ኢትዮጵያ በአልጀሪያ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለመዝጋት ወሰነች

ኢትዮጵያ በአልጀሪያ የሚገኘውን ኤምባሲዋን በመዝጋት የሚኖራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አዲስ አበባ በሚገኝ አምባሳደር አማካይነት ለማድረግ መወሰኗን ኤምባሲው አስታወቀ።

በአልጀሪያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ እንዳሳወቀው ለመዘጋቱ ምክንያት የሆነው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ባስከተለው አሉታዊ መዘዝ በገንዘብ እጥረትና የምጣኔ ሀብት ቀውስ ነው ብሏል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ማሻሻያዎችን በማካሄድ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዓለም የበለጠ የምትወከልበትን መንገድ እንደገና ማደራጀት አስፈላጊ መሆኑ በመታመኑ እንደሆነ ኤምባሲው አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከዚህ ቀደም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አገሪቷ ካሏት ከ60 በላይ ኤምባሲዎች ውስጥ ግማሹን የመቀነስ እቅድ እንዳላት አስረድተው ነበር።

በአልጀሪያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጊዜያዊነት የሚዘጋ ሲሆን ከመስከረም 30/2014 ዓ.ም ጀምሮ የኤምባሲው ሥራዎች በአገሪቱ ተቀማጭ ባልሆኑ አምባሳደር ከአዲስ አበባ የሚሸፈን ይሆናል ተብሏል።

በአልጀሪያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የመዝጋት ውሳኔ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ሲሻሻል ለወደፊቱ በማንኛውም ጊዜ ሊታይ እንደሚችልም ኤምባሲው አስታውቋል።

ኤምባሲው ይህ ጊዜያዊ እርምጃ በምንም መልኩ በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ በኢትዮጵያ እና በአልጄሪያ መካከል ያለውን ታሪካዊና ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንደማይጎዳ አጽንዖት ለመስጠት ይፈልጋል ብሏል።

አገራቱ በአህጉራዊ፣ በዓለም አቀፍ እና በአካባቢያዊ መድረኮች የሚያከናውኑትን የሁለቱን አገራት ልማት እና ደኅንነት የሚጠቅሙ ሥራዎች እንዲሁም ሁለቱንም አገራት የሚያስተሳስረውን የሁለትዮሽ እና የብዝሃነት ግንኙነቶችን ያከብራል ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም ዙሪያ ባሉት የዲፕሎማሲ ተልዕኮዎቹ ላይ በሚያደርገው ለውጥ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኤምባሲዎችና የቆንሰላ ጽህፈት ቤቶች እንደሚታተፉ ሲነገር ቆይቷል።