ግብፃዊው መነኩሴ ጳጳስ በመግደላቸው በሞት ተቀጡ

በግብፅ የሚገኝ አንድ ገዳም አበምኔትና ጳጳስ ገድለዋል የተባሉት አንድ መነኩሴ በስቅላት ሞት ተቀጡ።

ጳጳስ ኤፒፋፊኒየስ የተገደሉት ከሶስት አመታት በፊት ቅዱስ ማካርየስ በሚባል ገዳም ሲሆን በከፍተኛ ድብደባ እንደሆነም ተገልጿል።

በግድያው እጃቸው አለበት የተባሉ ሌላ መነኩሴ እንዲሁ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል።

የጳጳሱ ግድያ የግብፅን የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ምዕመናንን በከፍተኛ ሁኔታ ያስደነገጠ ሆኗል። የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ምዕመናን በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ የክርስትና እምነት ቁጥር ይይዛል።

ዋኤል አል ሳድ ታዋድሮስና ሬሞን ራስሚ ማንሱር የተባሉት መነኮሳት የገዳሙን አበምኔትና ጳጳስ በሰሜን ምዕራብ ካይሮ በሚገኝ ዋዲ አል ናቱርን በተባለ ስፍራ እንደገደሏቸው ተዘግቧል። ለግድያው ምክንያትም የተባለው በነበራቸው ልዩነት ሲሆን ይህ ልዩነት ምን እንደሆነ አልተጠቀሰም።

አቃቤ ህግ እንዳለው መነኩሴው ዋኤል አል ሳድ ታዋድሮስ ጳጳሱን በብረት ዘንግ ደብድበው እንደገደሏቸው የተናዘዙ ሲሆን ሌላኛው መነኩሴ ሬሞን ራስሚ ማንሱር ሰው እንዳይመጣ ሲጠብቁ ነበር ተብሏል። የመነኩሴው የስቅላት ሞት ቅጣት እሁድ እለት ተፈፅሟል።

ሬሞን ራስሚ ማንሱር በመጀመሪያ የፍርድ ቤቱ ብያኔ የሞት ፍርድ ፈርዶባቸው የነበረ ቢሆንም በኋላ ይግባኝ ማለታቸውን ተከትሎ ወደ እድሜ ልክ እስራት ተቀይሮላቸዋል።

የጳጳሱን ግድያም ተከትሎ የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ለአዳዲስ መነኮሳት ማዕረግ ከመስጠት ለአመት ያህል ተቆጥባ ነበር።

የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን በግብፅ ዋነኛ የክርስትና እምነት ተከታዮች ቁጥር የያዙ ሲሆን ምንም እንኳን አብዛኛው በግብፅ ቢኖሩም ከአገሪቷ ውጭም አንድ ሚሊዮን አማኞች ይኖራሉ ተብሏል።

የኮፕቲክ እምነት ተከታዮች ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ50 አመተ ምህረት እንደተጀመረ የሚያምኑ ሲሆን ይህም ሃዋርያው ማርቆስ ግብፅን መጎብኘቱን ተከትሎ እንደሆነ ይነገራል።