድ ያስገባው ተቋምም በሕንድ የሚገኝ ኩባንያ ስለመሆኑ የቀደመ መረጃ እንዳለ አመልክቷል።
"ባለሙያዎቻችን እቃውን በቁጥጥር ሥር አውለው ምርመራ ሲያደርጉ፤ በኮንቴነሮቹ ውስጥ ዕጽ ተገኝቷል። ኮኬይን መሆኑም ተረጋግጧል" ብሏል ዳይሬክቶሬቱ በመግለጫው።
ባለሥልጣናት እንዳሚሉት ከሆነ ከአደንዛዥ ዕጹ ዝውውር ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በመዲናዋ ዴልሂ ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ዘመቻ መካሄዱን አስታውቀዋል።
"እስካሁን የተካሄዱ ምርመራዎች በቁጥጥር ስር ላይ ያሉት የአፍጋኒስታን ዜጎች በዕጹ ዝውውር ውስጥ መሳተፋቸውን አሳይቷል" ብሏል ኤጀንሲው።
ኮኬይንን ጨምሮ በርካታ አደንዛዥ ዕጾችን ለማምረት የሚውለው ኦፒየም ፖፒይ የተባለውን ተክል በማምረት አፍጋኒስታን ቁጥር አንድ አገር ነች።
እንደ ተባበሩት መንግሥታት የዕጽ እና ወንጀል ቢሮ መረጃ ከሆነ ለዓለም ገበያ ከሚቀርበው የኦፒየም ምርት 80 በመቶው የሚመረተው በአፍጋኒስታን ነው።