ዩቲዩብ ክፍያ ሳይፈጽም ማስታወቂያዎችን በቪዲዮዎች ላይ ሊያስገባ ነው

ዩቲዩብ ብዙ ቪዲዮዎች ላይ ማስታወቂያዎችን ማሳየት እንደሚጀምር እና ለሁሉም ግን ክፍያ ላይፈጽም እንደሚችል አስታወቀ፡፡

ኩባንያው በአሁኑ ወቅት የማስታወቂያ ገቢውን በሽርክና መርሃ ግብሩ ላይ ከተመዘገቡ ቪዲዮ ሠሪዎች ጋር ይጋራል።

ከዚህ በኋላ ግን ዩቲዩብ የሽርክና መርሃ ግብሩ አካል ያልሆኑ አንዳንድ ቪዲዮዎች ላይም ማስታወቂያዎችን ማስገባት እጀምራለሁ ብሏል።

በአገልግሎት ውሉ ላይ በተደረጉ ለውጦች ምክንያት ዩቲዩብ ከማስታወቂያዎቹ የሚገኘውን ገቢ ለቪዲዮ ሠሪዎች አያጋራም ማለት ነው።

በተጨማሪም ተመልካቾች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ማስታወቂያዎችን እንዲያዩ ሊገደዱ ይችላሉ ተብሏል።

የዩቲዩብ የሽርክና መርሃ ግብር አካል ለመሆን ጥያቄ ማቅረብ የሚያስፈልግ ሲሆን፤ 1000 በላይ ተከታይ ላላቸው እና በአንድ ዓመት ውስጥ ለ4000 ሰዓታት ቪዲዮዎቻቸው ለታዩላቸው ብቻ የሚሰጥ ነው።

ዩቲዩብ በመርሃ ግብሩ ውስጥ የሌሉ ቪዲዮ ሠሪዎች "ከእነዚህ ማስታወቂያዎች የገቢ ድርሻ አይወስዱም" ቢልም ቪዲዮ ሠሪዎች በመደበኛ መንገድ የሽርክና መርሃ ግብር አካል ለመሆን ጥያቄ ማቅረብ ዕድል ይኖራቸዋል ተብሏል።

እንደ ዩቲዩብ የማመልከቻ ሂደት ገለፃ ጥያቄዎች በሰዎች እንዲገመገሙ ወረፋ ተራቸውን እንዲጠብቁ እንደሚደረግ ገልጾ ይህም ከአንድ ወር በላይ ሊፈጅ ይችላል ብሏል።

ጋዜጠኛና ደራሲው ክሪስስቶከል-ዎከር "ይህ ማለት የሽርክና መርሃ ግብሩ አካል ያልሆነ አነስተኛ የቪዲዮ ሠሪ ምንም ዓይነት የማስታወቂያ ገቢ ሳያገኝ ብዙ ተመልካች ያገኛል ማለት ነው" ሲል ያስረዳል።

"አንድ የቪዲዮ ሠሪ ስኬቱን ተጠቅሞ እንደ ስፖንሰር ባሉ ሌሎች ገቢዎች ሊጠቀም ቢችልም ውሳኔው ግን እንግዳ ይመስላል" ሲል ጥያቄ አንስቷል።

"ዩቲዩብ ቀድሞውንም ትኩረቱ እጅግ በጣም ብዙ ገንዘብ በማግኘት ላይ ነው" ሲልም አብራርቷል።

"በበቂ ሁኔታ ሳይክሳቸው ወይንም ላደረጉት አስተዋጽኦ ተገቢውን እውቅና ሳይሰጣቸው ዩቲዩብ በሥራቸው ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን የፖሊሲ ለውጥ ማድረጉ ቪዲዮ ሠሪዎችን ይበልጥ የሚያበሳጭ ነው" ብሏል።

ለውጦቹ በአሜሪካ ውስጥ እየተጀመሩ ሲሆን አዲሱ ውል በሚቀጥለው ዓመት በሌሎች ቦታዎችም "ተግባራዊ ይሆናሉ" ሲል ዩቲዩብ አስታውቋል።

ይህ የዩቲዩብ ውሳኔ ተቃውሞ ቢገጥመውም ሀሳቡን የመቀየር ዕድሉ ጠባብ መሆኑን ስቶከል-ዎከር ገልጿል።