ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምርጫ ቦርድ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ገለጸ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ እየተካሄደ ባለው አገራዊ ምርጫ እስካሁን ድረስ ያጋጠመ የጸጥታ ችግር የለም ሲሉ ተናገሩ።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንም በበኩሉ በአገር አቀፍ ደረጃ እስከአሁን ባሰባሰበው መረጃ መራጩ ሕዝብ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላማዊና በተረጋጋ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ገልጿል።
ሰብሳቢዋ አክለውም አምቦ 1 የሚባለው ጣቢያ ላይ ከተሰራጨ መረጃ ጋር በተያያዘ አስፈጻሚዎች ከምርጫ ጣቢያው ገለል እንዲሉ መደረጉን ነገር ግን ምንም ያጋጠመ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።
"ምርጫውን ዳግም እናስጀምራለን። የተፈጠረ ነገር ግን የለም።"
ምርጫ መካሄድ ባለባቸው ቦታዎች አብዛኞቹ በሰዓታቸው ከፍተው መራጮችን ሲያስተናግዱ መቆየታቸውን ሰብሳቢዋ በመግለጫቸው ላይ አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከማለዳ ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ለውድድር አቅርበዋል።
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤቶች የሚወዳደሩት 8,209 ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል 125 የሚሆኑት የግል ተወዳዳሪዎች መሆናቸወን የምርጫ ቦርድ መረጃ ያሳያል።
በሐረሪና በሶማሊ ክልሎች ምርጫው ጳጉሜ 1/2013 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በተጨማሪ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ከምርጫው ጋር ሰኔ 14 በአንድ ቀን እንዲካሄድ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ጳጉሜ 1/2013 ዓ.ም እንዲካሄድ ተወስኗል።
በተጨማሪም ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በዛሬው ዕለት በትግራይ ክልል አይካሄድም።
በስድስተኛው ምርጫ ላይ ድምጽ ለመስጠት 37 ሚሊዮን 408 ሺህ 600ዜጎች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ መካከልም 20 ሚሊዮን 317 ሺህ 472 ወንዶች እንዲሁም 17 ሚሊዮን 91 ሺህ 128 ሴቶች ናቸው።
ገዢው ብልጽግናፓርቲ 2,432 ተወዳዳሪዎችን በማቅረብ በዕጩዎች ብዛት ቀዳሚ ሲሆን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) 1,385 ዕጩዎችን እንዲሁም እናት ፓርቲ ደግሞ 573 ዕጩዎችን በማቅረብ ዋነኞቹ ናቸው።
ዛሬ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በሚካሄደው ምርጫ ለ445 የፓርላማ መቀመጫዎች ድምጽ የሚሰጥ ሲሆን ለ64ቱ ወንበሮች ደግሞ ጳግሜ 1/2013 ዓ.ምድምጽ ይሰጣል።
በአዲስ አበባ ኃላፊነት የጎደላቸው የዘጠኝ ምርጫ ጣቢያዎች ምርጫ አስፈጻሚዎች በሰዓቱ አለመክፈታቸውን የገለፁት ብርቱካን፣ በ9 ጣቢያዎች 29 ምርጫ አስፈጻሚዎች ወደ ሥራ አስገብተናል ሲሉ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ በአንድ የምርጫ ጣቢያ መራጮች የተመዘገቡብት መዝገብ መጥፋቱን ተናግረው ጉዳዩን እንደሚያጣሩ አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ ከዚያ ምርጫ ጣቢያ ካርድ የወሰዱ ሰዎች ካርዳቸውን በመያዝ ድምጽ እየሰጡ መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደ ሰብሳቢዋ ገለጻ በአንዳንድ ቦታዎች የምርጫ ቁሳቁስ እጥረት ማጋጠሙን ገልፀው "ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ እንጠይቃለን" ብለዋል።
በጥቂት ቦታዎች ላይ የምርጫ ቦርድ አስፈጻሚዎች ታዛቢዎችን ወደ ምርጫ ጣቢያ አናስገባም ብለው የነበረ ቢሆንም፣ ማስተካከያ መደረጉን ተናግረዋል።
ምርጫ አስፈጻሚዎች ይህን ማድረግ አይችሉም ሲሉ አክለዋል።
በደቡብ ክልል አንድ ምርጫ ጣቢያ ሰሚያዊ ሳጥን መሰረቁን የተናገሩት ሰብሳቢዋ፣ እነዚህ ጣቢያዎች ብብር እና ጌቾች የሚባሉ ሁለት የምርጫ ክልሎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች የክልል ምክር ቤቶች እና የተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጥባቸው ምርጫ ጣቢያዎች እንደሆኑ በማስታወስ ለብብር መሄድ የነበረበት ወደ ጌቶቾ ተልኳል ብለዋል።