መስከረም 20 ለሚደረገው ምርጫና ሕዝበ ውሳኔ 7.6 ሚሊዮን ሰዎች ተመዝግበዋል ተባለ

በተራዘመውና መስከረም 20 ሊካሄድ በታቀደው ምርጫና ሕዝበ ውሳኔ ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር 7.6 ሚሊዮን መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

ምርጫው የሚካሄድባቸው በሶማሌ፣ በሐረሪ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ሲሆን በዚሁ ዕለትም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ ይካሄዳል።

ስድስተኛው አጠቃላይ ብሔራዊ ምርጫ በዋናነት ሰኔ 14/2013 ዓ.ም የተካሄደ ቢሆንም በፀጥታ ችግር፣ በመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ በታዩ ግድፈቶች፣ በመራጮች ምዝገባ ላይ የቀረቡ አቤቱታዎችን ለማጣራት ጊዜ በማስፈለጉ የድምፅ መስጫው ቀን በአንዳንድ ክልልሎችና የምርጫ ክልሎች እንዲራዘም መወሰኑ ይታወቃል።

መስከረም 20 የሚካሄደው ምርጫ ለ47 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ሲሆን 105 ምርጫ ክልሎች ላይ እንደሚከናወንም ተገልጿል።

በእነዚህ ምርጫዎች የሚሳተፉት 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን አቅርበዋል።

ለዚህም ምርጫ 7 ሺህ 54 ምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ የሚሰጥባቸው መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን 30 ሺህ የሚጠጉ ምርጫ አስፈፃሚዎችም ተዘጋጅተዋል።

ከመስከረም 8 ቀን 2014 ጀምሮ የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶች ስርጭት የተጀመረ ሲሆን እስከ መስከረም 12 ድረስም እንደሚጠናቀቅ ቦርዱ ገልጿል።

ምርጫ ቦርድ መስከረም 20 የሚደረገውን የድምፅ አሰጣጥ አስመልክቶ ባደረገውም ዝግጅት ለምርጫ ክልል አስፈጻሚዎች የክለሳ ስልጠና እና ለምርጫ አስፈፃሚዎች ደግሞ የመራጮች ምዝገባን አስመልክቶ እና የድምፅ መስጫ ቀንን እንዲሁም የሕዝበ ውሳኔ አፈፃፀምን አስመልክቶ ስልጠናዎችን መውሰዳቸውን አስታውቋል።

በአጠቃላይ ከ26 ሺህ በላይ አስፈፃሚዎች መሳተፋቸውም ተመልክቷል።

የመራጮች ምዝገባ በተቋረጠባቸው እና ባልተጠናቀቀባቸው ቦታዎች ምዝገባው ከነሐሴ 26 ጳጉሜ 05 ቀን ድረስ የተከናወነ ሲሆን ተጨማሪ አንድ ቀን የመራጮች ለመራጮች ምዝገባ ተከናውኗል።

በሶማሌ ክልል በሰባት ምርጫ ክልሎች ላይ በድጋሚ የመራጮች ምዝገባ የተከናወነ ሲሆን ይህም ውሳኔ ቦርዱ ባሰማራው አጣሪ ቡድን ላይ መስረት በማድረግ መሆኑ ተገልጿል።

ምርጫ ያልተደረገበት የሶማሌ ክልልንም በተመለከተ የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ በነበረበት ወቅት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ለቦርዱ አቤቱታ ቀርቦ ነበር።

ከሰሞኑ የሶማሌ ክልል ምርጫ ላይ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ከመራጮች የምዝገባ ሂደት ማጭበርበር የተሞላበት እንደሆነና ሌሎች ችግሮችን በተመለከተ ለምርጫ ቦርድ አቅርቦት የነበረው አቤቱታ መፍትሄ ባለማግኘቱ ከምርጫው ራሱን ማግለሉን ባለፈው ሳምንት አስታውቋል።

በመስከረም 20ው ምርጫ በአማራ ክልል የተወሰኑ ቦታዎች ምርጫው አይካሄድም።

ምርጫ በተራዘመባቸው አጣዬና የሰሜን ሸዋ 10 በሚደርሱ ቦታዎች ካለው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ምዝገባ ባለመከናወኑ መስከረም 20/2014 ምርጫ እንደማይካሄድ ተገልጿል።

በድሬዳዋ ሁለት የምርጫ ጣቢያዎች ምርጫው ድጋሚ እንዲደገም ከዚህ ቀደም ቢወሰንም አሁንም ያለው የደኅንነት ስጋቱ ባለመቀረፉ ልዩ ውሳኔ ያስፈልገዋል ተብሏል።