እስራኤል በሎድ ከተማ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አወጀች

የእስራኤል መንግሥት በእስራኤላዊያን እና አረቦች መካከል ከፍተኛ አመፅ መነሳቱን ተከትሎ በሎድ ከተማ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አውጇል።

በእስራኤል የፀጥታ ሃይሎች እና በፍልስጤም ተቃዋሚዎች መካከል ያለው ግጭትም ተባብሶ ቀጥሏል።

በሎድ ከተማ በተነሳው አመፅ መኪኖች ጋይተዋል እንዲሁም 12 ሰዎች ተጎድታል። የከተማው ከንቲባም ስማቸው ከእርስ በእርስ ጦርነት ጋር ተያይዞ እየተነሳ ይገኛል።

ማክሰኞ ምሽት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በሎድ ከተማ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ መታወጁን ይፋ አድርገዋል። የእስራኤል የድንበር ጠባቂ ፖሊሶችም ከዌስት ባንክ እንዲመጡ ተደርጓል።

በቴል አቪቭ አቅራቢያ ባለችው የሎድ ከተማ የሚኖሩ እስራኤላዊያን፤ አረቦች የጀመሩት የተቃውሞ ሰልፍ ወደ ረብሻ ተቀይሮ ወደ ፖሊስ ድንጋይ በመወርወሩ ፖሊስ ከፍተኛ ድምፅ በሚያሰሙ ፍንዳታዎች ምላሽ ሰጥቷል።

ሰልፈኞቹ ከአንድ ቀን በፊት በረብሻው ህይወቱ ያለፈ ሰውን አስክሬን በበርካታ ቁጥር ተገኝተው ሸኝተዋል።

የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት በሎድ ከተማ በርካታ የንግድ ሱቆች እና ምኩራቦች በእሳት ተያይዘዋል። ሮይተርስ እንደዘገበው አንድ አረብ እየነዳ በነበረበት ወቅት አይሁዶች መኪናውን በድንጋይ አጥቅተዋል።

የፍልስጤም ተዋጊዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል የተኮሱ ሲሆን እስራኤል በበኩሏ ከባድ የአየር ድብደባ በጋዛ ላይ አካሂዳለች።

ባለፉት አመታታት በነበሩ ተመሳሳይ ግጭቶች ቢያንስ 40 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

የፍልስጤም ተዋጊዎች በበኩላቸው እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ባካሄደችው የአየር ጥቃት አንድ ህንፃ ሙሉ ለሙሉ መውደሙን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳኤሎችን ወደ ቴል አቪቭ ተኩሰናል ብለዋል።

የእስራኤል መከላከያ በጋዛ እያካሄደ ያለው የአየር ድብደባ የጋዛ ተዋጊዎች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ገልፆ ይህም በእየሩሳሌም እና ሌሎች አካባቢዎች ለተሰነዘሩ ጥቃቶች ምላሽ ነው ሲል ተደምጧል።

ለሳምንታት የቆየው ይህ ውጥረት ለሙስሊሞችም ሆነ ለአይሁዶች ቅዱስ በሆነቸው እየሩሳሌም የእስራኤል ፖሊስ እና ፍልስጤማዊያን ሰልፈኞች መካከል በነበረው ግጭት ተባብሶ ለውጊያው መነሻ መሆኑ ተነግሯል።

የዓለማ አቀፉ ህብረተሰብም ሁለቱም ወገኖች ውጥረቱን ለማርገብ እንዲሰሩ እየጠየቀ ይገኛል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመካከለኛው ምስራቅ ተወካይ ቶር ዌንስላድ ‹‹ሁለቱም ጎራዎች ነገሩ ወደ ለየለት ጦርነት እንዲገባ እያባባሱት ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል።

እስካሁን ድረስ 10 ህፃናትን ጨምሮ 35 ፍልስጤማዊያን እና አምስት እስራኤላዊያን በዚህ ግጭት ተገድለዋል ሲሉ የጤና ባለሞያዎች ገልፀዋል፡፡