ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስለ ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት አገራትና ተቋማት ምን አሉ?
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት መጀመሯን ተከትሎ ግብፅ የቀጠናውን መረጋጋት አደጋ የሚጥል ነው በማለት እርምጃውን ተቃውማዋለች።
ለአመታት ያህል በግብፅ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ሲደረግ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር ፍሬ ሳያፈራ የቀረ ሲሆን ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌቱን ተከትሎ ግብፅ ለተመድ የፀጥታ ጉባኤ ምክር ቤት ደብዳቤ መፃፏን አስታውቃለች።
በሱዳን የሚገኙት የኢትዮጵያ አምባሳደር እሁድ እለት እንዳሉት ግብጽና ሱዳን የሦስቱ ዓመት የሕዳሴ ግድብ ሙሌት ዝርዝር መረጃ እንዳላቸው ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ዘገባው ጨምሮም አገራቱ ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት ጉባኤ መውሰድ እንደማይገባቸውና ይህ ጉዳይ የሰላምና የጸጥታ ጉዳይ አይደለም በማለት አምባሳደሩ መናገራቸውን አስነብቧል።
ለመሆኑ የተለያዩ አገራትና ተቋማት በሙሌቱ ዙሪያ ምን አስተያየት አላቸው?
ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጀመሯን በይፋዊ ደብዳቤ እንዳስታወቀቻቸው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የተደራዳሪ ከሚቴ አባል ፕሮፌሰር ይልማ ስለሺ አስታውቀዋል ሲል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ ይህንን መሰረት ያደረገችው በአውሮፓውያኑ 2015 በሦስቱ ሀገራት መካከል በተደረሰው የመርሆ ስምምነት መሠረት ግብፅና ሱዳን ለዝግጅት እንዲያመቻቸው ሲባል ነው።
መሰረታዊ መረጃ ቦታው ድረስ ሂደው የማየት፣ አብረው መወያየት እና ባለሙያዎቹ አብረው እንዲነጋገሩ የማድረግ ሥራዎች ባለፉት አስርት አመታት ከውሃ ባለሙያዎች፣ ከፖለቲከኞች እንዲሁም ከዲፕሎማቶች ጀምሮ ስናደርገው የከረምነው ነው ያሉት ፕሮፌሰር ይልማ፤ ኢትዮጵያ በይፋዊ ደብዳቤ የሰጠችው መረጃም በዚህ መርህ የተመርኮዘ እንደሆነና ይህም የመረጃ ልውውጥ አንዱ አካል ነው ሲሉ አብራርተዋል።
አገራቱም ይህን በመገንዘብ በእነሱ በኩል የሚያስተካክሉትን ጉዳዮች ሲያስተካክሉ ነበር ያሉት ፕሮፌሰር ይልማ፤ አገራቱ በስምምነታቸው መሰረት ግድቡ ሐምሌና ነሐሴ ላይ እንደሚሞላ ያውቁታል ግን ማረጋገጫ እንዲሆናቸው ተነግሯቸዋል ብለዋል፡፡
ሐምሌና ነሐሴ ይሞላል የሚለውን መረጃ አስቀድመው በተጨባጭ አውቀው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴራቸው በኩል ሙሌቱ አይጎዳንም፤ ለዚህም እየተዘጋጀን ነው ሲሉ መደመጣቸውን ፕሮፌሰር ይልማ አስታውሰዋል።
የውሃ ሙሌቱ የማይካሄድ ቢሆን ኖሮ የቅድሚያ ዝግጅቱ ለወጪና ለኪሳራ ስለሚዳርጋቸው ዝግጅት ማድረግ አያስፈልጋቸውም ነበር ሲሉም ፕሮፌሰር ይልማ አክለዋል፡፡
ግብጽ
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት መጀመሯን ተከትሎ ግብጽ የቀጠናውን መረጋጋት አደጋ የሚጥል ነው ስትል እርምጃውን ተቃውማለች።
የግብጽ የመስኖ ሚኒስትር መሐመድ አብደል አቲ ከኢትዮጵያ በኩል የውሃ ሙሌቱ ስለመጀመሩ የሚገልጽ ይፋዊ ደብዳቤ እንደደረሳቸው አመልክተው ውሳኔውን ግን አንቀበለውም ብለዋል።
ሚኒስትሩ ባወጡት መግለጫ "የተናጠል ውሳኔው" የዓለም አቀፍ ሕጎችን የሚጥስ እንዲሁም የናይል ወንዝን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ወንዞች ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን አሠራርም ያላከበረ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ የወሰደችውን እርምጃም በተመለከተ ሚኒስትሩ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት ደብዳቤ መጻፋቸው በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።
ቱኒዝያ
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምትገነባውን ግዙፍ ግድብ የውሃ ሙሌት እንድታቆም ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ቱኒዝያ ማቅረቧን የዲፕሎማቲክ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
ግድቡ በሃገራቱ መካከል አለመግባባትን የፈጠረ ሲሆን ግብጽ እና ሱዳን እንደሚሉት አዲስ አበባ ግድቡን ከመሙላቷ በፊት አሳሪ የሆነ ስምምነት እንዲደረስ ሲጠይቁ የቆዩ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን እንዲያየው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኤኤፍ ፒ ባገኘው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ መሠረት "ግብጽ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ በጋራ በሚገኙበት ድርድሩን እንደገና እንዲጀምሩ ጥሪ ያቀርባል፡፡ በግድቡ ሙሌት እና አሠራር ላይ አስገዳጅ የሆነ ስምምነት በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ እንዲደረስም" ይላል፡፡
የውሳኔ ሃሳቡ አክሎም ስምምነቱ "በታችኛው የተፋሰሱ አገራት የውሃ ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስ በመከላከል ኢትዮጵያ ከግድቡ ኃይል የማመንጨት አቅሟን ማረጋገጥ አለበት" ይላል።
ሦስቱ አገራት ማንኛውንም መግለጫ ከመስጠት ወይም የድርድር ሂደቱን አደጋ ላይ ከሚጥል ማንኛውንም እርምጃ እንዲቆጠቡ ያሳስባል። ኢትዮጵያም በተናጠል ግድቡን ከመሙላት ያሳስባል።
ኢትዮጵያ እና አረብ ሊግ
የአረብ ሊግ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን በመቃወም ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ፅፋለች።
የውጪ ጉዳይ ሚንስትር በማኅበራዊ ድረ ገጾቹ ይፋ እንዳደረገው፤ ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ አገራት በግድቡ ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸውን ተቃውማለች።
ሊጉ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ አስገብቶ የግድቡን ግንባታ በተመለከተ ጣልቃ እንዲገቡ ጠይቋል። ይህንን ጥያቄ ተከትሎ ኢትዮጵያ ጥያቄውን በመቃወም ነው ማስገባቷ የተገለጸው።
ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን ሰኔ 28/2013 ዓ. ም ለጸጥታው ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ፤ የአረብ ሊግ የሕዳሴ ግድቡን በተመለከተ የጣልቃ ገብነት መብት ሳይኖረው ለተባበሩት መንግሥታት ደብዳቤ በመጻፉ ኢትዮጵያ ተቆጥታለች ብለዋል።
"የአረብ ሊግ አገራት አባይን በተመለከተ ግብፅ የምትለውን ማንኛውንም ነገር ሳያመዛዝኑ ሲቀበሉ የመጀመሪያቸው አይደለም" ይላል የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ያወጣው መግለጫ።
ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን የታላቁ ሕዳሴ ግብድ ግንባታን በተመለከተ በአፍሪካ ሕብረት አማካይነት የሦስትዮሽ ውይይት እያደረጉ ባሉበት ወቅት የአረብ ሊግ ጣልቃ ገብነት ተገቢ አለመሆኑ ለጸጥታው ምክር ቤት በተጻፈው ደብዳቤ ተጠቁሟል።
የአረብ ሊግ የሚከተለው መንገድ በአፍሪካ ሕብረት እና በሊጉ መካከል ያለውን ወዳጅነት እንዲሁም ትብብር አደጋ ውስጥ የሚጥል እንደሆነም ተመልክቷል።
"የአፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያ፣ የግብጽ እንዲሁም የሱዳንም ነው። ሁሉም አካል ተጠቃሚ መሆን በሚችልበት መንገድ ላይ የሦስትዮሽ የድርድር መድረክ ዘርግቷል። ይህም ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለውን አካሄድ የተከተለ ነው" ይላል ደብዳቤው።
አሜሪካ
ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ማከናወን ከጀመረች በኋላ አሜሪካ በህዳሴው ግድብ ምክንያት ውዝግብ ውስጥ የገቡ ሁሉም ወገኖች ውጥረትን ከሚፈጥሩ ከማንኛውም የአንድ ወገን እርምጃዎች እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርባለች፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ እንዳሉት ኢትዮጵያ ግድቡን መሙላት መጀመሯን ማስታወቋ ውጥረትን የመቀስቀስ አቅም አለው ብለዋል፡፡
"በእርግጥ የአባይ ውሃ ለሦስቱም ሀገሮች ያለው ጠቀሜታ ስለምንገነዘብ ፍሬያማ፣ ጠቃሚ እና ገንቢ ውይይት እንዲጀመር ማበረታታታችንን እንቀጥላለን" ብለዋል፡፡ አሜሪካ ዘላቂ መፍትሔ ላይ አንዲደረስ ለሚመለከታቸው አካላት ትብብር እና ገንቢ ጥረቶችን ለመደገፍ ምታደርገውን ጥረት ትቀጥላለች ብለዋል፡፡
ውጥረትን በማርገብ እና የቀጠናዊ ትብብርን በማሳደግ ውጤታማ ድርድሮችን ለማካሄድ ያለመውን እና በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን ድርድርም አሜሪካ እንደደገፈች ፕራይስ ተናግረዋል፡፡
"ሁሉም ወገኖች ውጥረቶቹን ከፍ የሚያደርግ፣ አሁን ከተደረሰበት ደረጃ የሚያራርቅ እና በሠላማዊ መንገድ ገንቢ የሆነ መፍትሔን የሚያስቀርን ማንኛውንም የአንድ ወገን እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠቡ ጥሪ እናቀርባለን። በሁሉም ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ለማምጣት ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጥሪ እናቀርባለን"ሲሉ አክለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማክሰኞ ዕለት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በግዙፉ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ዙሪያ ወደ ውይይት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቦ ማናቸውም የአንድ ወገን እርምጃ እንዳይወሰዱም አሳስቧል፡፡
የድርጅቱ የጸጥታው ምክር ቤት በሱዳንና በግብጽ ጥያቄ መሠረት በዚህ ሳምንት እንደሚወያይ ይጠበቃል ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የአፍሪካ ህብረት ሀገራቱን በማስማማት ረገድ የሚጫወተውን ሚና እንደሚደግፉ ቃል አቀባያቸው ስቴፋን ዱጃሪክ ለጋዜጠኞች ኒው ዮርክ ውስጥ ተናግረዋል፡፡
"አስፈላጊው ነገር ማንኛውንም መፍትሔን የሚያደናቅፍ የተናጠል እርምጃ አለመኖሩ ነው። ስለዚህ በእውነተኛ ሂደት በመተማመን ለመሥራት እንደገና መመለሳቸው አስፈላጊ ነው "ሲሉ ዱጃሪክ ተናግረዋል፡፡