በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚደረገው ድርድር፡ የግብፅ ፍላጎትና የኢትዮጵያ ውሳኔ

በአሜሪካና በዓለም ባንክ አሸማጋይነት ሲደረግ የነበረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ፍሬ አለማፍራቱን ተከትሎ ዳግም የሦስትዮሽ ድርድሩ በበይነ መረብ የቪዲዮ ኮንፈረንስ ለአምስት ቀናት ያህል ተካሂዷል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌትና ዓመታዊ የውሃ አለቃቅን በተመለከተ ሦስቱ አገራት የሚያደርጓቸው ውይይቶች ከመቋጨታቸው በፊት ኢትዮጵያና ግብፅ ለድርድሩ አለመሳካት ምክንያት እርስ በርስም እየተወነጃጀሉ ነው።

ሰኞ ዕለትም ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት የሦስቱ አገራት ጥቅም በምን መልኩ ይሆናል የሚለው ላይ የተወያዩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሉ አቅም እየተጠቀመች ድርቅ ቢያጋጥም ችግሩ የሦስቱም አገራት ኃላፊነት ነው የሚል አቋም ላይ መድረሷንም የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መግለጫ አስረድቷል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ትናንት አመሻሽ ላይ በሰጡት መግለጫ ግብፅ ግትር ያለ አቋም በመያዟ ድርድሩ ወደተፈለገው ደረጃ ሊሄድ እንዳልቻለ አስታውቀዋል።

ግብፅ በአንድ በኩል ታሪካዊ ተጠቃሚነት በሚል መርህ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት እንዳለ አፅንኦት በመስጠትም ተናግረዋል።

"የተለያየ መንገድ ፈልገው ድርድሩን ለማቋረጥ ነው ሃሳባቸው። ለመስማማት የፈለግነውን ስጡን ይላሉ። ካልሰጣችሁን አንስማም ይላሉ። የሚፈልጉትን በሙሉ ካላገኙ አንስማማም ይላሉ። ካልተስማማን ደግሞ ውሃ አትሞሉም ይሉናል" ብለዋል።

በድርድሩ ላይ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌትና ዓመታዊ አለቃቅና አስተዳደርን የተመለከተ ሰነድ ያቀረበች መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ በቀረበው ሰነድ ላይ ውይይት አድርጎ ውጤት ከማምጣት ይልቅ ድርድሩን የማፋረስና ኢትዮጵያን የማጠልሸት ሥራዋን ቀጥላለች በማለት ወንጅለዋል።

"ድርድር በባህርዩ ሰጥቶ መቀበል ነው። እኛ እየተደራደርን ያለነው ምንም መስጠት ከማይፈልጉ ነገር ግን ሁሉንም መውሰድ የሚፈልጉ ኃይሎች ጋር ነው።

"ከእንዲህ አይነቱ ኃይል ጋር መደራደር በጣም አስቸጋሪ ነው። ሁሉንም ልውሰድ ከሚል ኃይል ጋር መደራደር ምንም አይነት ስምምነት ላይ ሊደረስ አያስችልም" የሚሉት አቶ ገዱ በግብፅ በኩል የሚታየው "ስስታምነት" ነው ብለውታል።

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያ የአባይን ውሃን በፍትሐዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት መርህ የመጠቀም እንጂ የታችኞቹ ተፋሰስ አገራትን በፍጹም የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላትም አረጋግጠዋል።

ነገር ግን በግብፅ በኩል የሚታየው በድርድሩ ችግሮችን የመፍታት አካሄድ ሳይሆን በተለያዩ አቅጣጫዎች በመሄድ ኢትዮጵያ ላይ ጫና የመፍጠር አካሄድ ነው ብለዋል።

"በድርድሩ የተለመደ አቀራረብ ይዘው ነው የመጡት፤ በአንድ በኩል ከእኛ ጋር ይደራደራሉ በሌላ በኩል ደግሞ ወደተለያዩ ዓለም አቀፍ አካላት በተለይም ለፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን ለማቅረብ ጥረት ያደርጋሉ። አሁንም በድርድሩ ሂደት አንድ እግራቸውን ኒውዮርክ (የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት) ሌላ እግራቸውን ድርድሩ ውስጥ አድርገው ቀጥለዋል። ሁለት መንታ መንገድ ይዘው ነው እየተደራደሩ ያሉት" ብለዋል።

ግብፅ ለዘመናትም ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ያላትን ጥቅም እንዳታስከብር ሴራ ስትጎነጉን ኖራለች በማለት የወነጀሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግድቡን ለመስራት አቅም እንዳይኖር፣ እንዳይሰራ እንዲሁም ኢትዮጵያን በማዳከም ግብፅ እየሰራች ነው ብለዋል።

በተለይም ከሰሞኑ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪህ እየተደረገ ባለው የሦስትዮሽ ድርድር ምንም ለውጥ እንዳያመጣና ስምምነት ላይ ሳይደረስ የግድቡ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት ሥራ ለመጀመር ኢትዮጵያ መወሰኗ የግብፅን ጥቅም የሚጋፋ በመሆኑ አቤቱታዋን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደምታስገባ አስታውቀዋል።

ይህንንም አስመልክቶ በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ አቋም ምንድን ነው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም አቶ ገዱ ምላሽ ሰጥተዋል።

"ለተባበሩት መንግሥታትም ይውሰዱት። የትም ቦታ ይውሰዱት ፤ የፈለገውን ነገር ይበሉ። ኢትዮጵያንም ስሟን ያጥፉ አንዳንድ ጊዜም ያስፈራሩ። የራሳችንን ከአገራችን የሚመነጨውን ውሃ፣ በራሳችን ግዛት የሚገነባውን ግድብ የአባይ ውሃ የመጠቀም መብታችንን በምንም ተአምር አሳልፈን ልንሰጥ አንችልም። ይሄንን ማወቅ አለባቸው፤ ለግብፅ ሕዝብም ማሳወቅ ኦለባቸው" ብለዋል።

ግብፅ የሦስትዮሹን ድርድር አቋርጣ ከወጣች ሦስቱ አገራት ተቀምጠው የሚነጋገሩበት ጉዳይ ይፈርሳል፤ ኢትዮጵያም ከዚህ በኋላ ለድርድር የምትቀመጥበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም ብለዋል። ለድርድር ወደ ኋላ እንደማትመለስም አስታውቀዋል።

በውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ የሚካሄደው ድርድር የሚቀጥል ሲሆን በደቡብ አፍሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና አሜሪካ ታዛቢነትም እየተካሄደ ነው ያለው።

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሦስቱ አገራት ድርድር የግድቡ የመጀመሪያ ሙሌት እና ዓመታዊ አለቃቅ ላይ ብቻ የተወሰነ እንደሚሆን ገልፆ በግብጽ በኩል ድርድሩ ከሕዳሴው ግድብ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ አልፎ በውሃ ድርሻና አጠቃቀም ላይም እንዲሆንና የኢትዮጵያን የወደፊት በአባይ ውሃ የመጠቀም መብትን የሚገድብ ዓይነት ስምምነት ላይ እንዲደረስ ፍላጎቶች ያሉ መሆናቸውንም ጠቁሟል።

ይህንንም ተከትሎ ከየግብፅ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ የሦስቱ አገራት ድርድር እንደተፈለገ መካሄድ ያልቻለው በኢትዮጵያ ችግር ነው ማለታቸው ውንጀላ መሆኑን የገለፀው ሚኒስቴሩ፤ በተቃራኒው ስምምነቶቹ ውጤታማ መሆን ያልቻሉት ግብፅ የቅኝ ግዛትን የውሃ ስምምነት ሙጥኝ ብላ በመያዟ እንደሆነ ገልጿል።

ይህ ስምምነት ኢትዮጵያንም ሆነ የላይኛው ተፋሰስ አገራትን የተፈጥሮና ተገቢ የውሃ መብታቸውን የሚከለክል ነው ብሏል።

ሚኒስቴሩ አክሎም የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብንም ግራ ለማጋባትም ሆነ ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ስምምነትን እንድትቀበል የሚደረግ ጫና፣ ግፊትም ሆነ ዘመቻ ተቀባይነት የለውም ብሏል።

ኢትዮጵያ በሌለችበት የተፈረመ ስምምነት እንዲሁም ሕጋዊ ከሆነው የአባይን ወንዝ መጠቀም መብት ለመካለከል ግብፅ የምትሄድበት መንገድንም እንደሚቃወም አስታውቋል።

አገራቱ የግድቡን ደኅንነት ሕጎች፣ አካባቢያዊና ማኅበራዊ ግምገማ ጥናት እንዲሁም መመሪያዎችና ሕጎች አጠቃቀም ላይም የጋራ መግባባት ላይ እንደተደረሰም ገልጿል።