ሻደይ፦ለሴቶች፣ በሴቶች ፌስቲቫል

በየአመቱ ከነሐሴ 14 ጀምሮ ለሶስት ቀናት በአማራ ክልል በሰቆጣ፣ በላሊበላና በቆቦ አካባቢ እንዲሁም በትግራይ ክልል የሚገኙ ሴቶች በመንገዶችና አደባባዮች ላይ በመውጣት ነፃነታቸውን የሚያውጁበት እንደሆነ ይነገራል።

በአማራ ክልል ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፤በትግራይ ክልል አሸንዳ ክብረ በዓል ሴቶችን ማዕከል ያደረገ፤ ለሴቶችና በሴቶች የምትዘጋጅ ክብረ በዓል ናት።

ሴቶች ያለምንም ተፅእኖ የሚጫወቱበት ባህል እንደሆነ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ቸኮሉ በለጠ ይናገራሉ።

ቤተሰቦች አልባሳትንና ጌጥን ከመግዛት ጀምሮ፣ በባህሉ ለሴቶች ብቻ ተብሎ የተተወውንም የቤት ስራም ለሶስት ቀናት ያህል በሻደይ ለመስራት አይገደዱም ይላሉ።

"በሶስቱ ቀናት ሴቶች ነፃ ሆነው መጫወት ብቻ ነው ያለባቸው" ይላሉ።

የበዓሉ አከባበር

ሻደይ የሚለው ቃል አገውኛ ሲሆን የቅጠል ስያሜ ነው የሚሉት ወይዘሮ ቸኮሉ አሸንዳ/ አሸንዳየ/ ከሚሉት ሌሎች ስያሜዎች ጋርም የበዓሉ አከባበሩም ሆነ መነሻው ተመሳሳይነት አለው ይላሉ።

ዝግጅቱ የሚጀምረው ከሳምንት በፊት ሲሆን የአንድ ሰፈር ሰዎች በመሰባሰብ፣ የሚለብሷቸውን አልባሳት መምረጥ፣ ጌጣጌጦችን በመግዛትና በመጨረሻም ቡድኑን የሚያስተባብር አንድ ሰብሳቢም በመምረጥ ይጀመራል።

አከባበሩ በሶስት የእድሜ እርከን ተከፍሎ የነበረ ሲሆን እስከ 10 አመት ዕድሜ ያላቸው ህፃናት፤ ከ10-15 አመት ድረስና ከ15 አመት በላይ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ለህፃናት የተተወ መሆኑን ይናገራሉ።

ከ15 አመት በላይ የሆኑት ድኮት (የእጅ አምባር)፣ ሁለት አይነት መስቀል፣ በአንገታቸው ድሪ፣ የብር አልቦ እግራቸው ላይ ያጠልቃሉ፤ በጥልፍ ቀሚስ ተሽቆጥቁጠው ይሄዳሉ።

ከ15 አመት በታች የሆኑት ከብር የተሰራ ድሪ፤ ትልልቅ ክብ ቀለበት ጆሮ ጌጥ፤ ከ10 አመት በታች የሆኑት ቁንጮና ጋሜ (መሀል ፀገራቸው ተላጭቶ ዳርዳሩን ያደገ) የፀጉር ቁርጥ ይቆረጣሉ።

ጉዟቸውንም የሚጀምሩት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ነው ሲሆን በቀድሞው ጊዜ ወደ አካባቢው አስተዳደር ወይም አገረ ገዥው ይሄዱ እንደነበር ወይዘሮ ቸኮሉ ያስታውሳሉ።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢያቸው ያሉ ትልልቅ ሰዎች ቤት በመሄድ ዘፈናቸውን ይጀምራሉ።

"አስገባኝ በረኛ፣ አስገባኝ ከልካይ፤ እመቤቴን ላይ" በማለት ማንጎራጎር ሲጀምሩ በሩ ይከፈትላቸዋል " ይሄ የማን አዳራሽ የጌታየ የድርብ ለባሽ፤ ይሄ የማን ደጅ የእመቤቴ የቀጭን ለባሽ" በማለት ዘፈናቸውን ይቀጥላሉ።

በእለቱ ከሚዘፈኑ ዘፈኖች መካከል በሰቆጣ ከተማ ታዋቂው ዘፈን "አሽከር አበባየ አሽከር ይሙት፣ ይሙት ይላሉ የኔታ አሽከር አይደለም ወይ የሚሆነው ጌታ"እንደሆነ ወይዘሮ ቸኮሉ ይገልፃሉ።

በር ተከፍቶላቸው ከገቡ በኋላ የቤቱን ባለቤቶች ማወደስ ይጀመራል።

ከውደሳዎቹም መካከል "ከፈረስ አፍንጫ ይወጣል ትንኝ፤ እሰይ የኔ ጌታ ጤና ይስጥልኝ፤ ምድር ጭሬ፣ ጭሬ አወጣሁ ማሰሮ እሰይ የኔ እመቤት ድልድል ወይዘሮ" ይገኙበታል።

ይቀጥሉናም "ስለለየ፣ ስለለየ ....እሰይ የኔ እመቤት የፈተለችው ሸማኔ ታጥቶ ማርያም ሰራችው" በማለት ያንጎራጉራሉ።

ዘፍነው ሽልማት ካልተሰጣቸው ወይ ከዘገየ "አንቱን አይደለም የማወሳሳው፤ ቀና ብለው እዩኝ የሰው ጡር አለው" ብለው በነገር ሸንቆጥ ያደርጓቸዋል።

በዚያን ቀን ያው ሽልማት መስጠት ግድ ነው፤ እሱን ተቀብለው "አበባየ ነሽ አበባየ ጉዳይ ሰመረች በአንች ላይ" እያሉ ወደ ሌላ መንደር ይሄዳሉ።

በአራተኛው ቀን በተለያዩ ሰፈሮች ያሉ ሴቶች ተሰብስበው በግጥምና በዜማ ውድድር እንደሚጀምሩ ወይዘሮ ቸኮሉ ይናገራሉ።

ህዝብ በተሰበሰበት ቦታም በዘፈን ከሚገጠሙት መካከል " የቀሃ ገብርኤል ልጅ የሰራችው ዶራ ኩኩ ብሎ ወጣ መጉላሊቱን ሰብሮ" በማለት ሲዘፍኑ በምላሹ " የመከንዝባ ልጅ መጣች ተመልሳ፤ ከወገቧ በላይ አመድ ተለውሳ፤ከወገቧ በታች አቡጀዲ ታጥቃ" ይሉና ተመራርቀው፣ ተቃቅፈው ይለያያሉ።

የበዓሉ መሰረት

ክብረ በዓሉ ባህላዊና ኃይማኖታዊ መሰረት እንዳለው ወይዘሮ ቸኮሉ ይነገራሉ። መነሻውም አንድ የእስራኤል ንጉስ ጠላቴን አሸንፌ ከመጣሁ መጀመሪያ ያገኘሁትን መስዋዕት አደርጋለሁ ብሎ ቃል ገባ።

አሸንፎ ሲመጣ የተቀበለችው አንዷ ልጁ ሆና ተገኘች። አባትው ቢያዝንም ልጁ እንዳፅናናችው የምትናገረው ወይዘሮ ቸኮሉ "ልጃገረድ ስለነበረች ከጓደኖቼ ጋር ተራራ ላይ ተጫውቼ ልምጣ ብላ ተጫውታ መስዋዕት ሆነች" ይላሉ።

ክብረ በዓሉም ልጅቷ ለሶስት ቀናት ያህል የተጫወተችበትን ማስታወሻ እንደሆነ ይናገራሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ክብረ በዓሉ መፅሐፍ ቅዱስንና ትውፊቶችን በማጣመር ማርያም በምታርግበት ወቅት ለሐዋርያት የተገነዘችበትን ሰበን (ቅጠል) የሰጠቻቸው ማስታወሻ እንደሆነ ይናገራሉ።

ከትውልድ ትውልድም የተለያዩ ትውፊቶች እየተጨመሩበት ለማስታወሻነትም ቅጠሉን ሴቶች በጀርባቸው በኩል አስረው እንደሚጫወቱ ወይዘሮ ቸኮሉ ይናገራሉ።

በአመታት ውስጥ አከባበሩ ቀዝቅዞ የነበረ ሲሆን በባለፉት ጥቂት አመታት ብቻ እንደ አዲስ መከበር እንደጀመረ ይናገራሉ።

"የባለፉትን ሃያ አመታት የነበረው ትውልድ ትውፊቱን ዘንግቶታል፤ እየደበዘዘ ነበር" ይላሉ።

ይህ ፅሁፍ የወጣው ከሶስት አመት በፊት ነው