ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጋዜጣ ፡ ፈትል - የዓይነ ስውራን የብሬል ጋዜጣ
አዲስ አበባ ባለፈው ሳምንት ለየት ያለች አዲስ ጋዜጣ አግኝታለች። ጋዜጣዋ ለዓይነ ስውራን ተብላ የተዘጋጀች [በዳሰሳ የምትነበብ] በብሬል የተጻፈች ስትሆን "ፈትል" ትሰኛለች።
ጋዜጣዋን በባለቤትነት የምታሳትመው ደግሞ ፊዮሪ ተወልደ ስትሆን፤ የአንዷ ጋዜጣ የመሸጫ ዋጋ 30 ብር መተመኑን ትናገራለች።
የጋዜጣዋን ሃሳብ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን እንዲሁም የዓይነ ስውራን ብሔራዊ ማኅበራት መደገፋቸውን ፊዮሪ ለቢቢሲ ተናግራለች።
የጋዜጣዋ የመጀመሪያ ህትመት ባለፈው ሳምንት ለመንግሥት ተቋማትና ለዓይነ ስውራን ብሔራዊ ማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ለማስተዋወቅ በሚል ተሰራጭቷል።
ፊዮሪ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ህትመት ውጤት በሆነው ዕለታዊው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በጋዜጠኝነት ትሰራ ነበር።
አሁን ደግሞ ባዜን የማስታወቂያና ህትመትና ፕሮሞሽን የተሰኘ ድርጅት አቋቁማ "ፈትል" የተሰኘችውን ጋዜጣ ለዓይነ ስውራን ማሳተም ጀምራለች።
ይህችን አዲስና ለየት ያለች ጋዜጣን ለማዘጋጀት ምክንያት የሆናት ቀደም ሲል አራት ኪሎ ወደ ሚገኘው መሥሪያ ቤቷ በመትሄድበት ጊዜ የምትመለከተው ነገር እንደሆነ ታስታውሳለች።
ፊዮሪ፣ በዚያ ወቅት ዘወትር ወደ ሥራ ገበታዋ በምታቀናበት ወቅት አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኙት ካፌዎች ውስጥ ጋዜጣ ይዘው፣ የሚጠጡትን ትኩስ ነገር በማዘዝ የሚያነብቡ ሰዎችን ስትመለከት በውስጧ ጥያቄን ያጭርባታል።
እነዚህ በየዕለቱ የተለያዩ ጋዜጦችን ገጽ የሚያገላብጡ ሰዎች በአገራቸው በዚትዮጵያ ውስጥ እንደሁም በመላው ዓለም ስለተከሰቱ ነገሮች ዜና ፈልገው ብቻ ሳይሆን የሥራ ማስታወቂያም ለመመልከት ነው። ታዲያ ይህንን ዕድል ያላገኙት የኅብረተሰቡ ክፍሎች ነገር ያሳስውባት ነበር።
"በተለይ ደግሞ ዓይነ ስውራን ይህን እድል ተነፍገዋል" ትላለች ፊዮሪ። ስለዚህም እንደ ጋዜጠኛ እድሉን ላላገኙ ሰዎች በቻለችው አቅም እድሉን የማመቻቸት ኃላፊነት እንዳለባት በማመን ለዓይነ ስውራን የሚሆን ጋዜጣን ለማዘጋጀት እንደተነሳች ትናገራለች።
ስለዚህ ጋዜጣው ለዓይነ ስውራን መረጃ ብቻ እንዲያደርስ አልፈለገችም፤ የሥራ እንዲሁም የጨረታ ማስታወቂያዎችን ይዞ ዓይነ ስውራን በአገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ በመረጃ የታገዘና የተጠናከረ እንዲሆን አስተዋጽኦ ለማበርከት በማሰብ ሥራውን ጀመረች።
ፈትል የተሰኘችው ጋዜጣዋም ዜናና መረጃዎችን ከማቅረብ ባሻገር ለዓይነ ስውራን "የኢኮኖሚ ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥም" የራሷ አስተዋጽኦ እንደሚኖራት ትናገራለች።
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ወደ አራት ሚሊዮን ዓይነ ስውራን ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። ከእነዚህ ግለሰቦች መካከል ማየት ብቻ ሳይሆን የመስማት ችግርም ያለባቸው ስላሉ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የሚተላለፉ መረጃዎችን አፍ ተልብ ሆኖ ለመከታተል እድሉን ላያገኙ ይችላሉ።
ስለዚህ እንደ ጋዜጠኛዋ ፊዮሪ ገለጻ "እነዚህን ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው ዜጎች በብሬል ጋዜጣ የመረጃ ተጠቃሚ ማድረግ ችላ ተብሎ ሊታለፍ የሚገባው እድል አይደለም።"
ጋዜጣው ልክ እንደሌሎቹ አቻዎቹ ሁሉ የተለያዩ አምዶችን ይዟል።
ዜና ቀዳሚው ነው፣ ከአይነ ስውራን ጋር በተያያዘ የሚደርሱ የፍትህ መዛባትና መጓደልን በምርመራ ዘገባ የሚያቀርብበት፤ ፈትል ነቃሽ፣ እንግዳ፣ ተምሳሌትና የመሳሰሉ ሁሉን አቀፍ መረጃዎች የሚቀርቡበት ነው።
ከእነዚህ በተጨማሪ ደግሞ ዓይነ ስውር ልጆችን ለመድረስ በማሰብ የልጆች አምድ በጋዜጣዋ ውስጥ ተካቷል። ጋዜጣዋ የምታተመው በኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር በኩል መሆኑንም ፊዮሪ ተናግራለች።
መደበኛ ጋዜጦች ዘወትር ለሥራቸው ፈተና የሆነባቸው እየጨመረ የሚሄድ የወረቀት ዋጋ መወደድ የዓይነ ስውራኑ ጋዜጣ የሆነችው የ"ፈትል"ም ፈተና ነው።
የብሬል ወረቀት በአገር ውስጥ ገበያ ላይ እጅግ ውድ መሆኑን የምትጠቅሰው ፊዮሪ፤ ነገር ግን የጋዜጣዋ መሸጫ ዋጋ ለህትመትና ለወረቀት መግዣ ከሚወጣበት በእጅጉ አንሶ ለገበያ እንደቀረበች ትናገራለች።
ሌላው አብዛኞቹ ዓይነ ስውራን የኢኮኖሚ አቅማቸው አነስ ያለ መሆኑ ጋዜጣዋን በመደበኛው ገበያ ውስጥ አቅርቦ በመሸጥ ስርጭቱን ለማስፋት ተግዳሮት እንዳለባት ጠቅሳለች።
ጋዜጣዋን ለማስተዋወቅና ለዓይነ ስውራን ተደራሽ ለማድረግ አሁን እንደ መፍትሄ ብለው ያስቀመጡት፤ የመጀመሪያው የጋዜጣዋ ዕትም ስርጭት ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ በአገሪቱ በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እንዲሆን ታስቦ ነው።
በተጨማሪም የመንግሥት ተቋማት፣ የዓይነ ስውራን ብሔራዊ ማኅበሩ ዋና ቢሮ እና ቅርንጫፍ ቢሮዎች እንዲሁም ትልልቅ ጋዜጣ የሚሸጥባቸው አደባባዮች ላይ "ፈትል"ን ለማከፋፈል ማሰቧን ትናገራለች።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለዓይነ ስውራን ተማሪዎቻቸውና መምህራኖቻቸው በመግዛት በቢሮዎችና በቤተ መጻህፍት እንዲያስቀምጡላቸው ለመስራት በማሰብ ጥረት መጀመሯንም ገልጻለች።
"ፈትል" ሳምንታዊ የዓይነ ስርውራን የብሬል ጋዜጣ በአሁኑ ጊዜ በአማርኛ ብቻ የምትታተም ሲሆን በቀጣይ በሌሎች የአገሪቱ ቋንቋዎችም የማዘጋጀት ሃሳብ መኖሩንም አዘጋጇ ፊዮሪና ተወልደ ጠቁማለች።