ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከዩቲዩብ በወር ከ30 እስከ 220 ሺህ ብር የሚያገኙት ኢትዮጵያውያን ዩቲዩበሮች
ዩቲዩብ ጊዜና ሀሳባቸውን ሰጥተው 'ሥራዬ ብለው' በትጋት ቪዲዮዎችን ለሚሰሩ ሰዎች ሳይውል ሳያድር 'በረከት' ይዞላቸው ይመጣል። ለአንዳንዶቹ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ይከፍላል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 ዩቲዩብ ራያን ካጂ ለተባለ የ9 ዓመት ታዳጊ 29. 5 ሚሊዮን ዶላር [በወቅታዊ ምንዛሬ ከ1 ቢሊዮን 305 ሺህ ብር በላይ] ከፍሏል።
ይህ ታዳጊ በዓመቱ ትልቁ የዩቲዩብ ተከፋይ ሲሆን እሱን ተከትሎ ጂሚ ዶናልድሰን የተባለ ሌላ ዩቲዩበር ደግሞ በተመሳሳይ ዓመት 24 ሚሊዮን ዶላር [ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ] ከዩቲዩብ አግኝቷል።
በነገራችን ላይ ሁለቱ ዩቲዩበሮች ብቻ በዚያ ዓመት ያገኙት ገቢ ለሐዋሳ ከተማ በ2014 በክልሉ ከተመደበው በጀት ጋር የሚስተካከል ነው።
በኢትዮጵያም እንዲሁ ዩቲዩብ ለበርካቶች መተዳደሪያና የገቢ ምንጭ እየሆነ ነው።
ኢትዮጵያውያኑ ከዩቲዩብ ምን ተጠቀሙ?
ሚኪያስ ተከለማርያም ይባላል። 'ሚኪ ማይኮ' በሚል ስያሜ ዩቲዩብን ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር የተቀላቀለው።
ቀድሞም የተለያዩ የጥበብ ሥራዎችን የመስራት ፍላጎት የነበረው ሚኪያስ ኢንተርኔት ቤት ተቀጥሮ ይስራ በነበረው ጓደኛው አማካኝነት ዩቲዩብን የመመልከት እድል ተፈጠረለት።
እድሉም በዩቲዩብ ዝና ያተረፉ የውጭ አገር ዩቲዩበሮችን እንዲከታተልና እሱም በዚሁ መድረክ አማካኝነት ሥራ እንዲጀምር አነሳሳው፤ የዩቲዩብ ቻናልም ከፈተ።
እናም ካሜራ በመከራየት ከጓደኞቹ ጋር የ10 ደቂቃ ድራማ ሰርቶ ለመጀመሪያው ጊዜ ቻናሉ ላይ ቪዲዮ ጫነ። ሆኖም ይህ ቪዲዮ ምንም ተመልካች አላገኘም። በሁኔታ ተስፋ ያልቆረጠው ሚኪያስ ሌላ የፕራንክ ቪዲዮ ሰርቶ ጫነ። "እሱ የተሻለ ዕይታ ነበረው። ያው ዕይታ ስል 50 ወይም 60 ነበር" ሲል ያስታውሳል።
ሥራውን በዚህ መልኩ የቀጠለው ሚኪያስ የቪዲዮዎቹ የተመልካች ብዛት ቀስ በቀስ በመጨመር አሁን ላይ የሰራቸው ቪዲዮዎች በጥቅሉ ከ43 ሚሊዮን ጊዜ በላይ ታይተዋል።
ወደ 485 ሺህ የሚጠጋ 'ሰብስክራይበርም' [ተከታይ] አግኝቷል። ይህም በድምሩ እስከ 5 ሚሊዮን ብር እንዲያገኝ አስችሎታል።
"ከዩቲዩብ በርካታ ጥቅሞች አግኝቻለሁ" የሚለው ሚኪያስ በሳምንት በተለያዩ ርዕሶችና ይዘቶች አምስት ቪዲዮችን በመስራት ያሰራጫል።
ከዚህም በሚያገኘው ገንዘብ 'በጥሩ ሁኔታ' ኑሮን እየመራ ነው። "[ዩቲዩብ] በነጻነት የምፈልገውን ሳልገደብ እንድሰራ እድል ሰጥቶኛል፤ ይሄን ማግኘት ለኔ ትልቁ ጥቅም ነው። ከዚያ ውጪ ከሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያ በተሻለ ገንዘብ ይከፍላል። ያም ራሴን እንዳግዝ ራሴን እንድለውጥ ይረዳኛል" በማለት ያስረዳል።
"በወር ከአራት ሺህ እስከ አምስት ሺህ የሚደርስ ዶላር ከማስታወቂያ ሥራዎች ውጪ [በወቅታዊ ምንዛሬ 220 ሺህ ብር]" እንደሚያገኝ የሚናገረው ሚኪ ማይኮ፣ ካሜራ በመከራየት የጀመረው ሥራ አሁን ሁለት ዘመናዊ ካሜራዎችን ጨምሮ የተሟላ ቁሳቁስ እንዲኖረው አስችሎታል።
ከዚህም አልፎ ስምንት ሰዎችን ቀጥሮ እያሰራም ይገኛል።
ዊንታና ይልማ ደግሞ በአስተዳደጓ ውስጥ ያየችውና መታረም አለበት ብላ ያሰበችውን ልማድ ለመቀየር ነበር ዩቲዩብን የተቀላቀለችው።
በፍቅር፣ ትዳርና ግንኙነት ላይ በግልጽ መወያየት ያስፈልጋል ብላ የምታምነው ዊናታና ማኅበራዊ መድረኩ ይህን ዕድል ሰጥቷታል።
"የኔ ቤተሰቦች ልጅ ሆነው ነው የተጋቡት፤ ማስተዋልም ስለሌላቸው ነው መሰለኝ ብዙ ጊዜ ሲጣሉ ነው የማየው። ... ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ነው አባቴ ከእናቴ ጋር የተለያየው።...በጣም አስቀያሚ ህይወት አሳልፈናል - በእነርሱ መለያየት ምክንያት...የሚመራን አልነበረም። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ [በፍቅርና ትዳር ዙሪያ መስራት] ውስጤ የነበረ ነገር ነው" የምትለው ዊንታና የቤተሰብ ጉዳይ ላይ በትኩረት መሰራት ይገባል ትላለች።
"ይሄ ዝም የሚባልበት ጉዳይ አይደለም። ትውልድ የሚቀረጽበት ነው። ... እና ይህንንም ለመስራት ያነሳሳኝ የራሴ ህይወት፣ የቤተሰቤ ህይወት ነው" ስትል ታክላለች።
በዚህም መነሻነት በአንድ የዩቲዩብ ቻናል ተቀጥራ በጓደኝነት፣ በፍቅርና በትዳር ዙሪያ የሰራቻቸው የተለያዩ ቪዲዮዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ዕይታዎች አግኝቶላታል። እነዚህን ቪዲዮዎች ስታዘጋጅ የምትሰራበትን ዩቲዩብ የሚያስተዳድረው ድርጅት በየወሩ 10 ሺህ ብር ይከፍላት ነበር።
ዊንታና ዩቲዩብ ስትሰራ የገጠማት ፈተና ከሚኪያስ የሚለይ ነው። ቪዲዮዎቿ ጥሩ ተመልካች ቢኗሯቸውም ሥራውን ለመተው የሚገፋፉ አስተያየቶች ይደርሳት ነበር።
ርዕሰ ጉዳዮቹ አዲስ በመሆናቸው ቪዲዮዎቹ ሲለቀቁ 'የሚያስደነግጡ' እንዲሁም ዘለፋ የተሞላባቸው ጭምር አስተያየቶች ይሰነዘርባት ነበር። አንዳንድ አስተያየቶች "ሞራሏን እንዳይነኩ ጥንቃቄ" ማድረጓ እዚህ ስለመድረሷ ምክንያት መሆኑን ትናገራለች።
በምትሰራባቸው ጉዳዮች ላይ በማንበብና የሰዎችን ተሞክሮ በመጠየቅ በቂ ዝግጅት እንደምታደርግ የምትናገረው ዊንታና፣ የምትሰራቸው ቪዲዮዎች እይታ እየጨመረ ቢመጣም ደመወዟ ለውጥ አለማሳየቱን ታስረዳለች። እናም አጋጣሚው የራሷን የዩቲዩብ ቻናል እንድትከፍት አግዟታል።
ሁለት ዓመት የሰራችበትንና ለስኬቷና እንዲሁም ለመታወቋ ምክንያት እንደሆነ የጠቀሰችውን ቻናል በመልቀቅ የራሷን ከከፈተች ሁለት ወራት ያስቆጠረችው ዊንታና፤ በነዚህ ጊዜያት ከ19 ሺህ የሚልቅ ሰብስክራይበርና [ተከታይ] 750 ሺህ በላይ ጠቅላላ ዕይታን አግኝታለች።
ልክ እንደሚኪያስ ሁሉ በነጻነት መስራትና ሰፊ የቤተሰብ ጊዜ ማግኘት ከዩቲዩብ ያገኘችው አንዱ ጥቅም ነው። ከገቢ አንጻርም "ከ10 ሺህ ብር ወደ 30 ሺህ ብር ደርሻለሁ...ከጀመርኩ ሁለት ወሬ ነው ገና እያደግሁ እንደምሄድ እርግጠኛ ነኝ" ስትል ገልጻለች።
በሌላ በኩል የሰዎች ህይወት ላይ ለውጥ መፍጠር መቻሏን በመግለጽ ይህም ትልቁ ስኬቷ መሆኑን ታብራራለች "ከአምስት ሰዎች አንዱ እንኳን በጣም ነው የረዳሽኝ ካለኝ በጣም ነው ደስ የሚለኝ። አላማዬ ያ ነው። ጥሩ የሚመስል ውስጡ በጣም የፈራረሰ ቤተሰብ አለ - እኔ እንኳን የማውቀው። እዚያ መድረስ መቻሌ ደስ የሚል ነገር ነው... 'ከባለቤቴ ጋር ልለያይ ነበር ግን ያንቺን ቪዲዮ ሳይ ተመለስኩ የሚል ሰው ሳይ በጣም ደስ ይለኛል። ከዚያ በላይ ምን ስኬት አለ?" ስትልም ትጠይቃለች።
በዩቲዩብ እንዴት ውጤታማ መሆን ይቻላል?
"እኔ እዚህ ጋር የደረስኩት በጽናት ስለሰራሁ ይመስለኛል...በተከታታይ ያለ 'ቪው' [ተመልካች] ነው የሰራሁት። ለረጅም ጊዜ ስሰራ ዩቲዩብ አልከፈለኝም። ምክንያቱም የዩቲዩብን [ደንብ] መጠበቅ ነበረብኝ። ዩቲዩብ 4 ሺህ የዕይታ ሰዓት የሚል ነገር አለው ዩቲዩብ [ክፍያ ለማስጀመር የሚያስፈልግ የዕይታ ሰዓት ነው]። ያ እስኪ ሞላ ድረስ በትጋት ሰርቻለሁ" የሚለው ሚኪያስ በዩቲዩብ ውጤት ለማግኘት የጀመሪያው ቁልፍ ቁርጠኝነትና ጽናት ስለመሆኑ ይጠቅሳል።
"መጀመሪያ የሚቀድመው ዩቲዩብ ሥራ ለመስራት ራስን ማወቅ ነው። መስራት የምንፈልገውን ማስተላለፍ የምንፈልገውን ማወቅ አለብን። የእኔ ፍላጎት የውስጤ ባይሆን ኖሮ ፈተናዎቹን ማለፍ አልችልም ነበር። ብዙን ፈተና የሚያሳልፈን የእውነት ፍላጎታችን ሲሆን ነው" ያለችው ደግሞ ዊንታና ነች።
እንደሚኪያስ ገለጻ ዙሪያችንን ከተመለከትን ሁሉም ነገር ለዩቲዩብ ቪዲዮ ግብዓት መሆን ይችላል።
"አንዲት እናት ከሥራ መጥታ እንዴት ልጇን እንደምትንከባከብ፣ ሥራ ስትሄድ ለልጇ ምን ምን ነገር አዘጋጅታ ነው የምትሄደው? ይሄን ማየት ራሱ የሚፈልግ ተመልካች አለ። ... ፊኒሽንግ [የህንጻ ወይም የቤት ውበት የመጠናቀቂያ ግንባታ] የሚሰሩ ወጣቶች ዩቲይብን ተጨማሪ ገቢ ማድረግ ይችላሉ። አንድ ቤት ተጀምሮ እስኪያልቅ ያለውን ልፋት ሁላችንም ማየት የምንፈልገው ነገር ነው። ሁሉም ህይወቶች ከዩቲዩብ ጋር ማገናኘት እንችላለን።"
ዊናታና ደግሞ ዩቲዩብ በትጋት የሚሰሩትን እንደሚያበርታታ በመግለጽ የሚጫኑ ቪዲዮዎችና ዕይታቸው በጨመረ ቁጥር የሚገኘው ገንዘብና ጥቅም 'መቆሚያ' ስለማይኖረው ለዚህም ተወዳዳሪ ሀሳቦችን ይዞ መምጣት ያስፈልጋል ስትል ገልጻለች።
በዩቲዩብ የሚጫኑ ቪዲዮዎችን ውጤታማ ለማድረግ
ከዓመታት በፊት ፒት ዋልተር የተባለ የሚዲያ ስልጠና ባለሙያ ለቢቢሲ ባጋራው አስተያየት በዩቲዩብ የሚጫኑ ቪዲዮዎችን ውጤታማ ለማድረግ የሚረዱ ነጥቦችን አስቀምጧል።
የመጀመሪያ ጉዳይ የዕይታ ሰዓት ነው። የዕይታ ሰዓት ተመልካቾች አንድ ቪዲዮ በአማካኝ ምን ያህል ሰዓት ተመለከቱት የሚለውን የሚጠቁም ነው። ታዲያ እንደ ዋልተር ገለጻ በዩቲዩብ ከዕይታ ቁጥር [ከተመልካች] በላይ የተጫነውን ቪዲዮ ተመልካቾች ለምን ያህል ጊዜ ተመለከቱት የሚለው ወሳኝ ነው።
ለዚህም ምሳሌ ሲያስቀምጥ አንድ በሰከንዶች የሚቆጠር የዕይታ ጊዜ ያለው ግን 1 ሺህ ጊዜ የታየ ቪዲዮ 100 ጊዜ ከታየ ግን አንድ ደቂቃ የዕይታ ሰዓት ካለው ቪዲዮ ያነሰ ሊሆን ይችላል።
ስለዚህ ምንም እንኳን የተለየ ሕግ ባይቀመጥም የዕይታ ሰዓትን ለመጨመር ከአንድ እስከ 3 ደቂቃ ያሉ ማራኪ ቪዲዮችን መስራት ውጤታማ ሊያደርግ ይችላል ብሏል።
ርዕስ ሌላኛው ወሳኝ ጉዳይ ነው። ተመልካቾችን ሊስብ የሚችልና ቪዲዮን የሚገልጽ፣ ከቪዲዮ የተወሰደ ሀሳብ የያዘ ሐረግ ወይም ሌላ ርዕስ ብዙ ተመልካች ያስገኛል።
ከተደጋገመ የርዕስ አይነት መቆጠብ ተገቢ መሆኑም የጠቀሰ ሲሆን ርዕሱና የቪዲዮ ይዘት የተለያየ ሆኖ ተመልካችን የሚያሳስት ከሆነ ክፉኛ ሊጎዳ እንደሚችል አንስቷል።
በሌላ በኩል ቪዲዮን የሚገልጽና ከዚያው የተወሰደ ሳቢ ምስል [Thumbnail] ማያያዝ ተመልካቾች ቪዲዮውን እንዲመለከቱ እንደሚረዳ ተብራርቷል።
ይህ የዩቲዩብ ተመልካቾችን የመሳቢያ መንገድ ይዘቱን የሚገልጽ ጽሁፍ ለማከል እንደሚረዳ የተገለጸ ሲሆን ይህም የቪዲዮን ይዘት በአጭሩና በፍጥነት ለተመልካቾች ለማጋራት ያግዛል። ሆኖም ልክ እንደ ርዕስ ሁሉ አሳሳች ምስል መጠቀም መጉዳቱ አይቀርም።
የፒት ዋልተር የመጨረሻ ሀሳብ ደግሞ የተሰራውን ቪዲዮ በተለያዩ ማኅበራዊ መድረኮች ማጋራት ነው። ዩቲዩብ የመጠቀም ልምድ የሌላቸውን ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ለማግኝት ከዩቲዩብ 'ወጣ ብሎ ማጋራት' ያስፈልጋል ብሏል።
የሥራዎቹ ሁሉ ማዕከል ግን በዩቲዩበሮቹ እንደተጠቀሰው ተጠቃሚዎችን ሊስብ የሚችል ይዘት ያለውን ቪዲዮ ይዞ በተከታታይና በትጋት መስራት መሆኑ ተጠቅሷል።
የወደፊት ዕቅድ
ወደ ዩቲበሮቹ ስንመለስ ዊንታና ወደፊት ቀደም ብላ ስታስበው የነበረውንና ከልጇ ጋር የምትሰራውን ህጻናት ማዕከል ያደረጉ መጽሐፍት፣ ሙዚቃዎችና ፕሮግራሞች በስፋት የመቀጠል ውጥን አላት።
ሚኪያስ ደግሞ በጎ ሥራዎች ላይ የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ የመቀጠል ሃሳብ አለው። ከሳምንታዊ ፕሮግራሞቹ መካከል አንዱ የሆነውና 30 ሰከንድ የተሰኘው ፕርግራም በተለያዩ ምክንያቶች የተቸገሩ ሰዎች እርዳታ የሚያገኙበት ነው።
ይህንን ሀሳብ በማሳደግ 'የኔ ሰው' የሚል በጎ አድራጎት ድርጅት ከፍቷል። ታዲያ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወርና እስካሁን ያልተነኩ ርዕሶች ላይ በማተኮር የመስራት ዕቅድ ያለው ሲሆን ይህንንም ከበጎ አድራጎት ጋር በማስተሳሰር መስራትን አልሟል።