18 ዓመት ሙሉ ከእባብ ጋር በሰላም የኖረው የቦረናው ቤተሰብ

ቦታው ቦረና ዞን ነው። ወረዳው ደግሞ ድሬ። በወረዳው የሚኖሩ ሰዎች ስለ አንድ የእባብ አይነት ሲያወሩ አብዛኛው ሰው እንደሚያስበው በፍርሃት አይደለም።

ልክ እንደ ለማዳ እንስሳ ቀለል አድርገው ነው የሚጠሩት።

ይህ እባብ እንደ ማንኛውም መርዛማ ሲሆን በአገሬው ሰዎች አጠራር (Buutii) ቡቲ ይባላል።

"ለ18 ዓመታት ይህ "ቡቲ" መርዛማ እባብ ከግብያችን ጠፍቶ አያውቅም" ያሉን የቦሮና ዞን ድሬ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ኦቶ ዱባ ዲዳ ናቸው ።

ይህ እባብ አደገኛ መሆኑን የሚናገሩት ግለሰቡ ከተናደፈ ግለሰቡ የመትረፍ እድሉ እጅግ ውስን መሆኑን ይገልፃሉ።

አይደለም ተናድፎ እስትንፋሱ እንኳን አካልን አሳብጦ ለበሽታ እንደሚያጋልጥ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ተናግረዋል።

በቦረና ዞን ድሬ ወረዳ ሜልባና ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት እኚህ ግለሰብ "በሰላም ቀያችን ውስጥ እየኖረ ነው" ሲሉ ለበቢሲ አረጋግጠዋል።

" እኛ ወደ እዚህ የመጣነው ከ18 ዓመት በፊት ይሆናል። እዚህ ከሰፈርን ጊዜ ጀምሮ ግቢያችን ውስጥ ይኖራል። በእኛው ግቢ ውስጥ ይገባል፤ እዚሁ ውሎ እዚሁ አድሮ አብረን ወጥተን እየገባን ነው።"

አቶ ዱባ እንደሚሉት ከሆነ እንዲህ ዓይነት መርዛማ እባብ ወደ ሰው ቀዬ ከመጣ አይገደልም።

ምክንያቱ ደግሞ እንደእርሳቸው አባባል እባቡ በቀለኛ መሆኑ ነው።

ይህ እባብ ሰውን ይበቀላል ተብሎ ይታመናል "በቀለኛ ነው" ይላሉ አቶ ዱባ።

" አንገድልም። ከገደልን ሰውን ያጠቃል፤ ይበቀላል፤ አሁን ለምሳሌ ቀያችን ውስጥ ያለውን ብንገድል ሌላ 'ቡቲ' መጥቶ የኛን ሰው ይበቀላል። እንደዚህ አይነት ነገር "የቁምቢ በቀል ይባላል።" ይላሉ አቶ ዱባ።

" ከዚህም በፊት ልጆቻችን እኛ ሳናይ አንድ የ'ቡቲ' ልጅ ገድለው ነበር' ከዚያም በኋላ አንድ ወይፈናችንን ነድፎ ገደለ" በማለት መግደል ያለውን ጦስ ይናገራል።

ይህ እባብ በቀያቸው ውስጥ በኖረበት በእነዚህ 18 ዓመታት በሰላም አብሮ መኖር እንጂ ምንም ዓይነት ፍራቻና ስጋት እንደሌላቸው ይናገራሉ።

"ምንም ስጋት የለብንም ፈጣሪ ነው ይከላከልልናል" አሉ።

እንደ አቶ ዱባ ከሆነ በአሁን ሰዓት በቀያቸው ያለው ይህ እባብ በውፍረት ከሌሎች እባቦች የሚበልጥ ሲሆን ርዝመቱም ሁለት ክንድ ያክላል።