ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በምዕራብ ወለጋ ስድስት ልጆች በመብረቅ ተመትተው ሕይወታቸው አለፈ
በምዕራብ ወለጋ ዞን መነ ሲቡ ወረዳ ጎምቦ ቂልጡ ተብሎ በሚጠራ ቀበሌ ውስጥ መብረቅ የአንድ መንደር ነዋሪ የሆኑ ስድስት ታዳጊዎችን መግደሉን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
የዓይን እማኝ ነኝ ያሉት የቀበሌው ነዋሪ ኦልጅራ ዲባር ሟቾቹ ልጆች እድሜያቸው ከ12-14 መካከል እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በአደጋው ታናሽ እህቱን ያጣው ቀነኒ የተባለ ሌላ ነዋሪ ደግሞ አደጋው ከትናንት በስቲያ ሰኞ ዕለት መከሰቱን አስታውሶ፤ "የመጨረሻ ልጅ ነች። የ7ኛ ክፍል ተማሪ እና እድሜዋ ገና 14 ነበር። ቤት ውስጥ የቀረችው እሷ ብቻ ነበረች" በማለት በቤተሰብ አባላት ላይ የታዳጊዋ መሞት ከፍተኛ ሀዘን መፍጠሩን ይናገራል።
የቀበሌው ነዋሪ ኦልጅራ የመብራቅ አደጋው ሲከሰት በአከባቢው ከፍተኛ ዝናብ እንዳልነበረ ያስታውሳሉ።
ነዋሪው እና በአደጋው ታናሽ እህቱን ያጣው ቀነኒ ታዳጊዎቹ በመብረቅ የተመቱት ችግኝ ለመትከል አንድ ላይ ሆነው እየሄዱ ሳለ ነበር ብለዋል።
"ችግኝ ወደሚተከልበት ቦታ እየሄዱ ሳለ ዝናብ መዝነብ ጀመረ ከዛ ዛፍ ስር ተጠለሉ። እዛው ዛፍ ስር እንዳሉ በመብረቅ ተመቱ" በማለት ኦልጅራ ይናገራሉ።
ከሟቾቹ መካከል አንዱ ወንድ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን እና የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ትናንት መፈጸሙን ተናግረዋል።
የቀበሌው ነዋሪ ኦልጅራ በአከባቢያቸው አልፎ አልፎ በሚያጋጥም የመብረቅ አደጋ የሰው ሕይወት እንደሚያልፍ አስታውሰው፤ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ሰው ሲገድል ግን ይህ የመጀመሪያው ነው ብለዋል።
"አልፎ አልፎ መብረቅ ይወድቃል። አንድ ሰው ወይም እንስሳት ላይ ጉዳት ያስከትላል እንጂ እንዲህ በርካታ ሰዎችን በአንድ ላይ ሲገድል ሰምተን እንኳን አናውቅም" በማለት ኦልጅራ ይናገራሉ።
በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች አንድ ሰው በመብረቅ ተመትቶ ሕይወቱ ሲያልፍ፤ ማህበረሰቡ 'ሞተ' ወይም 'ሕይወቱ አለፈ' አይልም። መብረቅ የፈጣሪ ሥራ ነው ተብሎ ስለሚታመን ነዋሪዎች 'ፈጣሪን ላለማሳዘን' ሲሉ 'እንኳን ሆነ' እንደሚሉ ይነገራል።
ኦልጅራም በአካባቢያቸው ተመሳሳይ አስተሳሰብ እንዳለ ይናገራሉ።
"ማህበረሰቡ መብቅ የፈጣሪ ሥራ ነው ብሎ ያምናል። ሰው በመብረቅ ተመትቶ ሕይወቱ ካለፈ እንኳን ይባላል። እኛ አካባቢ እንዲህ አይነት ነገር ሲከሰት ፈጣሪ ነው የሚያውቀው፤ [ሟቹን] ፈጣሪ ወዶታል ተብሎ ይታሰባል" ይላሉ።
በሰሜን ሸዋ ገብረ ጉራቻ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አመዴ አበራም እርሳቸው በሚኖሩበት ማህበረሰብ ውስጥም ተመሳሳይ እምነት እንዳለ ያስረዳሉ።
"መብረቅ ጉዳት ካደረሰ 'እንኳን ሆነ' ነው የሚባለው። የፈጣሪ ሥራ ስለሆነ። ከተኮነነ አደጋው ዳግም ይከሰታል ተብሎ ነው የሚታመነው" በማለት አስረድተዋል።
ሳይንስ ስለ መብረቅ ምን ይላል?
በብሔራዊ ሜትሮሎጂ የአየር ትንበያ ባለሙያ ሆኑት ጫሊ ደበሌ፤ መብረቅ 'የፈጣሪ ቁጣ' ተብሎ የሚታመነው ትክክል አይደለም ይላሉ።
"ሳይንስ የሚለው ቀዝቃዛ እና ሞቃታማ አየር ሲጋጩ ኤሌክትሪክ ይፈጥራሉ። ይህም 'ኔጋቲቭ' እና 'ፖዘቲቭ' ኃይል አለው። ወደ መሬት የሚቀርበው 'ኔጋቲቭ' ሲሆን፤ ኤሌክትሪክ የሚያስተላለፉ ነገሮች ላይ ሲቀርቡ 'ዲስቻርጅ' (ኃይል ይለቃሉ) በማለት ያስረዳሉ።
እንደ ባለሙያዎች ከሆነ በብዛት ሳሳ ያለ የደን ሽፋን ያለባቸው ቦታዎች ለመብረቅ አደጋ በይበልጥ ተጋላጭ ናቸው።
መብረቅ በሚያጋጥም ወቅት መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች
- ትልቅ ቤት ወይም ሕንጻ ውስጥ ቶሎ ገብቶ መጠለል
- ሜዳማና ገላጣ ቦታዎች ከሆኑ ቶሎ ከዚያ ቦታ ለመልቀቅ መሞከር
- ከኮረብታማ ቦታዎች መራቅ
- መጠለያ ቦታ ካጡ ደግሞ ባሉበት ቦታ ሆነው ሸብረክ በማለት ጭንቅላትን ወደ መሬት ቀብሮ፣ የራስን መጠን አሳንሶ ቁጢጥ ብሎ መቀመጥ
- በተጋለጡና ሜዳማ አካባቢ በሚገኙ ዛፎችና ዘለግ ያሉ ተክሎች ሥር ለመደበቅ አለመሞከር
- በውሀ አካላት ውስጥ ከነበሩ ቶሎ ብሎ ከውሃ ወደ የብስ መውጣት