ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
185 ሴቶች ብቻ ድምጽ የሚሰጡባት የጣና ደሴት
ጣና ግርማ ሞገሱ ልብ ያሸፍታል፡፡ ከባሕር ዳር ጎንደር ነው የተነጠፈው፡፡ እስከ ጎርጎራ፡፡
3ሺህ 673 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ይሰፋል፡፡
ከሰሜን ደቡብ 104 ኪሜትር ይረዝማል፡፡ ከምሥራቅ ምዕራብ 66 ኪሎ ሜትር ነው፡፡
ከባሕር ዳር ርቆ የሚገኘው ደቅ ደሴት 37 ኪሎ ሜትር ላይ ነው የሚገኘው፡፡ በግምት እስከ 14ሺህ ሰዎች ይኖርበታል፡፡ እዚያ እርሻ ሁሉ አለ፡፡ ትልቅ ደሴት ነው፡፡
ደቅ በውስጡ 7 አድባራትን ይዟል፡፡ ለዚያም ነው የሰባት ደብር አገር ብለው የሚጠሩት፡፡
ደቅ ደሴት ሰፊ ከመሆኑ አንጻር ሦስት ምርጫ ጣቢያ ተቋቁሞለታል፡፡ ደቅ 01ሀ፣ ደቅ 01ለ እና ደቅ 02ሀ ይባላሉ፡፡
ደቅ ሩቅ ነው ይቅርብን፡፡
ሌሎች ብዙ አማራጮች አሉን፡፡
ምክንያቱም በጣና 37 ደሴቶች ይገኛሉ፡፡ እንዲያ የሚሆነው ግን ባሕረ ገቦቹን (Peninsula) ቆጥረን ነው፡፡
በቅርብ የሚገኘው ደሴት ደብረማያርም ነው፡፡ በጀልባ የሩብ ሰዓት መንገድ ነው፡፡
ከዚያ በጀልባ እልፍ ስንል ክብራን ገብርኤልና እንጦስ ደሴቶች አሉ፡፡ ጎረቤታሞች ናቸው፡፡ ያማምራሉ፡፡ ያሳሳሉ፡፡ ችምችም ብለው ይታያሉ፡፡ አረንጓዴ ለብሰዋል፡፡
ክብራን የወንዶች ገዳም ሲሆን እንጦስ የሴቶች ነው፡፡
በጣና ደሴቶች በደምሳሳው በሁለት ይከፈላሉ፡፡ አንድነት ደሴትና ማኅበራዊ ደሴት ተብለው፡፡
አንድነት ደሴቶች መንፈሳዊ ናቸው፡፡ ደብር ስለሆኑ ምርጫን የመሰለ ዓለማዊ እንቅስቃሴ አይነካቸውም፡፡ ክብራንና ገብርኤል እና እንጦስ ከዚህ ይመደባሉ፡፡
ዘጌ እና ደቅ ግን በርካታ አድባራት በውስጣቸው ቢይዙም መደበኛ ነዋሪዎች አሉባቸው፡፡ ስለዚህ ምርጫ ጣቢያም ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡
ታዲያ ወደ ዘጌ ባሕረገብ ደሴት ለምን አናቀናም?
ከባሕር ዳር አቻዮ ባለሞተር ጀልባ ተኮናትሮ ዘጌዎች ዘንድ ለመድረስ አንድ ሰዓት ይፈልጋል፡፡ ጀልባው ጣናን እየሰነጠቀ መብረር ይኖርበታል፡፡ አሊያ ከዚያም በላይ ሊወስድ ይችላል፡፡
ዘጌ ባሕረ ገብ ናት ብለናል፡፡ በጀልባ 14 ኪሎ ሜትር ብትርቅም በየብስ ከባሕር ዳር 28 ኪሎ ሜትር ነው፡፡
በዘጌ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ ጥንታዊ ናቸው፡፡ ዘጌ ጊዮርጊስና ኡራ ኪዳነ ምሕረት በይበልጥ ይጠቀሳሉ፡፡ ጎብኚ አንጀቱ ርስ የሚሰናበታቸው ሥፍራዎች ናቸው፡፡
ዘጌ ደሴትና ምርጫ
በባሕር ዳር ሦስት ምርጫ ክልሎች አሉ፡፡
ከነሱ ውስጥ ገዳማቱ የሚገኙት ዘጌ መሸንቲ በሚባል ምርጫ ክልል ነው፡፡
ወደ ዘጌ ደሴት እንዝለቅ፡፡ በዚያ ሦስት ቀበሌዎች አሉ፡፡
ሁለቱ ቀበሌዎች ባሕረ ገብ ናቸው፡፡ ኡራና ይጋንድ ይባላሉ፡፡
ሦስተኛው ግን የብስ ነው፡፡ 01 ዘጌ ቀበሌ ይባላል፡፡ ከተማም ነው፡፡ከባሕር ዳር ጋር በየብስ ይገናኛል፡፡ አሁን እንዲያውም ግሩም መንገድ እየወጣለት ነው፡፡
እኛ ትኩረታችንን በዘጌ ኡራ ቀበሌ ብቻ ብናደርግ ይሻላል፡፡ ይጋንድ ቀበሌ ለጊዜው ይቅርብን፡፡ ጊዜ የለንም፡፡
በዘጌ ኡራ ውስጥ ሁለት ምርጫ ጣቢያ ጎብኝተናል፡፡ ኡራ 01 ሀ እና ኡራ 01ለ ይባላሉ፡፡
በኡራ 01 ሀ ያገኘናት በለጠች የምርጫ አስተባባሪ ናት፡፡ መጠነኛ ድንኳን ዘርግታ የምርጫ ቁሳቁስ እስኪደርስላት እየጠበቀች ነበር፡፡ ‹አሁን ይደርሳል ብለውኛል እየጠበቅኩ ነው› አለችን፡፡
አብረዋት አንድ ሁለት ሦስት ሰዎች አሉ፡፡ ተፍ ተፍ ይላሉ፡፡ እንደነገሩ፡፡
እኛን ሲያዩ ቆቅ ሆኑ፡፡ ጋዜጠኛ እንዴት እዚህ ድረስ መጣ ብለው የተደነቁ ይመስላል፡፡
በለጠችም በከፍተኛ ጥርጣሬ ስትመለከተን ከቆየች በኋላ የመራጮችን ቁጥር አትናገሩ ተብለናል አለችን፡፡
‹ቪዲዮ መቅረጽም ክልክል ነው› ተብለናል፣ ይቅርባችሁ ወንድሞቼ› ብላ በትህትና አስጠነቀቀችን፡፡
አግባብተናት የምርጫ ካርድ የወሰዱ የደሴቲቱ፣ በተለይም እሷ የምትመራትን የኡራ 01ሀ ዜጎችን ቁጥር እንድትነግረን ተማጸንን፡፡
በደሴቲቱ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችስ እነማን እንደሆኑ ጠየቅናት፡፡ እምብዛምም አታውቃቸውም፡፡
ያነጋገርናቸው ነዋሪዎችም በደሴቲቱ ተፎካካሪ ፓርቲ መጥቶ ቀስቅሶ እንደሁ ብንጠይቅ የሚያውቅ አጣን፡፡ ዛፍ ግንድ ላይም ሆነ ቋጥኝ ላይ የተለጠፈ ፖስተር አጣን፡፡ ለአመል ያህል እንኳ ብናስስ የለም፡፡
የምርጫ ጣቢያ ኃላፊዋ በመጨረሻ በሷ ምርጫ ጣቢያ 3 ጎጦች እንዳሉ ገለጸችልን፡፡ ፈራ ተባ እያለች፡፡ ለችግር እንዳታጋልጡኝ የምትል ይመስላል፡፡
ሦስቱ ጎጦች አዘዋ ማርያም፣ ኡራ ኪዳነ ምሕረትና ዋሻ መድኃኒዓለም ተብለው ይጠራሉ፡፡
በድምሩ ስንት መራጮች እንደሚጠበቁ ጠየቅናት፡፡579 ናቸው፡፡ ወንድም ሴትም ተቆጥረው ነው ታዲያ፡፡
አመስግነናት ተሰናበትን፡፡
ቀጥለን በዚያው በዘጌ ኡራ ሌላኛው የምርጫ ጣቢያ ሄድን፡፡
በዘጌ ኡራ ከቦታ ቦታ ውር ውር የሚሉ አንድ 6 የሚሆኑ ባጃጆች አሉ ተባልን፡፡ የደሴቲቱ ብርታት ናቸው፡፡ አንድ ሁለቱን ደውለን ብንጠራቸውም ሥራ ላይ ነን ብለው ቀሩ፡፡
አማራጭ አልነበረም፡፡ በእግር ወደ ኡራ 01ለ ምርጫ ጣቢያ ሄድን፡፡
አሁንም ከዘጌ ደሴት አልወጣንም፡፡ ምርጫ ጣቢያ ቀየርን እንጂ፡፡
በጠባብ መንገድ እየተሸሎኮለኩን በግማሽ ሰዓት ኡራ 01ለ ተቃረብን፡፡ ዘጌ በር ደረስን፡፡
ነዋሪዎች ሰብሰብ ብለው ቡና እያፈሉ ደረስን፡፡ አነስ ያለች የድግስ ድንኳን ተዘርግታለች፡፡ ምርጫ ጣቢያ ናት፡፡
ጋዜጠኞች መሆናችንን እና ከሩቅ አገር መምጣታችንን ስንነግራቸው ጠብ እርግፍ ብለው አስተናገዱን፡፡ ፈገግታቸው ያጠግባል፡፡
ሙሉዓለም ዳምጤ ትባላለች፡፡ በዘጌ ደሴት የኡራ ቀበሌ ሥራ አስኪያጅ ናት፡፡
ሙሉዓለም የደሴቲቱን ቀበሌ እጥር ምጥን ቅልጥፍጥፍ ባለ ቋንቋ አስተዋወቀችን፡፡
በዘጌ ደሴት የኡራ ቀበሌ ነዋሪዎች ሎሚና ቡና በመሸጥ እንደሚተዳደሩ፣ የዘጌ ‹ኮከል› የተባለ ቡና በጣዕሙ ተለክቶ በዓለም አንደኛ ደረጃን እንደተጎናጸፈ ሙሉዓለም ነገረችን፡፡
አደስና ጌሾም በደሴቲቱ እንደሚነገድ አብራራች፡፡
በደሴቲቱ ጌሾም ተሸምጥጦ፣ ደርቆ ይሸጣል፡፡ ለአረቄ፣ ጠጅ፣ ጠላ ግብአት ይሆናል፡፡
ኡራ ቀበሌ የሕዝብ ብዛቷ መቶ ሺዎች አይደለም፡፡ ሚሊዮን አይባልም፡፡ ከዚህ ሺ በላይ ይገመታል ተብሎም አይገመትም፡፡
ጠቅላላ ሕዝብ ብዛቷ እቅጩ ይታወቃል እንጂ፡፡ እንደ ተማሪ ቤት ነዋሪዎቿ በስም ሁሉ ሊጠሩ ይችላሉ፡፡
የኡራ ቀበሌ ሕዝብ ስንት ነው አልናት ሥራ አስኪያጇን፡፡
‹ልጅ አዋቂ ተቆጥሮ አሁን 2ሺህ 734 ብቻ ነን፡፡› አለች፡፡
ለምርጫ የበቁና ካርድ የወሰዱት ወንድና ሴቶች በድምሩ 323 ናቸው፡፡
ከነዚህ ውስጥ 138ቱ ወንዶች ናቸው፡፡ ከመራጮቹ ቁጥር ከወንዶቹ የሴቶቹ ይበልጣል፡፡ ይበልጣል እንበል እንጂ ብዙ አይደለም፡፡ 185!
የዚች የዘጌ ኡራ ምርጫ ጣቢያ ኃላፊ ወጣት መልካሙ ይባላል፡፡
ለመሆኑ ነገ ጠዋት 12 ሰዓት ጀምራችሁ ታመሻላችሁ ወይስ ከቁርስ በፊት ፉት አድርጋችሁት ድንኳን ታፈርሳላችሁ?›› አልነው፡፡
323ቱም መራጮች ከረፋድ በፊት ድምጻቸውን ሰጥተው ምርጫውን ፉት አድርገውት ቢሄዱስ?
‹‹እኛ የምርጫ ሕጉን ጠብቀን ነው የምንሠራው፡፡ ምንም ትንሽ መራጭ ብንሆንም እስከ ምሽት 12 ሰዓት ድረስ አለን››
‹‹ረብሻ ይፈጠር ይሆን ? የየብስ ሰው ስጋት ላይ ነው፡፡ እናንተስ ትሰጋላችሁ?›› አልነው፡፡
‹‹እረ በፍጹም!››ብሎ ጀመረ፡፡
‹‹እንደምታየው ገዳም ያለበት ደሴት ነው፡፡ ንቃተ ሕሊናው ከፍ ያለ ሕዝብ ነው የሚኖረው፡፡ አብዛኛው ፊደል የቆጠረ ነው፡፡ መንፈሳዊ ነው፡፡ ፍጹም ሰላማዊ ቦታ ነው፡፡ ይቺን ታክልም ስጋት የለን››