ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አገራት ፍልስጥኤምና እስራኤል ግጭቱን እንዲያረጋጉ ጠየቁ
በእስራኤላውያን እና ፍልስጥኤማውያን መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ እንደ አሜሪካ፣ አውሮፓ ሕብረት እና ዩናይትድ ኪንግደም ያሉ የተለያዩ አገራት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ እየጠየቁ ነው።
ለውጥረቱ መነሻ የሆነው በምስራቅ እየሩሳሌም በሚገኘው የሼክ ጃራ ክፍል የፍልስጥኤማዊያን ቤተሰቦችን የማፈናቀል አደጋ መጋረጡ ነው።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማዊያን ሰልፈኞች ብሎም ከ 20 በላይ የእስራኤል ፖሊሰች ባለፈው ሶስት ቀናት በነበሩ ግጭቶች ተጎድተዋል።
እሁድ ምሽት ፍልስጥኤማዊያን ሰልፈኞች በእስራኤል ፖሊስ ላይ ድንጋይ ወርውረዋል። ፖሊስ ደግሞ በአፀፋው ስልፈኞችን ለመበተን ሙከራ አድርጓል።
ትናንት ሰኞ ዕለት የፍልስጥኤም ታጣቂዎች ወደ እየሩሳም ሮኬቶችን መተኮሳቸው ደግሞ ነገሮችን ይበልጥ አባብሶታል። በምላሹ የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ኢላማዎች ላይ የአየር ጥቃቶችን ፈጽመዋል።
የፍልስጥኤም የጤና ኃላፊዎች እንደሚሉት ደግሞ እስራኤል ጋዛ ውስጥ በወሰደችው የአየር ድብደባ እርምጃ ህጻናትን ጨምሮ 20 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። እስራዜል ደግሞ ጋዛን ይመሩ የነበሩ ሶስት የሀማስ ቡድን አባላትን በድብደባው ገድያለው ብላለች።
ሰኞ ዕለት በቅዱሱ የእየሩሳሌም አካባቢ ከእስራኤል ፖሊሶች ጋር በተፈጠረው ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን መጎዳታቸውን ተከትሎ ሃማስ የአጸፋ ምላሽ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ደግሞ ሀማስ 'ቀዩን መስመር ተላልፏል' እስራኤልም ብትሆን ለሚደርሰው ነገር በሙሉ በከፍተኛ ኃይል ምላሽ ትሰጣለች ብለዋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን ሀማስ የሮኬት ተኩሱን በፍጥነት እንዲያቆምና ሁለቱም ወገኖች ነገሮችን ለማበብረድ ጥረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይዋ ጄን ሳክ በበኩሏቸው ፕሬዝደን ጆ ባይደን እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ እንዳሳሰባቸውና ግጭቱ በፍጥነት እንዲቆም ጥሪ ማቅረባቸውን አስታውቀዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ኃላፊው ዶሚኒክ ራብ ደግሞ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ''በሮኬት የሚፈጸሙት ጥቃቶች መቆም አለባቸው፤ የንጹሀን ዜጎች ኢላማ መሆንም መቆም አለበት'' ብለዋል።
የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬልም በጉዳዩ ላይ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ''በዌስትባንክ፣ ጋዛ እና ምስራቃዊ እየሩሳሌም እየጨመረ የመጣው ግጭት በፍጥነት መቆም አለበት'' ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት በበኩሉ ትናንት ሰኞ ዕለት በጉዳዩ ላይ አስቸጓይ ስብሰባ አካሂዷል። ነገር ግን እስካሁን ድረስ ምንም አይነት መግለጫ አላወጣም።
ትናንት በተከበረው ዓመታዊው የእየሩሳሌም የባንዲራ ቀን ሲደርስ ባንዲራ የያዙ ወጣቶች በሙስሊም አካባቢዎች ያልፋሉ ተብሎ ነበር። ይህም የሚካሄደው እስራኤል ምስራቅ እየሩሳሌምን የያዘችበትን ቀን ለመዘከር ነው። በርካታ ፍልስጤማዊያን ይህንን ድርጊት ትንኮሳ ነው ይሉታል።
ሊፈጠር የሚችለውን የጸጥታ ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባትም ይህ ቀን በዚህ ቦታ እንዳይካሄድ ተወስኗል።