ከችግር ወደ ችግር የሚገላበጡት በደቡብ አፍሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያን

ከሳምንታት በፊት የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ጃኮብ ዙማ እስርን ተከትሎ በመላው አገሪቱ የተቃውሞ ሰልፎች ተቀስቅሰው ነበር።

ፖሊስ እንደሚለው በጃኮብ ዙማ የትውልድ ቦታ ክዋዙሉ-ናታል ተቀስቅሶ በመላው አገሪቱ የተስፋፋውን አለመረጋጋት ወንጀለኛ ቡድኖች መጠቀሚያ አድርገውት ነበር።

ዘረፋ ተፈጽሞባቸዋል በተባሉ ስፍራዎች ፖሊስ ምላሽ ሲሰጥ በርካታ ሰዎችም በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ይፋ አድርጓል።

ይህን ተከትሎ ኑሮዋቸውን በደቡብ አፍሪካ ያደረጉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተጎጂ ሆነዋል።

ይሄው ተጽዕኖ ከሳምንታት በኋላም ቀጥሏል።

'ከዜሮ መጀመር ነው'

አሰግድ ዮሐንስ ደቡብ አፍሪካን ከረገጠ ዘጠኝ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ደርባን ዙሪያ በምትገኘው ክዋዙሉ ናታል የወንድ እና የሴት ልብሶች እንዲሁም ጫማዎችን ይሸጥ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግሯል።

እርሱ በሚኖርበት አነስተኛ ከተማ ላይ አራት ኢትዮጵያውያን ብቻ ይኖራሉ። የቀድሞው ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ መታሰራቸውን በመቃወም ተነስቶ በነበረው ነውጥ የሁለቱ ንብረት ሙሉ በሙሉ ሲወድም የሁለቱ መትረፉን ይናገራል።

አንድ ዓመት ከሠራ በኋላ ያለውን ጠቅልሎ ንብረቱን ሸጦ አዲስ አበባ ተመልሶ የመሥራት ሃሳብ የነበረው አሰግድ አሁን ግን ያንን ማድረግ ከባድ መሆኑን ይናገራል።

አሰግድ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ባደረገበት ወቅት ጆሃንስበርግ ከጓደኞቹ ጋር እየኖረ ነው።

"ከተማውን ለቅቄ ወጥቻለሁ፤ በመደብርህ የነበሩ ልብሶችን ሰዎች ለብሰው ማየት ይረብሻል። ለዚያ ነው ወደ ጆሃንስበርግ የመጣሁት" ሲልም ለቢቢሲ ተናግሯል።

የነበረው ንብረት ሙሉ በሙሉ መዘረፉን እና ይህም ከአንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ ራንድ በላይ እንደሚገመት አብራርቷል።

አሰግድ እንደሚኖርበት ባሉ አነስተኛ የደቡብ አፍሪካ ከተሞች ውስጥ ያሉ የሌላ አገር ተወላጆች በቁጥር ጥቂት በመሆናቸው ንብረታቸውን ተባብረው ለመታደግ አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል።

አሰግድ ከዚህ በፊት እንደዚህ አይነት ጥቃት ሦስት ጊዜ እንዳጋጠመው ያስረዳል።

በደቡብ አፍሪካ እንዲህ ዓይነት መጤ ጠል ጥቃቶች ሲደርሱ እንቅስቃሴዎች እንደሚገደቡ፣ የንግድ ተቋማትን መክፈት እንደማይቻል እና ከቤት መውጣትም ፈታኝ መሆኑን ይናገራል።

በተለያየ ጊዜ መብራት እና ውሃ ተቋረጠብን ከሚል ተቃውሞ ጀምሮ በመጤው ላይ ጥቃት ወደ ማድረስ የሚሸጋገሩ ግጭቶች ተፈጥረው እንደነበር ያነሳል።

ተቃውሟቸውን ለማሰማት የሚወጡ ሰዎች በስተመጨረሻ ንግድ ቤቶችን ዘርፈውና አውድመው መሄድ የተለመደ ነው ይላል።

በአወሮፓውያኑ 2018 የተቃውሞ ሰልፍ ሲነሳ "ዙማ ከስልጣን ይውረድልን" የሚል ጥያቄ እንደነበራቸው የሚያስታውሰው አሰግድ፣ በዚህም የተነሳ በርካታ ስደተኞች ተዘርፈዋል።

አሁን በአውሮፓውያኑ 2021 ደግሞ ሌላ ርዕስ ይዘው ብቅ አሉ- ዙማ መታሰር የለበትም የሚል።

የአሁኑ ግጭት ከሌላው ጊዜ መጠነ ሰፊ እና የተለየ እንደነበር ይናገራል።

በዚህ ዘረፋ እና ውድመት ከ150 ሺህ በላይ ደቡብ አፍሪካውያን ሥራ አጥ ሆነዋል የሚለው አሰግድ፣ በቢሊዮን ዶላሮች የሚገመት ንብረት ወድሟል ሲል ሁኔታውን ይገልፀዋል።

"እኔ ጋር ብቻ ይሠሩ የነበሩ ስድስት ደቡብ አፍሪካውያን ሥራ ፈትተዋል" ይህ ቁጥር ደግሞ በትልልቅ የገበያ አዳራሾች ሲታይ ከፍተኛ ቁጥር እንደሚኖረው ያብራራል።

አንዳንድ እስከ 300 ሠራተኞች ያስተዳድሩ የነበሩ ትልልቅ የገበያ አዳራⶄች ከ20 ሚሊዮን ራንድ በላይ የተዘረፈባቸው ግለሰቦች መኖራቸውን የሚያነሳው አሰግድ "እነርሱ መልሰን አንከፍትም" እስከማለት መድረሳቸውን ይናገራል።

አሰግድ ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ ስገነባ የመጣሁት ነው የሚለው ሱቁን በደረሰበት ዘረፋ ሙሉ በሙሉ ወድሞ ማየቱ መንፈሱን ሰብሮታል።

የተፈጠረው ሁኔታ ገና እግሩ ደቡብ አፍሪካን በረገጠበት ወቅት ሲመጣ እንደነበረው ባዶ እጁን እንዲሆን እንዳደረገው ይናገራል።

"ከዜሮ ነው የምትጀምረው፤ ስትገባ ምንም አልነበረህም እንደዚያ ማለት ነው"

መንግሥት በዘረፋ ጉዳት ለደረሰባቸው እንግዶች ካሳ እሰጣለሁ ሲል ቃል ቢገባም "ግፋ ቢል ቢሰጡ ለዜጎቻቸው እንጂ ለስደተኞች የመስጠት እድሉ አነስተኛ ነው" ይላል።

አሁንም ደኅንነት የማይሰማቸው ስደተኞች መኖራቸውን የሚያነሳው አሰግድ፣ ተመሳሳይ ጥቃት በድጋሚ ስላለመፈጠሩ ዋስትና የለም ብሏል።

"አንዳንዶች መልሶ ለመክፈት ጥረት እያደረጉ ነው" የሚለው አሰግድ የራሱን ሁኔታ ሲያስረዳም፣ በሃሳብ ደረጃ ወደ ሥራ ለመመለስ ቢፈልግም ጊዜው ከባድ መሆኑን ይናገራል።

በቀጣይ የቤት ኪራይ ከፍሎ፣ ራስን መመገብ እና ሥራ መጀመር ፈታኝ ነው የሚለው አሰግድ፣ "በደረሰው ጉዳት እንደድሮው መኖር እንደማልችል ሳየው ጉዳቱ ዘላቂ ነው እላለሁ" በማለት ያስረዳል።

በግጭቱ ወቅት አብዛኛው ሰው በመዘረፉ አንዱ ለአንዱ ለመድረስ የሚያስችል ሁኔታ አለመኖሩ ደግሞ የበለጠ ህይወትን ፈታኝ አድርጎታል።

"ሁለት ሦስት የተዘረፈ አለ፤ ሰፈር ውስጥ ዘጠኝ አነስተኛ ሱቆች የነበረው እና ሙሉ በሙሉ የተዘረፈበት አለ" የሚለውን ጠቅሶ ይህም ከዚህ በፊት የነበረውን የእርስ በእርስ የመረዳዳት ባህል አዳጋች እንዳደረገው ይናገራል።

መልሶ ለመቋቋም ሁኔታዎች ፈተና መሆናቸውን የሚያስረዳው አሰግድ ነግዶ ወዳተረፈባት ከተማ ስለመመለስ ሲጠየቅ ". . .የማይሆን ከሆነ ላልመለስም እችላለሁ" ብሏል።

"ሱቅህም ከቃጠለ ተቃጠለ ነው. . . ከተዘረፈም ተዘረፈ ነው"

ጆሃንስበርግ ውስጥ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት ወ/ሮ መዓዛ ተስፋዬ በበኩላቸው ረብሻው መቀስቀሱን ተከትሎ በጣም አሳሳቢ እና አስፈሪ ሁኔታ ተከስቶ እንደነበር በወቅቱ ለቢቢሲ ገልዋጸል።

ችግሩን ተከትሎ ለቀናት ሱቆችን ጨምሮ ማንኛውም እንቅስቃሴ ቆሞ እንደነበር አጫውተውናል።

"እኛ አካባቢ ያኔ መጥተው ለዘረፋ ሲዘጋጁ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ስደተኞቹ ተባብረው እንዳባረሯቸው በዚያው እንቅስቃሴያቸው ቆመ" ብለዋል።

በአካባቢያቸው ከዚያ ወዲህ ምንም አለመፈጠሩንም ይገልጻሉ።

"አሁን በጣም ተረጋግተን እየሠራን ነው። በአጠቃላይ ምንም ነገር የለም። ሁልጊዜ የሚከሰት ዝርፊያ አንዳንድ ሌቦች በየሱቁ የሚገቡት ካልሆነ በስተቀር ምንም ነገር የለም" ሲሉ አሁን ያሉበትን አጋርተውናል።

በሌሎች አካባቢዎችም ሰዎች ወደ ሥራ መመለስ መጀመራቸው እንደሰሙም አጫውተውናል።

"በዚህ አገር እርስ በእርስ ካልተረዳዳን በስተቀር በመንግሥት በኩል የሚደረግ ነገር የለም። ሱቅህም ከተቃጠለ ተቃጠለ ነው ምንም የሚደረግ ነገር የለም። ከተዘረፈም ተዘረፈ ነው። እርስ በእርስ ከመረዳዳት ውጪ በመንግሥት በኩል የሚደረግ ነገር የለም" ብለዋል።

አሁን አካባቢው ሠላም መሆኑን ጠቅሰው በተረጋጋ ሁኔታ መሥራት መጀመራቸውን ገልጸዋል። ሥራውን ግን ከበፊቱ መቀዝቀዙን ያስረዳሉ።

ምክንያቱ ደግሞ የኮሮና ወረርሸኝ ነው። "በዘመኑ ካለው የኮሮና ሁኔታ መቀዛቀዝ ውጪ በተረጋጋ ሁኔታ እየሠራን ነው" ብለዋል።

"ተስፋ የሚያስቆርጥ የጨለማ ጊዜ"

ከ17 ዓመት በላይ በደቡብ አፍሪካ እንደኖሩ የሚናገሩት አቶ ግርማ ፊጣ መኖሪያቸውን በጃኮብ ዙማ የትውልድ ስፍራ ክዋዙሉ-ናታል ዋና ከተማ ፒተማርስበርግ ነው።

ባለፈው ጊዜ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተዘርፈዋል ይላሉ።

"በተለያዩ አካባቢዎች ሱቃቸው ተዘርፏል ብዙ ሰዎችም ሥራ አጥተው ነበር። ብዙ ችግር ውስጥ ነበሩ" ሲሉ ይገልጻሉ።

የአካባቢው ማኅበረሰብ መሪ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ግርማ ችግሩ ቀደም ሲል በደቡብ አፍሪካ ሲከሰት ከነበረው ዜኖፎቢያ (መጤ ጠል) እንቅስቃሴ የሚበልጥ መሆኑን በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ቀደም ሲል መጤ ነበረው የሚባሉት ላይ ያነጣጠረው ጥቃት እና ዝርፊያ መሆኑን ገልጸው በዚህኛው ግን ሁሉንም ያማከለ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

"የእኔ ሦስት ሱቅ ተዘርፏል" ሚሉት አቶ ግርማ "አንደኛው ሱቅ 1.8 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ እያንዳንዳቸው 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው" መሆኑንና መዘረፋቸውን በወቅቱ ጠቅሰዋል።

ከከተማው ዳርቻ ያሏቸውን ሱቆች ዝርፊያን 'ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው' ብለዋል።

"በሰዓቱ የነበረው ነገር ተስፋ የሚያሳጣ ነው። ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት እንዴት እንደምንኖር እንድናስብ፣ እንድንጨነቅ ያደረገን ነው። ደስተኞች አይደለንም። አሁን ብቻ አይደለም ከዚህ በፊት በነበሩት ጊዜያትም በጣም በጣም ተጎድተን ተዘርፈን ነው ሠርተን ያገኘነው። . . . የባለፈው ግን ተስፋ የሚያስቆርጥ የጨለማ ጊዜ ነበር። በጣም በጣም መጥፎ ሰዓት ነበር" ሲሉ ይገልጻሉ።

ከሳምንታት በኋላ ሰው ተረጋግቶ ወደ ሥራ ተመልሷል የሚሉት አቶ ግርማ አልፎ አልፎም ቢሆን የሚያጋጥማቸው ችግር መኖሩን ያስረዳሉ።

"የገጠመን ችግር መልሶ ዕቃ ማስገባት፣ ሱቆችን መክፈት አትችሉም የሚል ነው። አንዳንድ የሱቅ ባለቤቶች (አከራዮች) 'ይዘረፋል፣ ይቃጠለላል' በሚል ነው ሁለተኛ እንዳይከፈቱ የከለከሉት" ብለዋል።

ግልጽ የሆነ ችግር ባይሆንም "በአንዳንድ የማኅበራዊ ድር አምባ ግሩፖች ላይ ልቀቁልን፣ እንዘርፋለን ስደተኛ ሱቅ መክፈት አይችልም፣ ቢዝነስ መሥራት አይችልም የሚል የተለያየ ምንጩ የማይታወቅ ነገር ይጻፋል" ይላሉ።

በተለያዩ ቦታዎች ሱቆች የነበራቸው አቶ ግርማ "በፈጣሪ እርዳታ" ጥበቃ ቀጥረው እና በአካባቢው ያሉትን ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር ከተማ የሚገኘውን ሱቅ ማትረፍ መቻላቸውን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

እሳቸውም ቢሆኑ ሙሉ ለመሉ ወደ ሥራ አልገቡም።

"ከከተማ ውጪ (ሎኬሽን እያሉ ይጠሩታል) ያለው ተዘርፏል። ያንን ግማሹን አስገብተናል። የተበላሹ ነገሮች ስላሉ እሱን እያስተካከልን ነው።"

የእሳቸው ሥራ በዚህ መልኩ እየዳኸ ሲሆን ሌሎችም ሥራቸውን ለመጀመር ደፋ ቀና እያሉ ነው።

"ባለሁበት ከተማ የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ሰብሳቢ ነኝ። ከአንዳንድ ድርጅቶች እና ሰዎች በጣም ለተጎዱ 85 ሰዎች እንደገና [ሱቅ] እንዲከፍቱ ብድር አመቻችተናል። አንዳንዶች ሥራ የጀመሩሲሆን ብዙዎች ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ አልጀመሩም። አንዳንዶች በብድር፣ ያለው ደግሞ ለሌለው በመደጋገፍ እና በመበዳደር ሥራ በመጀመር ላይ ነን" ይላሉ።

በጉዳቱ ወቅት የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደር፣ ሚሲዮኑ እና ሚዲያዎች ተገኝተው መጎብኘታቸውን እና "ከዚያ ውጭ ግን ምንም" አለመደረጉን ያስረዳሉ።

በዚህ ረገድ ደቡብ አፍሪካዊያን ዜጎች ከዚህ የተለየ ድጋፍ እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

"[የደቡብ አፍሪካ] መንግስት ለዜጎቹ ካሳ እከፍላለሁ ብሏል። የእኛ ሰው በብዛት እንደሚታወቀው ስደተኛ ነው። ፈቃድ ማውጣት ብዙ ፕሮሰስ ስለሚጠይቅ የእኛ ሰው ያለ ፈቃድ ነው ሥራ የሚሠራው። ስለዚህ እኛን የሚረዳ ሥርዓት የለም። ለዜጎቹ ካሣ ይከፍላል ይባላል። ለእኛ ግን ምንም የለም" ሲሉ አጠናቀዋል።

"ወረቀት የሌላቸውንም ሰዎች እየያዙ ነው"

ከ15 ዓመት በላይ በስደት ነው የኖርኩት የሚለው ኮስሞስ ገብረሚካኤል የደርባን ነዋሪ ነው።

ባለፈው በደቡብ አፍሪካ ከተነሳው አመጽ እና ረብሻ ትልቁ የሚባለው በደርባንና አካባቢው መከሰቱን በወቅቱ ገልጾ ነበር።

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን በንግድ ሥራ መሠማራታቸውን ገልጾ በተለያየ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ያስረዳል።

የመጀመሪያዎቹ 'ሎኬሽን' በሚባሉ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚኖሩበት አካባቢዎች የሚሠሩ ናቸው። እነዚህ አካባቢዎች ላይ የሚሠሩ ኢትዮጵያውያን "ሙሉ ለሙሉ ንብረታቸው ወድሟል" ብሏል ኮስሞስ ለቢቢሲ።

በሎኬሽን ለሚሠሩ ነጋዴዎች ዕቃዎችን በማቅረብ እና በማከፋፈል የሚሠሩ ኢትዮጵያውያን በሁለተኛው ምድብ ሲገኙ ሆቴሎች፣ የባህል ልብስ መሸጫዎች እና ግሮሰሪዎችንም ያቀፉ ናቸው።

እነዚህኛዎቹ ደግሞ ቀደም ሲል መጤ ጠል [ዜኖፎቢያ] ጥቃቶች በደረሱበት ወቅት በመማራቸው አብዛኛዎቹ ራሳቸውን ለመጠበቅ ተደረጅተው በመንቀሳቀሳቸው የደረሰባቸው ጉዳት አነስተኛ ነው ይላል።

አቅም ያላቸው እና በሦስተኛው ምድብ የሚገኙት ኢትዮጵያዊያን ደግሞ የንግድ እንቅስቃሴያቸውን የሚያደርጉት በትላልቅ የንግድ ማዕከላት [ሞሎች] ውስጥ ሲሆን "እነዚህ ሙሉ ለሙሉ ንብረታቸውን ያጡበት ሁኔታ ነው ያለው" ብሏል።

ከዚያ በኋላ ስለተከሰተው ሲናገር ለደኅነነት ይሁን በስጋት ባላወቀው ምክንያት ሙላዚ አካባቢ የሚገኙ ባለሱቅ ኢትዮጵያውያን በሕገ ወጥ መንገድ ለሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ገንዘብ እንደሚከፍሉ ያስረዳል።

"እነዚህ ወንበዴዎች ራሳቸውን እንደቢዝነስ ማኅበር አደራጅተው ባለፈው የነበረውን ዝርፊያ በመጠቀም 'ሃበሾቹን' (ኢትዮጵያውያንን) ለኅብረተሰባችን ደኅንነት ለዘለቄታዊ መፍትሔ ሲባል ተመልሳችሁ ሱቃችሁን እንዳትከፍቱ ብለው ሱቆችን የመንጠቅ አዝማሚያ አሳይተዋል። በኋላ ላይ ግን ችግሩ ተፈቶ ወደ ሥራ ጀምረዋል። እነዚህ ወንበዴዎች ተከፋዮች ናቸው። ለእኛ ኮሙኒቲ ሁሌም ሁሌም ስጋት ናቸው" በማለትም ይናገራል።

ወንበዴዎቹን ማበረታታትም ሆነ ፈርቶ አገልግሎት ማግኘት ተገቢ ይመስለኝም የሚለው ኮስሞስ ኅብረተሰቡም እንደዚህ አይነት ነገር ማቆም አለበት ብሏል።

ከተከሰተው አለመረጋጋት በኋላም በየመንገዱ ወታደሮች እና ፖሊሶች እየቆሙ መሆኑን ጠቅሶ በተለይም ጆሃንስበርግ፣ ፍሪስቴት እና ክዋዙሉ ናታልን የሚያገናኙት ዋና ዋና መንገዶች ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል።

ዓላማቸው ደግሞ መንገድ ዘግተው የተሰረቁ ዕቃዎች ካሉ ከአንዱ ግዛት ወደ ሌላው እንዳይሸጋገር ለመከላከል ነው።

"ነገር ግን ወረቀት የሌላቸውንም ሰዎች እየያዙ ነው። ብዙ ኢትዮጵያውያን ወረቀት ስለሌላቸው በዚህ ምክንያት ችግር እየገጠማቸው ነው። ወደ አካባቢዎቹ እየሄድን ችግሩን ለማስቀረት እየጣርን ነው" ብሏል ኮስሞስ።

ካሉት ውጣ ውረዶች ውጪ አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን "ከሞላ ጎደል ሥራ ጀምረዋል። ለዚህ ደግሞ ያላቸውን ሃብት ተቀጠቅመው እና ኅብረተሰቡም የሚችለውን ድጋፍ አድርጓል" ብሏል።

"ደርባን ለተዘረፉ እና ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ከሚሊዮን ራንድ በላይ በማዋጣት ሰዎቹን ዳግም ወደ ሥራ ተመልሰዋል።"

እንደ ወ/ሮ መዓዛ ሁሉ ኮስሞስም ሥራ ላለፉት ሁለት ዓመታት አመርቂ የሚባል አይደለም ሲል ሃሳቡን ይጋራል።

"የኮቪድ ሁኔታ ብዙም ደስ የሚል ድባብ አልፈጠረም። ሥራ ቀዝቅዟል። ክለብ እና ቡና ቤት ያላቸው ኢትዮጵያውያን አሉ። እነሱ ሥራ ካቆሙ ሁለት ዓመት ሊሆናቸው ነው። ከሠርግ ጋር በተያያዘ ሥራ የሚኖሩም ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ከሥራ ውጪ ሆነዋል" ብሏል።

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር በችግሩ ወቅት መጥው ነበር የሚለው ኮስሞስ ያለውን ነገር ኅብረተሰቡን አነጋግረው እንደነበነር ያስታውሳል። "ከማነጋገር እና ሞራል ከመስጠት ውጪ ግን ድጋፍ የለም።"

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት የተመደበ በጀት በመኖሩ ገንዘብ እንከፍላለን ማለታቸውን አስታውሶ "ብዙ ጊዜ መንግሥት ለውጪ ዜጎች ቃል እየገባ የማይተገበርብት ሁኔታ ነው ያለው። ኅብረተሰቡ የተዘረፈ፣ የተቃጠለበት ካለ ኬዝ ይክፈቱ ተብሏል። ራማፎሳ ቃል እንደገባው ያደርገዋል አያደርገውም የምናየው ይሆናል" ሲል ሃሳቡን አጋርቷል።

ከሳምንታት በፊት የነበረው ጥቃት ከዚህ ቀደሞቹ የተለየ እንደሆነ የሚስማሙት በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም ናቸው።

"የአሁኑ በደቡብ አፍሪካ ታላላቅ የማምረቻ፣ የንግድ እና የኢኮኖሚ ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ነው። ከዚህ በፊት ከነበረው በተለየ ትላልቆቹ ላይ ያነጣጠረ ነው። ትላላቅ የገበያ ማዕከላት ተዘርፈዋል፣ ተቃጥለውል፣ ወድመዋል በሎኬሽንም ይሄው ሆኗል" ብለው ነበር በወቅቱ ለቢቢሲ።

በትላላቅ የንግድ ማዕከላት እና 'ሎኬሽን' ያሉ የኢትዮጵያዊያን ሱቆች መዘረፋቸውን እና መቃጠላቸውን አስታውቀዋል።

በየአካባቢው በመደራጀት ራሳቸውን እና ንብረታቸውን ከመጠበቅ ባለፈ ኤምባሲው እና የኮሚውኒቲው ሚዲያን በመጠቀም በተላለፈው መልዕክት ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

ከማኅበረሰቡ የሚነሱ መልዕክቶችን በማንሳት ከሚመለከታቸው ከደቡብ አፍሪካ የመንግሥት አካላት ጋር በማድረስ በትኩረት እየሠሩ መሆኑንም ጨምረው ገልጸው ነበር።

አሁን ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄም በጽሑፍ በሰጡት ምላሽ "ደቡብ አፍሪካ ሙሉ ለሙሉ ሠላማዊ ሲሆን ቢዝነሶች ወደ ተለመደው ሥራ እየገቡ ነው" ሲሉ ምላሸ ሰጥተዋል።

በችግሩ ጉዳት የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን "እርስ በእርሳቸው በመረዳዳት በአብዛኛው በሚባል ደረጃ ወደ ሥራ መግባታቸውን" ጠቁመዋል።

ማኅበረሰቡ በየአካባቢው ተመሳሳይ ውጤት ለማግኘት በደንብ መደራጀቱንም አስረድተዋል።