" 'ፖስት ፒል' ብወስድም አረገዝኩ"

"እስከዛች እለት ድረስ ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ (ፖስት ፒል) ላይሠራ ይችላል የሚል ቅንጣት ጥርጣሬ አልነበረኝም።"

ሬቸል (ስሟ ተቀይሯል)፤ አንድ ዓመት ከዩኒቨርስቲ እረፍት ወስዳ ካናዳ በነበረችበት ወቅት ነው የተደፈረችው። ጥቃቱ በደረሰባት በዛው እለት ምሽትም ነው ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ እንክብል የተሰጣት።

"ከሁለት ወራት በኋላ ማርገዜን ተረዳሁ፤ በጣም ነው የደነገጥኩት፤ በጭራሽ አረግዛለሁ የሚል ሃሳብ ጭንቅላቴ ውስጥ አልነበረም።"

የ34 ዓመቷ ሬቸል ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ እርግዝናን ላይከላከል እንደሚችል ፍንጭ የሰጣትም አካል አልነበረም። "ውጤታማ ላይሆን ይችላል የሚለው እሳቤ ሲነሳ ራሱ ሰምቼ አላውቅም" ትላለች።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያን ከሚወስዱት መካከል ከ0.6-2.6% የሚገመቱት ሴቶች ያረግዛሉ።

ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ (ፖስት ፒል) እንክብል ከተወሰደ በኋላ እርግዝና ሊያስከትል እንደሚችል መነጋገሪያ የሆነው አንዲት ጦማሪ እንክብሉን ብትወስድም እንዳረገዘች መፃፏን ተከትሎ ነው።

ፅሁፏ ከፍተኛ የመወያያ ርዕስ የሆነ ሲሆን፤ እንክብሉ አንዳንድ ጊዜም ቢሆን ሊሠራ እንደማይችል በደንብ ሊታወቅ ይገባል የሚሉ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።

ጦማሪዋ በፅሁፏ ላይ እንዳሰፈረችውም፤ ከውፃት (ኦቩሌሽን) በኋላ አንዲት ሴት ጥንቃቄ የጎደለው ወሲብ ፈፅማ እንክብሉን ብትወስድ ምንም ትርጉም እንደሌለው የተረዳችው በቅርቡ ነው።

ይህንን መረጃ ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ የሚያመርቱ ኩባንያዎች በሰፊው የማሳወቅ ሥራ ሊሠሩበት የሚገባ ነው ብላለች።

ኮንዶም በመቀደዱ ምክንያት ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ብወስድም ማርገዜ አልቀረም፤ እናም ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ ምርመራዬን ጀመርኩ ብላለች።

ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ የሚሠራው እንዴት ነው?

  • ፖስት ፒል፤ ሲንተቲክ ሆርሞን የያዘ ሲሆን ውፃት (እንቁላል ከማህፀን የሚወጣበት) ወቅትን ያዘገያል
  • እንክብሉን ሲወስዱ ውፃት ተከናውኖ ከሆነና ጥንቃቄ የጎደለው ግንኙነት ከፈፀሙ እርግዝናን አይከላከልም
  • ምንም እንኳን ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ቢወስዱም ውጤታማ ላይሆን ይችላል
  • ውፃት የሚከናወነው የወር አበባዎትን ካዩ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ነው
  • ሌቮኖጀስትሬል እና ዩሊፕሪስታል አሴቴት የሚባሉ ሁለት ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ እንክብል አይነቶች አሉ
  • ሌቮኖጀስትሬል ጥንቃቄ የጎደለው ግንኙነት ካደረጉ በሰባ ሁለት ሰዓታት (በሦስት ቀናት) ውስጥ መወሰድ አለበት
  • ዩሊፕሪስታል ንቃቄ የጎደለው ግንኙነት ካደረጉ በ120 ሰዓታት (በአምስት ቀናት) ውስጥ መወሰድ አለበት

ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ መድኃኒቶች በእንክብሉ መሥራት አለመሥራት ላይ ተፅእኖ እንደሚያደርሱ የሥነ ተዋልዶና የጤና ባለሙያዋ ዶክተር ካሮሊን ኩፐር ይናገራሉ።

"እነዚህ መድኃኒቶች ከጉበት መድኃኒት ጋር ጣልቃ ይገባሉ" በማለት ዶክተሯ ገልፀው፤ እነዚህ መድኃኒቶች የኤችአይቪ፣ የሚጥል በሽታ እንዲሁም አንዳንድ ባህላዊ መድኃኒቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ሙያዊ አስተያየቶቻቸውን ሰጥተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ሊሠራ የማይችልበት ሌላኛው ምክንያ፤ የሴቲቷ የሰውነት ክብደት እንደሆነ ዶ/ር ኩፐር ያስረዳሉ። የሰውነት ክብደታቸው በጣም ከፍተኛ የሆነ ሴቶች ድንገተኛ እርግዝና መከላከያ ቢወስዱም ሊያረግዙ እንደሚችሉ ዶክተሯ ይናገራሉ።

ግን ምን ያህል ሴቶች ስለዚህ ሁኔታ መረጃ አላቸው? የሌቭኔልም ሆነ ኤላዋን በራሪ ወረቀቶች የሚሰጡት መረጃ ውፃትን (ኦቩሌሽን) በማዘግየት እንክብሎቹ እንደሚሠሩ ቢሆንም የማያዩት ብዙዎች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም የመድኃኒቱ መሥራት አለመሥራት በወር አበባ ዑደት ዙሪያ ሊደናቀፍ እንደሚችልም ግልፅ ያለ መረጃ አይሰጥም።

ታዲያ ለምንድን ነው ማንኛዋም ሴት ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ (ፖስት ፒል) ስትገዛ ይሄ ሁሉ መረጃ የማይሰጣት?

"እንክብሎቹ አይሠሩም ብዬ አልሜ አላውቅም" ትላለች የ26 አመቷ ሃሪየት፤ ኮንዶም ቢቀደድባትም ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ስለወሰደች አረግዛለሁ ብላ አልጠበቀችም።

ያልጠበቀችው ሆነና አረገዘች። እሷ እንደምትለው በትክክል እንክብሎቹን ወስዳለች።

ሃሪየት እንደተነገራትም እንክብሎቹ ረዘም ያለ ጊዜ ከተጠበቀ እንደማይሠሩ ነው። ነገር ግን እሷ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ስለወሰደች አላስጨነቃትም ነበር። ከሳምንት በኋላ ግን ማርገዟን ተረዳች።

ለሬቸል ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ እንደማይሠራ ማወቋ ያለችበትን ሁኔታ ባይቀይረውም፤ የአስራ አምስት አመት ልጅ እንዲኖራት አድርጓል። "እርግዝናዬ በጭራሽ ያልጠበቅኩት ነው። የሆነውን ነገር በፍፁም ባልቀይረውም ልጄን አልወልደውም ነበር" ትላለች።

የቢቢሲ ጋዜጠኛ ዶ/ር ኩፐርን የወር አበባ ዑደት በድንገተኛ እርግዝና መከላከያ ውጤት ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ በፋርማሲስቶች ወይም በህክምና ባለሙያዎች ይነገራቸዋል ወይ? ብላ ለጠየቀቻት ጥያቄ "መንገር አለባቸው፤ ግዴታም ሊሆን ይገባል" ትላለች።

ሌላኛው ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ኮፐር ኢንትራዮትሪን ዲቫይስ (አይዩዲ) ነው። ያለ ጥንቃቄ ግብረ ሥጋ ግንኙነት በተፈፀመ በአምስት ቀናት ውስጥ በብልት ውስጥ ይገባል።

ፖስት ፒል ውፃትን የሚያዘገዩ ሲሆን፤ ኮፐር አይዩዲ ደግሞ የተመረተ እንቁላል ማህፀን ውስጥ እንዳይቆይ ያደርገዋል፤ ውጤታማነቱም 99% ነው።

ኤላዋንን ከሚጠቀሙ 100 ሴቶች መካከል ሁለቱ ያረግዛሉ፤ እንዲሁም ከሌቮኔል ተጠቃሚዎች መካከል በአማካይ 0.6-2.6 ፐርስንቱ የማርገዝ አጋጣሚዎች አሏቸው።

ሬቸልም ሆነ ሃሪየት ኮፐር አይዩዲ እንደ አማራጭ እንዳልቀረበላቸው ይናገራሉ።

የሥነ ተዋልዶ ጤና ባለሙያዋ ዶ/ር ጄይን ካቫንጋህ፤ ለዚህ ሁሉ መፍትሔ የሚሆነው ስለ ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያም ሆነ ስለ እርግዝና መከላከያ አወሳሰድ በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ ሊካተት ሲችል ነው ይላሉ።

"እንዴት ነው ሁሉም ተማሪ ስለ እርግዝና መከላከያ የማይማረው? የግብረ ሥጋ ግንኙነት አድርገው ሊያረግዙ የሚችሉበት አጋጣሚ ቢፈጠር ምን ያደርጋሉ? ማወቅ አለባቸው" ይላሉ።

በተለያዩ ጊዜዎች ያነጋገረቻቸው ተማሪዎችም ብዙዎቹ ስለ ድንገተኛ እርግዝና መከላከያ እንደማያውቁ ከውይይቱ መረዳት ችለዋል ባለሙያዋ።

ስለ ድንገተኛ እርግዝና መከላከያ ሴቶች ብቻ ሳይሆኑ ወንዶችም ሊያውቁ እንደሚገባ ሃሪየት ትናገራለች።