ውዳሴ፡ በ 11 ጷጉሜዎች ለ16 ሺህ ሰዎች ነጻ የምርመራ አገልግሎት የሰጠው ማዕከል

ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ከ12 ዓመታት በፊት ነበር ስራ የጀመረው። ታዲያ ዘንድሮን ጨምሮ ከምስረታው በኋላ ባሉ ጷጉሜ ወራት በሙሉ ነጻ የምርመራ አገለግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በእነዚህ ዓመታት ማዕከሉ ከ2500 እስከ 5 ሺህ ብር የሚገመቱ የጤና ምርመራዎችን ከ46 ሺህ ለሚልቁ ሰዎች በነጻ መስጠቱን የማዕከሉ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬከተር ዳዊት ሀይሉ ይገልጻሉ።

ከዚህ ውስጥ 16 ሺህ የሚሆኑት ሰዎች ከማዕከሉ ምስረታ እስከ ባለፈው ዓመት በነበሩት የጷጉሜ ወራት አገልግሎት ያገኙ ናቸው።

የነጻ አገልግሎቱ ተጠቃሚዎች እነናቸው?

"ይህ የነጻ አገልግሎት በዋነኛነት ያተኮረው እኛ የምንሰጣቸው አገልግሎቶች የሚያስፈልጋቸው፣ ነገር ግን አቅም የሌላቸው ሰዎች ላይ ነው። አቅም የለኝም ነገር ግን አገልግሎቱ ያስፈልጋኛል የሚሉ ሰዎችን ነው የሚያጠቃልለው" የሚሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ "ይህንን እኛ የምንለይበት መንገድ [አቅም እንደሌለው] በመጠየቅ ነው። 'አቅም የለኝም' ካለ እናምነዋለን" በማለት ያስረዳሉ።

ማዕከሉ አገልግሎት የሚሰጠው የህክምና ትዕዛዝ የሚያስፈልጋቸውን እና ያለ ትዕዛዝ የሚሰጡትን ሲሆን ነጻ የህክምና ምርመራን በተመሳሳይ መንገድ የሚከወን ነው።

የነጻ ምርመራው በተለይ የሐኪም ትዕዛዝ የማይጠይቁ ምርመራዎች በጷጉሜ ወር ባሉት አምስት ወይም ስድስት ቀናት በ9888 የስልክ መስመር አማካኝነት ምዝገባ ተደርጎ ምርመራው ከጷጉሜ ወር በኋላም ይቀጥላል ብለዋል።

"እኛ በምዝገባው መሰረት እንደ አስፈላጊነቱ እንደ አስቸኳይነቱ እያደረግን እንሰጣለን። ለምሳሌ ባለፈው ዓመት እስከ ታህሳስ ድረስ ሄደናል። [ጷጉሜ ላይ ለተመዘገቡት ምርመራ ለመስጠት] በዚህ ጊዜ ይመዝገቡ እንጂ ስራው ጷጉሜ 5 ያቆማል ማለት አይደለም። ከክፍለ ሃገር የሚመጡትን ቅድሚያ በመስጠት አስቸኳይ ወይም ከአደጋዎች በኋላ ለሚያስፈልግ ምርመራ ቅድሚያ በመስጠት እንሰራለን" ሲል ያስረዳሉ።

ማዕከሉ ስራ ሲጀምር በአንድ የሲቲ ስካን ማሽን ብቻ እንደነበር የሚያስታውሱት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አቅም ለሌላቸውና የጤና ምርመራ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ይገልጻሉ።

ውዳሴ ሲቲስካን፣ ኤም አር አይ፣ አልትራሳውንድ፣ ኤክስ ሬይና ሌሎች አገልግሎቶችን በአዲስ አበባ በሚገኙ ስድስት ቅርንጫፎች እየሰጠ እነደሚገኝ የሚናገሩት ዳዊት፣ በሁሉም ቅርንጫፎቹ ሁሉንም የምርመራ አገልገሎት አቅም ለሌላቸው ሰዎች በነጻ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።

እነዚህ ምርመራዎች 'ውድ የሚባሉ' እንደሆኑ የሚያስረዱት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ "እንኳን አቅም ለሌለው ይቅርና ደህና የመንግሥት ሰራተኛ ነው የሚባል እንኳን የሚያንገዳግዱ ናቸው።...አንዳንዱ ድንገት በአደጋ የተከሰተና ድንገት መከፈል ያለበት ሊሆን ይችላል።

አንዳንዱ ደግሞ ጊዜ ሰጥቶ መምጣት ያለበት አለ። ስለዚህ በጷጉሜ ጊዜ ምን አልባት አመቱን በሙሉ ነጻ በምንሰጥበት ጊዜ መምጣት ያልቻሉ፣ ይህንን ነገር ፈልገው በየቤታቸው የተቀመጡትን የምንጠራበት ወይም ይህንን አገልግሎት ለማግኘት ብለው ወደ ተለያየ የመንግሥት ሆስፒታሎች ሄደው ወረፋ እየጠበቁ ያሉ ሰዎችን ወደ እኛ የምንጠራበትና የምንሰራላቸው ጊዜ ነው" ብለዋል።

"ማህበራዊ ላፊነቱን ተወጥቶ የከሰረ ድርጅት የለም"

ማዕከሉ 'ከመስከረም እስከ መስከረም' ነጻ አገልግሎት ይሰጣል የሚሉት ዳዊት "ጷጉሜን ለጤና" በሚል መሪ ሃሳብ ከሚሰጠው የነጻ አገልግሎት ጋር በአጠቃላይ ከ46 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ነጻ አገልግሎት እንደሰጠ ጠቅሰዋል። ከዚህ ውስጥ ከ16 ሺህ በላይ የሚሆኑት ሰዎች አገልግሎቱ በአስራ አንዱ ጷግሜዎች የቀርቡላቸው ናቸው።

ማኔጂንግ ዳይሬከተሩ ማዕከሉ ይህንን አይነቱ አገልግሎት የሚሰጠው በዋነኛነት 'በጎነትን ለማጋባት' በማሰብ ነው ይላሉ።

"ሰዎች እኛ የምንሰራውን አይተው እኔስ ምን ማደረግ እችላለሁ ብለው እንዲያስቡ በጎነትን እንድናስተላልፍ፣ በበጎነት የምናደርገው ነገር ነው። በጎነት የሚጋባ ነገር ነው. . .።...ትርፍ ውጤት ነው ብለን እናምናለን...ዓላማችን ማህበረሰቡን ማገልገል፣ ዓላማችን የጤና አገልግሎት እንዲስፋፋ ማድረግ ሲሆን በዛ አገልግሎት ትርፍ ግን አብሮ ይመጣል ብለን እናምናለን። በዚህም አልከሰርንም ተቋማዊ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ተወጥቶ የከሰረ ድርጅት ደግሞ የለም - በአግባቡ እስከተወጣ ድረስ።"

በዚህም መነሻነት ማዕከሉ የሚሳተፍባቸውን የበጎ ተግባራት በማስፋፋት ላይ እንደሆነ ጠቅሰዋል። 'ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ' ደግሞ ከነጻ ምርመራ ባሻገር ማዕከሉ ባስቆጠረው ዓመት ልክ በጎ ተግባርትን እየሰራ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።

ለአብነትም ማዕከሉ 12ኛ ዓመቱ መያዙን በማስታወስ "12 ቀናትን መድበን 12 በጎ ተግባራትን እናድርግ ብለን ለ12 ቀናት [ከነሃሴ 24 ጀምሮ] በጎ ነገር የምናደርግበትን ጀምረናል" ያሉ ሲሆን ይህም አራት የአቅመ ደካማ ቤቶችን ማደስ፣ ደም መለገስ፣ የአስቤዛ ስጦታንና በጎዳና ያሉ ከ1ሺህ በላይ ዜጎችን መመገብ ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን የሚጨምር ነው።

እንደ ተቋም ማህበራዊ ኃላፊነትን መውጣት እንደ አንድ የድርጅቱ መርህ እንደተቀመጠ የጠቀሱ ሲሆን በዚህም ከሚሰጠው ነጻ አገልግሎት በተጨማሪ ማዕከሉ ቅርንጫፎቹ በሚገኙበት ክፍለ ከተሞች ላሉ ነዋሪዎች መታወቂያቸው በማሳየት ብቻ በሁሉም አገልግሎት የ 20 በመቶ ቅናሽ እንደሚደረግ ተናግረው ይህንንም "አካባቢን ማክበር" ነው ሲሉ ይገልጹታል።

"የበጎነትን ጣዕም ስለቀመስን መቼ ነው የሚመጣልን እያለን በናፍቆት ነው የምንጠብቀው። የበለጠ ለማድረግ የምንጓጓበት ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል "ተቋማዊ ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት የውዴታ ግዴታ ነው" ነው ሲሉ የገለጹ ሲሆን የእርሳቸው ተቋም ይህንን በማድረጉ በርካታ ጥቅሞችን ስለማግኘቱ ይናገራሉ።

"እኛ እንደድርጅት ያገኘነው ጥቅም በመጀመሪያ ደረጃ ሰራተኞቻቸን ከፍተኛ ተነሳሽነት እንዲኖራቸው አድርጓል።...መልካም ስም፣ መልካም ዝና እንዲኖር ያደርጋል። ይሄ መልካም ስም ወደ ገንዘብ የሚለወጥና ራሱን የቻለ ትርፍ ነው። ስለዚህ በጎነት ለኔ ማትረፍ ነው፤ በጎነት ማግኘት ነው፤ መስጠት መክሰር አይደለም። በየዓመቱ ለደረስንበት ከፍተኛ ዕድገት ትልቁን አስተዋጽኦ ያደረገው የመስጠት አስተሳሰባችን ነው" ሲሉ አክለዋል።

ማዕከሉ የባለ ብዙ ስፔሻሊቲ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ህንጻ እየገነባ ይገኛል። ይህም የማዕከሉን አገልግሎት በእጅጉ እንደሚቀይረውና ለምርመራ ወደ ውጪ ሀገራት የሚደረገውን ጎዞ ለመቀነስ እንደሚያግዝ አስረድተዋል። ታዲያ ማዕከሉ በዚህ ደረጃ ሲያድግ የበጎ ተግባር ስራው አብሮ ከፍ እንደሚል ጠቁመዋል።

"እንኳን በዚህ ደረጃ ይቅርና አንዲት ሲቲስካን ኖሮን ገና የገዛነውን ማሽን ዕዳ ከፍለን ሳንጨርስ ብዙ እዳዎች እየነበርብን ይህን አድርገነዋል። አሁን ደግሞ የበለጠ በበርታ ሃይል እናደርገዋለን" የሚሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ "በጎነት ዕድሜ አይጠይቅም፤ በጎነት ገንዘብ መስጠት ብቻ አይደለም፤ ጊዜ ያለው ጊዜውን ዕውቀት ያለው ዕውቀቱን የሚሰጠበት ነው። ሀገራችን አሁን ባለችበት ሁኔታ ደግሞ ብዙ በጎ የሚሰሩ ሰዎችን የምትፈልግበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው" ሲሉ አክለዋል።