ኩባ በአደባባይ ተቃውሞ እየተናጠች ነው

ኩባ በአስር አመታት ውስጥ አይታው የማታውቀው ትልልቅ የሚባሉ የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን ተከትሎ በርካታ ነዋሪዎቿ ለእስር እየተዳረጉ መሆኑን የመገናኛ ብዙኃን እና የተቃዋሚ ምንጮች ገልጸዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎቿ የተሳተፉበት የተቃውሞ ሰልፍ በደሴቲቱ የኮሚዩኒስት መንግሥት ላይ የተቃጣ ነው።

ኩባውያን በኢኮኖሚው ውድቀት፣ በምግብ እና መድኃኒት እጥረት፣ በሸቀጦች ዋጋ መናር እና በመንግሥት የኮቪድ-19 እንዝህላል አያያዝ ተቆጥተዋል።

የመንግሥት ተቺዎች ከባድ ቅጣት በሚያጋጥማቸው ኩባ የነዚህ ተቃዋሚ ሰልፎች መደረግ ጉልህ ሚና አለው እየተባለ ነው።

የኩባ ፕሬዚዳንት በምላሹ ደጋፊዎቻቸው ሰልፈኞቹን "እንዲፋለሙ" ጥሪ አቅርበዋል።

በእለተ እሁድ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ከተገኙት መካከል አሌሃንድሮ የተባለ ግሰለ ለቢቢሲ ሙንዶ "ምግብ የለም፣ መድኃኒት የለም፣ ነፃነት የለም እነሱ እንድንኖር እየፈቀዱልን አይደለም" ብሏል።

መዲናዋን ሃቫናን ጨምሮ በመላው ኩባ በተካሄዱ ሰልፎች የተቃውሞ ሰልፈኞች "ነፃነት" እና "የአምባገን መንግሥት ሊገረሰስ ይገባል" የሚሉ መፈክሮችን እያሰሙ ነበር።

በሳን አንቶኒዮ የተቃውሞ ሰልፍ የተሳተፈ ግለሰብ ለቢቢሲ እንደተናገረው "አንፈራም ፣ ለውጥ እንፈልጋለን ፣ ከዚህ በኋላ አምባገነንነትን አንፈልግም" ብሏል።

የፀረ-መንግሥት ተቃዋሚዎች ወታደራዊ መለዮ ባልለበሱ መኮንኖች በሚታገዙ የፀጥታ ኃይሎች መታሰራቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በማኅበራዊ ትስስር ላይ የወጡ ምስሎችም የፀጥታ ኃይሎች ተቃዋሚዎችን ሲይዙ፣ ሲደብድቡ እና አስለቃጭ ጋዝ ሲረጩ አሳይተዋል።

ይህንንም ተከትሎ በደሴቱቱ ኢንተርኔት የተቋረጠ ሲሆን የአሶሺዬትድ ፕሬስ ፎቶግራፍ አንሺ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር መጋጨቱን ተከትሎ ጉዳት ደርሶበታል ተብሏል።

የአገሪቱ ፕሬዝዳንቱ ሚጌል ዲአዝ-ካኔል ለዚህ ያልተለመደ አመፅ ምላሽ በቴሌቪዥ ቀርበው ለህዝባቸው ንግግር ያደረጉ ሲሆን በሁከቱ አሜሪካን ተጠያቂ አድርገዋል።

ከ1962 ጀምሮ በተለያየ መንገድ ሲተገበር የነበረው የኩባ ጥብቅ ማዕቀብን አንስተው "ኢኮኖሚውን የማፈን ፖሊሲ" ነው በማለት ወቅሰዋል።