ኢንስታግራም ለአዳዲስ ተመዝጋቢዎች እድሜን ሊጠይቅ ነው

ኢንስታግራም በአባልነት የሚቀላቀሉትን አዳዲስ ግለሰቦች የትውልድ ቀናቸውን እንዲያስገቡ ሊጠይቅ መሆኑ ተሰማ። ለዚህም ምከንያቱ ነው የተባለው እድሜን ያገናዘቡ ምስሎችን ለማጋራት እንዲያስችለው መሆኑ ተገልጿል።

ምስል የሚጋሩበት ይህ የማህበራዊ ሚዲያ አባላቱ የራሳቸው አካውንት እንዲኖራቸው ቢያንስ እድሜያቸው 13 እንዲሆን ይጠይቅ ነበር።

የትልውልድ ቀንን መጠየቅ ኩባንያው እድሜን መሰረት ያላደረጉ ማስታወቂያዎች ለልጆች እንዳይደርሱ ማድረግ ያስችለዋል ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ኢንስታግራም ግን ማስታወቂያ ከለውጡ ጀርባ ያለ ምክንያት አይደለም ሲል አስታውቋል።

ኩባንያው "ዕድሜ መጠየቃችን በእድሜ ትንንሽ ልጆች ይህንን ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይቀላቀሉ ለመከላከል፣ ታዳጊዎች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን፣ እንዲሁም እድሜያቸውን ያገናዘበ አጠቃቀም እንዲኖር ለማድረግ ይረዳል" ሲል በጡመራ ገፁ ላይ አስታውቋል።

" ለእኛ የምታጋሩንን የልደት ቀናችሁን ተጠቅመን፣ በእድሜያችሁ ልክ የተመጠነ አጠቃቀም እንዲኖራችሁ እንሰራለን፤ ለምሳሌ ለታዳጊዎች እንዴት የግል መረጃቸውንና ገፃቸውን መጠበቅና መከላከል አንደሚችሉ ትምህርት መስጠት" ሲልም ያክላል።

መረጃው ኢንስታግራምን ለአዋቂዎች የሚለቃቸውን የቁመራ፣ አልኮሆል መጠጦች፣ እና የወሊድ መቆጣጠሪያን የተመለከቱ መልዕክቶች ለልጆች እንዳይደርሱ ለማድረግ ይረዳዋል።

ኩባንያው በሚቀጥሉት ሳምንታት ወጣቶች የግል መረጃቸውን ደህንነት የሚጠብቁበትን ክፍል እንዲከፍቱት ያበረታታል።

" በእድሜ ከፍ ያሉ ተጠቃሚዎች ለስራችን አስፈላጊ በመሆናቸው እድሜን ያማከለ ልምድ እንዲኖር ማድረግ ብቻ ሳይሆን ለረዥም ጊዜ አብሮን የኖረውን መመሪያ በማክበር አንዳንድ መልዕክቶች ለታዳጊዎች እንዳይደርሱ መከላከል ያስችለናል" ሲሉ የኢንስታግራም ምርቶች የበላይ ኃላፊ ቪሻል ሻህ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ኢንስታግራም እስካሁን ድረስ አዳዲስ አባላቱ አካውንት ሲከፍቱ እድሜ አይጠይቅም፤ እንዲሁም ፌስቡክ በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ይህ የማህበራዊ ሚዲያ ገፅ፤ አባላት ያስገቡት የልደት ቀን እውነት መሆኑን አያረጋግጥም ነበር።

በልጆች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች የኢንስታግራምን ውሳኔን ሲተቹ "ተጣርቶ ለማይገኝ፣ ተጠቃሚዎች የልደት ቀን መጠየቃቸው ልጆችን እድሜ ተኮር የሆነ ልምድ እና አጠቃቀም እንዲኖራቸው እንዲሁም ለመከላከል ነው የሚሉት ምክንያቶች ውሃ አያነሱም" ብለዋል።

ወደፊት የሚወጡ አዳዲስ የአጠቃቀም መመሪያዎች ሕጻናትና ታዳጊዎች በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ተጨማሪ ከለላ እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል።

ነገር ግን የማህበራዊ ሚዲያዎች መጀመሪያውኑ ሕጻናት ሊጠቀሟቸው የሚችሏቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋልም ብለዋል።

ፌስቡክ በበኩሉ "ሁሉም ሰው እድሜውን በትክክል እንደማይሞላ እንረዳለን። በኦንላየን ተጠቃሚዎችን እድሜ እንዴት መሰብሰብና የተሻለ ማጣራት እንደሚቻል በዘርፉ ላይ የተሰማሩ በሙሉ እየሰሩበት ያለ ነው። እኛም መንግስትም የተሻለ ነው የምንለውን መንገድ ለመፈለግ እየሰራን ነው" ሲል ገልጿል።

የየትኛውም ኢንስታግራም ተጠቃሚ እድሜው በገፁ ላይ ለተጠቃሚዎች ፊት ለፊት እንዲታይ አይደረግም።