ደቡብ አፍሪካ የተነሳውን ሁከት ለመቆጣጠር ሰራዊቷን አሰማራች

የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ እስርን ተከትሎ በሃገሪቱ ለተፈጠረው አመጽ ምላሽ ለመስጠት ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ "ህዝቡ አመጹን እንዲቃወሙ" ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፈው ሳምንት ዙማ እጃቸው ለፖሊስ ከሰጡ በኋላ ቢያንስ ስድስት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ወደ 500 የሚጠጉት ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ሱቆች ተዘርፈዋል ሕንፃዎችም ተቃጥለዋል።

በጋውቴንግ ግዛት እና በዙማ የትውልድ ስፍራ በክዋዙሉ-ናታል ወታደሮች ተሰማርተዋል፡፡

ዙማ በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ሰርተውታል በተባለው የሙስና ክስ ላይ ምርመራ ላይ መገኘት ባለመቻላቸው በእስር እንዲቀጡ ተፈርዶባቸዋል፡፡

የሙስና ክሱን ያስተባበሉት የ 79 ዓመቱ ዙማ የ 15 ወር እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡

ቅጣቱ በሀገሪቱ ህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት እንዲሰረዝ ወይም እንዲቀነስ ለማድረግ ተስፋ ተደርገወል፡፡

የህግ ባለሙያዎች እንደሚሉት ግን የመሳካት ዕድሉ አነስተኛ ነው፡፡

ራማፎሳ ሰኞ ዕለት በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር "በዴሞክራሲያችን ታሪክ ውስጥ እምብዛም የማይታይ ዓይነት የህዝብ አመጽ ድርጊቶችን" እንደሚያወግዙ ገልጸዋል፡፡

አለመረጋጋቱ የጀመረው የዙማ እስርን በመቃወም ቢሆንም ተባብሷል፡፡

በኩዋዙሉ-ናታል ከደርባን የተገኙ ምስሎች ሱቆች ሲዘረፉ እና የንግድ ቤቶች ሲቃጠሉ አሳይተዋል፡፡

በጆሃንስበርግ ዘራፊዎች ቴሌቪዥኖችን፣ ማይክሮዌቮችን እና ልብሶችን ሲወስዱ ታይተዋል፡፡

ራማፎሳ "አሁን እያየነው ያለነው የወንጀል ድርጊቶች ናቸው። ቡድኖች ብጥብጥን እንደ መሸፈኛ አድርገው ይዘርፋሉ" ብለዋል፡፡

"በኩዌዙሉ ናታል እና በጋውቴንግ የተመለከትነውን ሁከትና ውድመት ሊያረጋግጥ የሚችል ቅሬታ ወይም የፖለቲካ ምክንያት የለም፡፡"

እሑድ ዕለት ዱላ፣ የጎልፍ መምቻ እና አጠና የያዙ ሰልፈኞች በጆሃንስበርግ የንግድ ስፍራሰዎች ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል፡፡

በሁከቱ ምክንያት የኮቪድ-19 የክትባት ፕሮግራም ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።

አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች የክትባቱ መስጫዎች "ወድመዋል እና ተዘርፈዋል" ማለታቸውን የኤ ኤፈፍ ፒ የዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡ አንዳንድ ጣቢያዎች በደህንነት ስጋት ምክንያት ለመዝጋት ተገደዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ራማፎሳ "የክትባት ፕሮግራማችን እየጨመረ በመጣበት ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ተስተጓጉሏል፡፡ ይህ በኢኮኖሚ ማገገም ጉዟችን ላይ ዘላቂ ተጽዕኖ ይኖረዋል" ብለዋል፡፡

ዙማ ፍርድ ቤት ባለመቅረብ ከተላለፈባቸው እስር በተጨማሪ በሙስና ወንጀል ክስ ተመሰርቶባቸዋል፡፡ እአአ በ 1990ዎቹ ከተከናወነ የ 5 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሣሪያ ስምምነት ጋር በተያያዘ ተፈጸመ ስለተባለው ሙስና ባለፈው ወር ጥፋተኛ አይደለሁም ብለዋል፡፡

ደጋፊዎቻቸው በራማፎሳ አጋሮች የተቀናበረ የፖለቲካ ክስ ሰለባ እንደሆኑ ይከራከራሉ፡፡