ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምርጫ 2013፡ኢሰመኮ በምርጫው ወቅት የሰብአዊ መብቶች ክትትል እንደሚያደርግ ገለፀ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰኞ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በሚደረገው ብሔራዊ ምርጫ ላይ የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ለማድረግ ባለሙያዎች ማሰማራቱን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ዛሬ እሁድ ሰኔ 13/2013 ዓ.ም በማኅበራዊ የትስስር ገፁ ባወጣው መግለጫ የሰብአዊ መብቶችን ሁኔታ ለመከታተል ያስችል ዘንድ የምርጫ ክትትል ቡድኖች ማቋቋሙንና ምርጫ በሚካሄድባቸው ሁሉም ክልሎች ባለሙያዎች ማሰማራቱን አመልክቷል።
ኮሚሽኑ ለዚህም በተሻሻለው የማቋቋሚያ አዋጁ አንቀፅ 6 መሰረት በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅን ክትትል የማድረግ ስልጣን እና ኃላፊነት እንደተሰጠውም አስታውቋል።
እነዚህ ቡድኖች በምርጫው ዕለት እና ከምርጫው በኋላ ባሉት ቀናት በተለያዩ ክልልሎች በመገኘት ምልከታ እንደሚያደርጉም በመግለጫው ሰፍሯል።
በምርጫው ላይም መራጮችን ጨምሮ የምርጫ አስተባባሪዎች፥ የፀጥታ አካላት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ዕጩዎች፣ ታዛቢዎችንና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር መረጃዎችን እንደሚሰበስቡ ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ በፖሊስ ጣቢያዎች እና በህክምና ተቋማትም ተገኝተው አስፈላጊውን ክትትል እንደሚያደርጉም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ባለሙያዎቹ ሥራቸውን በአግባቡ ይወጡም ዘንድ የኮሚሸኑን መለያ ካርድ ለያዙ በሙሉ አስፈላጊው ትብብር እንዲደረም ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል።
በዚህ ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ መረጃ ያለው ማንኛውም ሰው ለክትትል ቡድኑ አባላት ወይም በኮሚሽኑ ነፃ የስልክ መስመር በመደወር መረጃ መስጠት ይቻላል ተብሏል።
ኢሰመኮ በምርጫው ወቅት የሰብአዊ የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን ለመታዘብ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ቦርዱ ጥያቄውን እንደማይቀበል ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን መታዘብ ከሥራዎቹ መካከል አንዱ መሆኑን በመግለጽ ጥያቄ ያቀረበው ኢሰመኮ፤ ተቀባይነት ያላገኘው በታዛቢነት እንዲሳተፉ ከተፈቀደላቸው አካላት መካከል ባለመካተቱ መሆኑን ቦርዱ ገልጿል።
ቢቢሲ ከታማኝ ምንጮቹ ያገኘው ደብዳቤ የተሻሻለውን የምርጫ ሕግ በመጥቀስ "ኢሰመኮ የታዛቢነት፣ የጋዜጠኝነት ወይም ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲ እና የግል ዕጩ ወኪል ስላልሆነ ቦርዱ የይለፍ ካርድ የሚሰጥበት የሕግ አግባብ ባለማግኘቱ ጥያቄውን ተቀብሎ ማስተናገድ አልቻለም" ሲል ይገልጻል።
ኢሰመኮ ለቦርዱ ሰብሳቢ ሰኔ 08/2013 ዓ.ም የላከው ደብዳቤ ውሳኔው አግባብ አይደለም፤ በማለት ለቦርዱ ሰብሳቢ አቤቱታውን አቅርቧል።
ይህም የተሻሻለውን የኮሚሽኑን አዋጅ በመጥቀስ ለኮሚሽኑ ከተሰጡት ተግባር እና ኃላፊነቶች ውስጥ አንዱ ምርጫን መታዘብ የሚል እንደሚገኝበት በመጥቀስ ያስረዳል።
ቦርዶ ለኮሚሽኑ በላከው ደብዳቤ ላይ የተሻሻለው የኮሚሽኑ አዋጅ በምርጫ ወቅት ኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶችን አጠባበቅ በተመለከተ ክትትል እንዲያደርግ ስልጣን እንደሚሰጠው እንደሚረዳ ገልፆ፤ ነገር ግን ይህንን የመታዘብ ሥራ ምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ እንዲገባ የሚያስችለው የይለፍ ካርድ ከሚሰጣቸው አካላት ውስጥ የምርጫ አዋጁ አያካትተውም ብሏል።
ይህ በዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የተፈረመው ባለ ሁለት ገፅ ደብዳቤ ከተጠቀሱት 10 ነጥቦች ውስጥ ሁለተኛው "ኮሚሽኑ ይህንን ተግባር እና ኃላፊነቱን የሚወጣው በምርጫ ጣቢያዎች ጭምር በመገኘት ነው" ሲል የሞገተ ሲሆን "ለአብነትም የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ መሆናቸውን ለመረጋገጥ በምርጫ ጣቢያ በመገኘት የሚጣራ ነው" ሲል ጠቅሷል።
የኢሰመኮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አሮን ማሾ ለቢቢሲ በቦርዱ እና በኮሚሽኑ መካከል ንግግሮች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረው ነበር። ኢሰመኮ ለምርጫው ያሰማራቸው ባለሙያዎች በምርጫ ጣቢያዎች ላይ መግባት የሚያስችላቸው የይለፍ ካርድን በተመለከተ ያለው ነገር የለም።
ባለሙያዎቹ ክትትሉን በምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ስለማድረጋቸው የታወቀ ነገር የለም።