የዲያቆን ዳንኤል ንግግር 'አደገኛ ትርክት' ነው ስትል አሜሪካ ማውገዟ ተገለጸ

ከሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የትግራይ ኃይሎችን በተመለከተ በአንድ ስብሰባ ላይ የሰጡትን አስተያት አሜሪካ ማውገዟን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ።

"እንደዚህ ያለ የጥላቻ ትርክት አደገኛ እና ተቀባይነት የለውም" በማለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በትናንትናው ዕለት መተቸተቻውን የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ዘግቧል።

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙ ሲሆን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ቦርድ አባልም ናቸው።

ከዚህ ቀደም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዘር ጭፍጨፋ አማካሪ እንዲሁም የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) ኃላፊ ሰማንታ ፓወር በትግራይ ጦርነት ሰብዓዊነትን ዝቅ የሚያደርጉ ጥላቻን የሚሰብኩ ትርክቶችና ቃላቶች መጠቀማቸው ስጋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

ነገር ግን የዲያቆን ዳንኤል ክብረት አስተያየት በአሜሪካ መንግሥት ትኩረት አግኝቶ ትችት ሲቀርብበት የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

የአማራ ከልል ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት አንድ ዝግጅት ላይ ዲያቆን ዳንኤል "እነሱ" ብለው የጠሯቸውን አካላት "ከምድረ ገጽ ብቻ ሳይሆን ከሰዎች ህሊናም እንዲጠፉ" ሲናገሩ ተሰምተዋል።

በኤኤፍፒ ዲያቆን ዳንኤል አስተያየታቸውን እንዲያብራሩ የተጠየቁ ሲሆን በመልዕክት በሰጡት ምላሽም "እነሱ የሚለው የሚያመለክተው ህወሓት የሚለው አሸባሪ ቡድኑን ነው" ሲሉ አስተባብለዋል።

ግሎባል ሴንተር ፎር ዘ ሪስፖንሲብሊቲ ቱ ፕሮቴክት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሲሞን አዳምስ ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት የዲያቆን ዳንኤል ንግግር "በእውነት የሚረብሽ እና ጥንቃቄ የጎደለው ነው" ብለዋል።

አክለውም "በኢትዮጵያ ውስጥ በብሔር የሚከሰቱ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ መበራከታቸውን ከማየት አንፃር ዳንኤል በአጠቃላይ ከትግራይ ተወላጆች ይልቅ ስለ ህወሓት ብቻ ነው የሚናገረው የሚለውን ለመገመት ከባድ ነው" ብለዋል።

ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ የፌደራል መንግሥት ባለስልጣን ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት ዳንኤል "የግል ስሜታቸውን ነው" በማለት የተናገሩ ሲሆን ሁሉም የትግራይ ተወላጆች ሊጠፉ ይገባል አላሉም በማለት አፅንኦት ሰጥተዋል።

በጥቅምት መጨረሻ በትግራይ ከልል የተከሰተው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፈናቅሏል እንዲሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም በረሃብ አፋፍ ላይ ናቸው።

ጦርነቱ ወደ አጎራባቾቹ አማራና አፋር ክልልም ተዛምቶም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አፈናቅሏል።

በትግራይ ክልል በከፋው ረሃብ ምክንያት ሰዎች አረንጓዴ ቅጠሎችን ለመብላት መገደዳቸውን ኤሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

ባለፈው ሳምንት በአንድ የጤና ማዕከል አንዲት እናትና 0.77 ግራም የምትመዝን ጨቅላ በረሃብ ሞተዋል። አንድ የእርዳታ ቡድን በሚሰራበት ከ20 በላይ በሆኑ ወረዳዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች በረሃብ መሞታቸው ተዘግቧል።