ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጓደኛው ራሱን ሲያጠፋ በፌስቡክ በቀጥታ የተመለከተው ግለሰብ ትግል
ጆሽ ስቲን የቅርብ ጓደኛው ሮኒ መክነት ራሱን ሲያጠፋ በፌስቡክ ቀጥታ የተመለከተው ከሦስት ሳምንት በፊት ነበር።
ፌስቡክን ጨምሮ ጓደኛው ራሱን ሲያጠፋ ከሚያሳዩ ሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች ጋርም እየታገለ ነው።
“ላለፉት ሁለት ሳምንታት የሮኒ ፊት በየኢንተርኔት ገጹ እየታየ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ቁጥጥር እናደርጋለን ቢሉም ምንም አልተደረገም” ይላል።
ጆሽ ጓደኛው ራሱን ሲያጠፋ በቀጥታ ማሰራጨት በጀመረ በሁለት ሰዓት ውስጥ ለፌስቡክ ጠቁሟል። ይህም ከጓደኛው ህልፈት ከግማሽ ሰዓት በፊት ነው።
ሆኖም ግን ጥቆማ አድርጎ እስከ ለሁለት ሰዓት ገደማ ምላሽ እንዳላገኘና ፌስቡክ እየተሰራጨ የነበረው ተንቀሳቃሽ ምስል የድርጅቱን ደንብ እንደማይጥስ እንደገለጸለት ጆሽ ይናገራል።
“ፌስቡክ ሮኒ ከመተኮሱ በፊት ስርጭቱን መግታት ይችል ነበር”
ጆሽ እንደሚለው ከሆነ ፌስቡክ ስርጭቱን ማቆም ይችል ነበር።
“ፌስቡክ ሮኒ ከመተኮሱ በፊት ስርጭቱን መግታት ይችል ነበር። የጓደኛዬን ሕይወት ማትረፍ ባይቻልም ቪድዮው በማኅበራዊ ሚዲያ አይሰራጭም ነበር።”
ሮኒ 33 ዓመቱ ነበር። ኢራቅ ውስጥ ወታደር ነበር። ከአስደንጋጭ አጋጣሚ በኋላ የሚከሰት የአዕምሮ ጤና መዛባት ገጥሞተም ነበር።
በቅርቡ ከሴት ጓደኛው ጋር የተለያየው ሮኒ፤ ራሱን ያጠፋ እለት ሲጠጣ ነበር ያመሸው። ራሱን ስለማጥፋት ሲያወራ ሊያስቆሙት ከሞከሩ ሰዎች ጋር ሲጋጭ ነበር። ፖሊሶችም ቤቱ ተገኝተው ነበር።
ሮኒ ራሱን ሲያጠፋ ከ200 በላይ ሰዎች በቀጥታ ተመልክተዋል። ሞቱ በነጋታው ራሱን ሲያጠፋ የሚታይበት ተንቀሳቃሽ ምስል ተቆራርጦ መሰራጨት ጀመረ።
“ቪድዮው ማንም ማየት የሚችለው (ፐብሊክ) ነበር። ቪድዮውን እየቆረጡ ያሰራጩ ሰዎች ስለ ሮኒ የተሳሳተ ነገር እየተናገሩ ነበር። ይህም ቪድዮው የበለጠ እንዲሰራጭ አድርጓል” ይላል ጆሽ።
የሮኒ ፌስቡክ ላይ ተገቢ ያልሆኑ መልዕክቶች ይላኩ ነበር። ጆሽ ጉዳዮን ለፌስቡክ ቢያመለክትም፤ የገጹ ባለቤት እሱ ስላልሆነ ምንም ማድረግ እንደማይቻል ገልጸውለታል።
በሌላ በኩል ለሮኒ ማስታወሻ በሚል የገንዘብ ማሰባሰቢያ ገጾች ተከፍተዋል። የሮኒ ቤተሰቦች ስለነዚህ ገጾች የሚያውቁት ነገር የለም።
“ከቁጥጥራችን ወጥቷል። አውስትራሊያ ውስጥ ያለ ሰው የዘጠኝ ዓመት ልጁ የሮኒን ቪድዮ ቲክቶክ ላይ እንዳየ ተናግሯል” ይላል ጆሽ ስለሁኔታው ሲያስረዳ።
ሮኒ ራሱን ሲያጠፋ ቪድዮ በመቅረጹ የሚወቅሱት አሉ። ቪድዮው ላደረሰባቸው ሥነ ልቦናዊ ጫና ሮኒን ተጠያቂ የሚያደርጉም አሉ። ጆሽ ግን በዚህ አይስማማም።
“የቀጥታ ስርጭቱን ሲጀምር ያሰበው ይህን አይመስለኝም። ገጹ ላይ ብዙ ደስ የሚሉ ነገሮች አሉ። በቀጥታ እያሰራጨ ከሰዎች ጋር ያወራ ነበር።”
ከማኅበራዊ ሚዲያ አልጠፋ ያለው ቪድዮ
ጆሽ ጓደኛው ራሱን ሲያጠፋ የሚታይበት ተንቀሳቃሽ ምስል ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ባለመጥፋቱ አዝኗል።
ቪድዮው እየተሳጨ ያለው በሰው ሰራሽ የሐሰት ገጾች (ቡትስ) እንደሆነ ያምናል።
“አንድ ገጽን በተመለከተ ለፌስቡክ ቅሬታ ስናቀርብ ገጹ ተዘግቶ ሌላ ገጽ ይከፈትና ተመሳሳይ መረጃ በስፋት ያሰራጫል።”
ፈርስት ድራፍት ኒውስ ውስጥ የሚሠሩት ክሌር ዋርድል እንደሚሉት፤ ምስሎች ከሚሰራጩበት ምክንያት አንዱ ምስሉ ሰዎችን የሚያስቆጣ ነው ተብሎ ሲታመን ነው።
እንደ ምሳሌ የሚጠቅሱት በኒው ዚላንድ ውስጥ የተከሰተውን የክራይስትቸርች ተኩስ ነው።
ፌስቡክ ሰው ሰራሽ ሐሰተኛ ገጾች በተመለከተ የቀረበለት ጥያቄ ላይ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።
ባወጣው መግለጫ ግን “ቪድዮው በተሰራጨበት ቀን ዋናውን ቪድዮ ከገጹ አውርደናል። ቅጂዎቹንም ለማስወገድ ሞክረናል። ከዚህ በኋላ የቀጥታ ስርጭትን እንዴት በፍጥነት ማስቆም እንደምንችል እናጠናለን። ለሮኒ ቤተሰቦችና ጓደኞች ሀዘናችንን እንገልጻለን” ብሏል።
የጆሽ ትግል
ጆሽ ኢንስታግራም ላይ በጓደኛው ስም የተከፈቱ ሐሰተኛ ገጾች ገጥመውታል።
ዩቲዩብ ላይም ከ500,000 በላይ ሰዎች የተመለከቱት ተንቀሳቃሽ ምስል ይገኛል። ቲክ ቶክ ላይ ቪድዮው ተቆራርጦ እየተሰራጨ ነው።
ዩቲዩብ ሰዎች ራሳቸውን ሲጎዱ የሚያሳይ ቪድዮ የማስወገድ መርህ እንዳለው ይናገራል።
ቲክቶክም እነዚህን ቪድዮዎች ተከታትሎ እንደሚያስወግድ አስታውቋል።
ጆሽ ግን የሮኒ ቤተሰቦች በደረሰባቸው ነገር ልቡ ተሰብሯል። ሰዎች ጭንቅ ውስጥ ሲገቡ እንደ ሮኒ የቀጥታ ስርጭት ከመጀመራቸው በፊት አንዳች እርምጃ መወሰድ እንዳለበትም ያምናል።
“በማንም ቤተሰብ ላይ ይህ እንዲደርስ አልፈልግም። እነዚህ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ሀያላን ናቸው። ለሰዎች ግን ግድ የላቸውም” ይላል።